‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት… ነው›› (ገላ.፭፥፳፪)
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
የካቲት ፳፰፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? በፈቃደ እግዚአብሔር የጀመርነው ጾመ ሁዳዴ (ጾመ ክርስቶስ) ሁለተኛው ሳምንት ላይ እንገኛለን፡፡ እሑድ ከወላጆቻችን ጋር ቤተ ክርስቲያን በመሄድ እያስቀደስን ነው አይደል? እንደ አቅማችን ደግሞ መጾምም አለብን! ከዚህ ቀደም ከምንጸልየው ጸሎት በተጨማሪ ጨምረን ልንጸልይም ይገባል!
በትምህርታችሁም በርቱና ተማሩ! ወላጆቻችን ከእኛ በጣም ብዙ ነገር ይጠብቃሉ፤ ጥሩ ውጤት እንድናመጣና ወደፊት ትልቅ ደረጃ እንድንደርስም ይመኛሉ፤ ታዲያ እኛ ስንፍናን አርቀን፣ ጨዋታን ቀንሰን፣ በርትተን በመማርና በማጥናት ጎበዝ ልጆች መሆን ይገባናል፤ መልካም! ባለፈው ትምህርታችን ስለ መታዘዝ ተምረን ነበር፤ አሁን ደግሞ ስለ ትዕግሥት እንማራለን፡፡
ትዕግሥት “ቻይ፣ ልበ ሰፊ፣ ትሑት፣ መሐሪ የሆነ ሰው መለያ” ማለት ነው፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ታጋሽ ነው፤ ቅዱስ መጽሐፍ እግዚአብሔር ታጋሽ እንደሆነ ያስተምረናል ‹‹…እግዚአብሔር መሐሪና ይቅር ባይ ነው፤ ከቁጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ›› እንዲል፡፡ (መዝሙር ፻፫፥፰)
ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ ‹‹… የጌታችሁ ትዕግሥት መዳናችሁ እንደሆነ ቁጠሩ…›› በማለት እግዚአብሔር ትዕግሥት ለእኛ መዳን እንደሆነ ነግሮናል፡፡ (፪ኛ ጴጥሮስ ፫፥፲፭)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እግዚአብሔር ታጋሽ ነውና ሥራውን ሁሉ የሚፈጽመው በትዕግሥት ነው፤ አይቸኩልም፤ ሰዎች በሕይወታቸው አንድ ነገር ፈልገው ትዕግሥት አጥተው ሲቸኩሉ (ስንቸኩል) በእኛ መቸኮል እርሱ የዘገየብን ይመስለናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ሁሉን የሚያደርገው በትዕግሥት ነው፡፡ የዘገየ ቢመስልም የሚቀድመው የለም፡፡
የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍና የእግዚአብሔር ትዕግሥት
ዮሴፍ ወደ ግብጽ አገር ተሽጦ በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር ሊያድነው ይችል ነበር፤ ነገር ግን ታገሠ ዓላማ ነበረውና ዮሴፍ ግብጽ ገብቶ ጲጥፋራ በተባለው ሰው ቤት ሠራተኛ ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ፡፡ (ዘፍጥረት ፴፯፥፩፣፴፱፥፩)
ይገርማችኋል ልጆች! አሁንም እዚያ ሆኑ በታማኝኘት ሲያገለግል የቤቱ እመቤት ባላጠፋው ከሰሰችውና ወደ እሥር ቤት ተወሰደ፤ አሁንም እግዚአብሔር መከራውን እንዲችል አደረገው እንጂ አላስፈታውም፤ ታግሶ ዝም አለ፤ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ቢያስፈታው ተመልሶ የሰው ቤት ሠራኛ ይሆን ነበር፤ እርሱ ግን ለታላቅ ክብር ኃላፊነት ፈልጎታልና ታግሶ ዝም አለ፡፡
ከዚያም በእስር በቤት ሰዎች ተዋወቀ፤ ሁለት እስረኞች ሕልም አለሙና ሕልማቸውን እንዲፈታላቸው ጠየቁት፤ አንደኛው እንደሚፈታና የንጉሥ አገልጋይ እንደሚሆን ከነገረው በኋላ በተፈታ ጊዜ እርሱንም እንዲያስፈታው ለመነው (ነገረው)፤ የሚገርመው ግን ያ ሰው ሲፈታ ዮሴፍን ረሳው፤ ዮሴፍ ለመፈታት በመቸኮሉ እግዚአብሔር የረሳው (የዘገየ) መሰለው፤ እግዚአብሔር ግን እየታገሠ ነው፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላም ንጉሡ ሕልም አለመ፤ ሕልሙን የሚተረጉምለት ሰው ሲፈልግ ጠፋ፤ ከዚያም ያ እስር ቤት ሆኖ ዮሴፍን የሚያውቀው ሰው ለንጉሡ ዮሴፍ ሕልም እንደሚፈታ ነገረው፡፡ ዮሴፍም ከእስር ቤት ወጥቶ ገላውን አጥበው፣ ፀጉሩን ላጭተው፣ የሚምር ልብስ አልብሰው ቤተ መንግሥት ወሰዱት፤ ዮሴፍም የንጉሡን ሕልም ፈታለት፤ ንጉሡም ዮሴፍን በቤተ መንግሥት ሾመው፡፡ (ዘፍጥረት ፵፩፥፲፬)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እግዚአብሔር በዮሴፍ የመከራ ጉዞ ውስጥ ዝም ያለው የታገሠው ለምክንያት ነበር፤ ለዚህ ታላቅ ክብር ሊያበቃው ስለፈለገ ታግሦ ዝም አለው፡፡ መታገሥ ታላቅ ዋጋ ያሰጣል፤ ‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት ነው›› በቸኮልን ጊዜ ነገሮች ይበላሻሉ፤ አባቶቻችን በብሒላቸውና በፈሊጣዊ ንግግራቸው ‹‹የቸኮለች አፍስሳ ለቀመች›› በማለት በመቸኮል ኪሳራ (ጉዳት) እንጂ ትርፍ እንደሌለው የነገሩን ለዚህ ነው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ገበሬ በክረምት መጀመሪያ በትዕግሥት ዝናሙን፣ ብርዱን፣ ድካሙን ችሎ ያርሳል፤ ከዚያ ደግሞ ይኮተኩታል፤ ይንከባከባል፤ የተዘራው ሲበቅል ወፍ እንዳይበላው አውሬ ረግጦ እንዳያላሸው ይጠብቃል፡፡
በትዕግሥት ሁሉን ደረጃ በደረጃ ይፈጽማል፤ ከዚያ ሲያድግ አጭዶ፣ ወቅቶ ምርቱን ከገለባው ለይቶ እህሉን በጎተራ ያስገባል፡፡ ይህን ሁሉ ግን በትዕግሥት ያሳልፋል፤ አንዳንዴ የሆነ የምንፈልገው ነገር እኛ በፈለግነው ጊዜ ካልተደረገ የዘገየብን ይመስላል፤ በዚህም ትዕግሥት አጥተን ለቁጣና ለኩርፊያ እንቸኩላለን፤ ግን ይህ መሆን የለበትም፤ መታገሥ አለብን፤ “ቆዩ” ስንባል “እሺ” ብለን በትዕግሥት መጠበቅ አለብን፤ በችኮላ የሚሆን ነገር ሁሉ ይበላሻል፡፡ አያምርም፡፡ ለምሳሌ ብንመለከት እኛ ልጆች ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ ፓይለት ፣…ሌላም ነገር ለመሆን ብንፈልግ በአንዴ አንሆንም፤ ቀስ በቀስ እየተማርን በትዕግሥት ጊዜውን ጠብቀን፣ በርትተን በማጥናት፣ ከክፍል ወደ ክፍል ተሸጋግረን በመጨረሻ የፈለግነውን እናገኛለን እንጂ በአንድ ጊዜ ሁሉን ነገር ካላደረግን ብንል የማይሆን ነገር ነው፡፡
ጻድቁ ኢዮብ
ኢዮብ ለትዕግሥት (ለመታገሥ) ምሳሌ ከሚሆኑን ቀዳሚውና ዋንኛው አባት ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካቸው ተመዝግቦ ከምናገኛው አባቶች አንዱ ነው፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ከክፋት የራቀ ደግና ትሑት ሰው ነው፤ ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር፤ ሁሉ የተሟላለት በቤቱ ምንም ያልጉደለ ልጆች የነበሩት ጻድቅ ሰው ነው፡፡
ታዲያ በአንድ ወቅት የነበረውን ሁሉ አጣ፤ እንደገናም ታመመ፤ በዚህም እግዚአብሔርን እያመሰገነ በትዕግሥት ለብዙ ዓመት ተቀመጠ፤ ጓደኞቹ እየመጡ “እስከመቼ ነው እንዲህ ዝም የምትለው? የምታምነው እግዚአብሔር ለምን አያድንህም” እያሉ ተስፋ እንዲቆርጥ፣ እንዳያመሰግን ሲነግሩት እርሱ ግን ታግሦ ዝም አለ።፡ ሕመሙን ችሎ መከራውን ታግሦ የእግዚአብሔርን ማዳን እየጠበቀ ኖረ፤ እግዚአብሔርንም የኢዮብን ትዕግሥት ተመለከተ፤ ከሕመሙም አዳነው ፤የጠፋበትን ንብረት ሁሉ እንደገና አገኘ ፣እግዚአብሔርም ባረከለት፤ ስለ ትዕግሥት (መታገሥ) ሲነሣ ምሳሌ ሆኖ ሲነገርለት ይኖራል፡፡ ‹‹…እነሆ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደታገሠ ሰምታችኋል ጌታም እንደፈጸመለት አይታችኋል…፡፡›› (ያዕቆብ ፭፥፲፩)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! መታገሥ መልካም ነው፤ የምንፈልገውን ነገር እንድናገኝ ያስችለናል፤ አለመታገሥ ግን ለመከራ ይዳርጋል፤ በታገሥን ጊዜ እግዚአብሔር ያየናል፤ ይህን ቆጥሮልን የምንፈልገውን መልካም ነገር ይሰጠናል፡፡ ትዕግሥተኛ መሆን አለብን፡፡ ‹‹ችኮላ የትዕግሥት ጠላት የጸጸት አባት ነው፡፡››
መልካም ልጆች! ለዛሬ በዚህ ይበቃናል! ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በዘመናዊ ትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ! ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም መማርን አትዘንጉ!፡፡ ቸር ይግጠመን!
ይቆየን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!