“እግዚአብሔር ሰንበትን ቀደሳት፤ ከዕለታትም ከፍ ከፍ አደረጋት” (ጾመ ድጓ)

በቃሉ እሱባለው

የካቲት ፳፳፻፲  .

ቅዱስ ያሬድም ይህችን ቀን በጾመ ድጓው “ቀደሳ እግዚአብሔር ለሰንበት ወአልዓላ እምኩሉ ዕለት፤ እግዚአብሔር ሰንበትን ቀደሳት፤ ከዕለታትም ከፍ ከፍ አደረጋት” በማለት የቅድስት ሰንበትን ልዕልና በዜማ ያመሰግናታል። (ጾመ ድጓ ዘቅድስት ዘሰንበት)

ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው ይህችን ዕለት “ንዑ ናዕብያ ንዑ ንወድሳ ናክብራ ንዑ ናብዕላ ለበኩረ በዓላት እንተ ይእቲ ሰንበተ ክርስቲያን ዕለት እንተ ገብረ እግዚአብሔር ንትፈሣሕ ወንትሐሠይ ባቲ ወንዘምር ምስለ አሳፍ ነቢይ እንዘ ንብል ተፈሥሑ በእግዚአብሔር ዘረድአነ፤ የበዓላትን በኩር ኑ፤ ከፍ ከፍ እናድርጋት። ኑ እናመስግናት። ኑ እናክብራት። ኑ በዓል እናድርጋት። ይህችውም ሰንበተ ክርስቲያን ናት። ይህች ቀን እግዚአብሔር ሥራ የሠራባት ቀን ናት እንበል። በእርሷም ደስ ይበለን፤ ኀሤትም እናድርግ፤ እንደ ነቢዩ እንደ አሳፍም በረዳን በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ እያልን እንዘምር” እያለ የተቀደሰች ዕለት ሰንበትን ክፍ ከፍ ያደርጋታል፤ ይልቁንም በእርሷ የተደረገውን ያንን የደስታ ቀን እያሰብን፣ ጌታችን በእርሷ ዕለት የሠራውን ድንቅ ነገር እያሰብን እንደ ነቢያቱ እንዘምር ደስም ይበለን” እያለ ያመሰግናታል። (ቅዳሴ ዘአትናቴዎስ)

ቅዱስ ያሬድም የዚህችን ዕለት ታላቅነት እና ክብር ለመግለጽ በእርሷ ስም የመጀመሪያውን ሳምንት “ቅድስት” ብሎ ሰይሞታል። ይህን ብቻ ያይደለ በዚህች ዕለት የተፈጸሙ ታላላቅ የድኅነት ሥራዎችን እያሰብን እንድናከብራትና ነፍስን በሰማያት የሚያሳርፍ ሥራን እየሠራን ከልብ በሚፍለቀለቅ ፍቅር እየተዋደድን ያችን ዕለት እንድናከብራት ያሳስበናል። አዘዞሙ ሙሴ ያክብሩ ሰንበተ በጽድቅ እስመ ሰንበትሰ በእንተ ሰብእ ተፈጥረት፤ አብ ቀደሳ አክብራ ወአልዓላ ለሰንበት እምኩሉ ዕለት፤ አዕበያ፤ ተፋቀሩ በምልዓ ልብክሙ፤ ወአክብሩ ሰንበተ በጽድቅ፤ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት፤ ሙሴ ሰንበትን በእውነት እንዲያከብሩ አዘዛቸው፤ ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥራለችና። አብ ከዕለታት ሁሉ ቀደሳት፤ አከበራት፤ ከፍ ከፍ አደረጋት። በሙሉ ልባችሁ ተፋቀሩ፤ በእውነት ሰንበትን አክብሩ፤ በሰማይም ለእራሳችሁ መዝገብን ሰብስቡ።” (ጾመ ድጓ ዘቀዳሚት ዘሰንበት)

ሌላው በዚህ ሳምንት በቅዳሴው፣ በመዝሙሩ፣ በመልእክታቱ ሁሉ የሚዜመው፣ የሚነበበው ሁሉ ስለ ቅድስና ነው። እግዚአብሔር አምላካችን ሰውን ካለመኖር ወደ መኖር ሲያመጣው በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ነው። “እግዚአብሔርም አለ ‘ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር።” እንዲል መጽሐፍ፡፡ (ዘፍ.፩፥፳፮)

እግዚአብሔር ሰውን ከባሕርይው ቅድስና ተካፋይ አድርጎ፣ በአርአያው ለቅድስና የሚስማማ ባሕርይ ሰጥቶ፣ ለቅድስና የሚስማማ ተፈጥሮን ገንዘቡ አድርጎ ሕይወትን አድሎታል። ይህም ሰውን በፈጠረ ጊዜ ”…በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር…” በሚለው ታውቋል። የእግዚአብሔር  ምሳሌነታችን ደግሞ በቅድስና ነው። ከዚያ መለኮታዊ ክብር ተካፋዮቹ ያደረገን አምላክ የእርሱን መልክእ እና አርአያ እንደያዝን ወደ ቅድስናም ከፍ እንድንል ሲጠራን እንዲህ ይላል፤ “እኔ አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንግዲህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።” (ዘሌ.፲፩፥፵፭)

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም እግዚአብሔር ለእስራኤል የተናገረውን ቃል ይዞ “ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” ያለን የእግዚአብሔር ቅድስና ተካፋዮች እንደ ሆንን እርሱንም በቅድስና መምስል እንዲገባን ሲነግረን ነው። የሐዲስ ኪዳን አማንያን በሕይወታችን ሁሉ ቅድስናን እንድንለብስ ቅድስና መልካችን እና ጌጣችን እንዲሆን ያሳስበናል። (፩ኛ ጴጥ.፩፥፲፭-፲፮)

ቅድስና ከመለኮት ክብር ተካፋይነት የመሆኛ መንገድ ነው። ጾማችን፣ ጸሎታችን፣ ምጽዋታችን፣ መሥዋዕታችን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ ሲሆን እና ወደ መሥዋታችንም ሲመለከትልን የሕይወታችን የሽልማት የቅድስና ነው። ቅድስና ጥንተ ተፈጥሮአችን ነው፤ ሁላችንም በምግባር ከፍ ስንል፣ ያንን ተፈጥሮአችንን ስናድስና አዲስ ሰውነትን ለብሰን ከኃጢአት ስንወጣ የምናገኘው የክብር ልብስ ነው።

የተወደዳችሁ ሆይ! እኛ የሐዲስ ኪዳን ሰዎች በሕይወታችን፣ በኑሮአችን፣ በአካላችን ሁሉ የእግዚአብሔር የቅድስናው ጥላ እንዲታይብን ሆነን መገኘት አለብን። በተቀደሰች ሕይወትም  ጾም፣ ፍሬዋም በሚለቀም አገልግሎት እየተቀደስን የሰውነታችን አካላት ሁሉ በቅድስና ጌጥ የተዋቡ የሰላም ዕረፍት የሚሰጡ መሆን ይገባቸዋል። ከእኛ ከአካላችን አንዳች እንኳ የእኛ የሆነ የለም፤ በዚህ እግዚአብሔር በሚነግሥበት የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ መቅደስ በቅድስና መጠበቅ መንፈሳዊ ግዴታችን ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል። ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ” የሚለን ለዚህ ነው። (፩ኛ ቆሮ.፩፥፲፰-፳)

እግዚአብሔር በባሕርይው ንጹሐ ባሕርይ ነው። ታዲያ እርሱ የሚያድርበት መቅደስ እንደምን ያለ መቅደስ ነው? እርሱ የሚያድርበት ሰውነት እንደምን ላለ ቅድስና የተገባ መሆን ይጠበቅበት ይሆን? እርሱን ደስ ብሎት ማደሪያ ይሆነው ዘንድ የምናዘጋጅለት ቤት (የራሳችን ሥጋ) ከኃጢአት እና ከዐመፅ የተለየ፣ የጽድቃ ዕቃ፣ የጦር መሣሪያ የሆነ፣ የቅድስና ዘውድ የደፋ ሥጋን ልናዘጋጅለት ይገባል። (ሮሜ ፮:፲፪-፲፫)

ተወዳጆች! እግዚአብሔር ቀድሞ ያዘጋጀልንን የዘለዓለም ርስት እንድንወርስ ቅዱሳን በተጓዙበት መንገድ ተጉዘን ከወደቡ (ፍቅረ እግዚአብሔር) እንድንደርስ፣ ለቁስላችን (ኃጢአታችን) ፈውስ እንድናገኝ ደጋግመን መለመን ይገባናል። በጾማችንም ድኅነት ይሆንልን ዘንድ፣ ባለመድኃኒት ጌታም ከመድኃኒቱ በቁስላችን ላይ ያርከፈክፍልን እና  ከሚጠዘጥዘን የኃጢአት ደዌ ዕረፍትን እናገኝ ዘንድ፣ በቅድስና ኖረን በቅድስና የምትገኝ በረከትንም እንድንበላ ከሊቁ ከቅዱስ ኤፍሬም ጋር እንዲህ እያልን እንለምነው፤ “ዕረፍትን ወደምታስገኝ የጌታ ደስታ እንገባ ዘንድ ከቅዱሱ ጋር እየለመንን የጾማችንን በረከት በልቅሶና በንስሓ እንልቀም። እንዲህም እንበል፤ “አቤቱ አንተን የመሰለ ባለመድኃኒት የለም። ያንተ መድኃኒት ፍጹም ድኅነት የሚሰጥ ነው። ምንም እንኳ የመጀመሪያው ቁስል ድኖ ሌላ ቁስል ቢከሰትም ያንተ በለሳን በሁሉም ጊዜያት ፍጹም መድኃኒት ነውና ቁስሉን ያሽራል። (በእንተ ንስሓ ቅዱስ ኤፍሬም፣ ገጽ ፳፮:- ትርጉም ዲያቆን መዝገቡ ከፍያለው)

የዕለቱ ምስባክ፦ “እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ አሚን ወሰናይት ቅድሜሁ ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ፤ ምስጋና እና ውበት በፊቱ ነው፤ ቅዱስነት እና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው።” (መዝ.፺፭(፺፮)፥፭)

ወንጌል፦ ማቴ.፮፥፳፭

ቅዳሴ፦ ቅዳሴ ዘኤጲፋንዮስ

መልእክታት

ዲያቆን (ገባሬ ሰናይ) ፦ ፩ኛ ተሰ፣፬፥፲፫

ንፍቅ ዲያቆን፦ ፩ኛ ጴጥ.፩፥፲፫-ፍጻሜው

ንፍቅ ካህን፦ ሐዋ.፲፥፯-፴

ስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን!