መልካም አስተዳደር ለሀገር ሰላም
የካቲት ፳፮፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
በቀደሙት ዘመናት የክብር ባለቤት አምላካችን በመለኮታዊ ጥበቡ እና ቅዱስ ፈቃዱ መርጦና ቀብቶ ያነገሠቸው ቅዱሳን ነገሥታት ከሀገራቸው አልፈው ለዓለም ሰላምና አንድነት ተጠሪ ነበሩ፡፡ ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀውና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በመኖር ትእዛዙን ሳያስታጉሉ ይፈጽሙም ስለነበር በሄዱቦት ቦታ የአምላካቸው ጠብቆት፣ ኃይልና ሰላም ስለማይለያቸው አሕዛብንም ጨምረው የመግዛት ሥልጣን በእጃቸው ነበር፡፡
ነገሥታቱ ዘወትር በቅድስናው ስፍራ ከመገኘት አልፎ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው የፈጣሪያቸውን መልካም ፈቃድና ሐሳብ በጸሎት በመጠየቅ ሕዝባቸውን በመልካም አስተዳድረው አልፈዋል፡፡ በፈሪሃ እግዚአብሔር ከመኖራቸውም የተነሣ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ፍቅር፣ ሰላምና በጎነት እንዲሁም ኃይል ሳይለያቸው ኖረዋል፡፡ በዚህም ሕዝባቸው ዘንድ የተከበሩ፣ የተወደዱና የተፈሩ ነበሩ፤ ከሁሉም የበለጠም የአምላካቸውን ቤት አስከብረው አልፈዋል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶ ከመሠረታት በኋላ ሕዝበ ክርስቲያኑ በእርሷ ይመራ ዘንድ ለቅዱሳን ሐዋርያቱ በአስተማራቸው መሠረት ሕግጋቱንና ትእዛዛቱን የመጠበቁ ውዴታና ግዴታ በዚያ ታውጇል፡፡ ደቀ መዛሙሩቱም የእርሱን ትምህርት፣ ፈውሰ ነፍስና ፈውሰ ሥጋ እንዲሁም ተአምራት ሁሉ ጽፈው ለዓለም እንዳስተላለፉት ሁሉ ሕገ እግዚአብሔርም እንዲከበር የትእዛዛት መጻሕፍትን ጽፈው አስተላልፈውልናል፡፡
እነዚህን መጻሕፍት ዐውቆ፣ አንብቦ፣ ተምሮና ተረድቶ የጠበቀ ትውልድ እንዳለፈ ሁሉ በዚያው ልክም ዓለም በቀረጸው የሥጋ ፈቃድ ውጤት፣ ምኞት፣ ዓለማዊነትና ኃጢአት የሚመራ ሕዝብ ተፈጥሯል፡፡ ይህም ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሚጣረስ፣ ሕጉን የሚያስታጉል እና ወደ ጥፋት የሚዳርግ በመሆኑ በዓለም የሚገኘው ሕዝበ ክርስቲያንም ይሁን አሕዛብ በመከራ ማዕበል በመዋዠቅ፣ በችግር አረንቋ ተይዘን፣ ሰላም አጥተንና አንድነታችን ጠፍቶ በየቦታው ተበታትነናል፡፡ የምንኖረውም የይመስል ኑሮ ሆኖብን ደስታ ካጣን ቆይተናል፡፡ ይህ ሁሉ ታዲያ የአምላካችን፣ የፈጣሪያችን የጌታችን ቤት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላሟን በማጣቷ ነው፡፡
የመልካምነት ሁሉ መገኛ የሆነችው፣ ሰብሳቢያችን፣ አስተማሪያችን፣ ቅድስት ስፍራ፣ የእውነተኛ ሕይወት መገኛ፣ የአምላክ ቤት መቅደሳችን በዚህ ጊዜ ተከፍታለች፡፡ ልጆቿን በስደት፣ በሞትና በኃጢአት በማጣቷ ሰላምን ማግኘት አልቻለችም፡፡ ይህን ሰላም ማግኘት የምትችለውም ልጆችዋን በቤቷ ስትሰበስብና በመልካም አስተዳደር ማኖር ስትችል መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ዛሬም ዘወትርም በጥላዋ ሥር እንድንከለል የምትጠራንም ለዚህ ነው፡፡ በቤቷ፣ በቅድስናው ስፍራ እንድንኖርም ታስተምረናለች፤ ትመከረናለች፡፡
ይህን የአምላካችንም የሰላም ጥሪ መስማትና ወደ ቤቱ መመለስ ደግሞ ከእኛ ይጠበቃል፡፡ የሰላም ባለቤት የሆነው ጌታችን ካለንበት ሥቃይ አውጥቶ፣ ችግራችንን ፈትቶና ከመከራ አውጥቶ በመልካሙ፣ በጽድቁ ጎዳና ይመራናል፤ እውነተኛ መንገድ እርሱ ነውና፤ ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› እንዲል፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፮) ሕዝብ ሰላም ከሆነ ሀገር ሰላም ይሆናል፤ ሀገር ሰላም የምትሆነው ደግሞ የሁሉ ፈጣሪ አምላካችን እግዚአብሔር ሲከበር፣ ሲፈራ፣ ሲመለክና ቤቱ በቅድስና ሲጠብቅ ነው፡፡
አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞችና እኅቶች! የሁሉ ነገር መገኛ የሆነችውን ቅድስት ቤታችንን ማክበር፣ በንጽሕናና በቅድስና መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ይህም የሚሆነው ሕጓን ስናከብር፣ ትእዛዞቿን ስንጠብቅና ሥርዓታን ስንፈጽም ነው፡፡
በቤታችን ከቤተ ሰቦቻችን፣ በመኖሪያችን ከጎረቤቶቻችንና ከማኅበረሰቡ፣ በሥራ ቦታችን ከባልደረቦቻችንና አለቆቻችን ጋር ሰላም እንድሆን ቤተ ክርስቲያንን ማክበር ይገባል፡፡ ቤታችን፣ ሀገራችንና ሕይወታችን ናትና የቤተ ክርስቲያንን ሰላም እንጠብቅ!
ይቆየን!