‹‹ልጆች ሆይ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ›› (ኤፌሶን ፮፥፩)
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
የካቲት ፲፯፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? የሁለተኛው መንፈቅ የትምህርት ዘመን እንዴት ነው? ከቀደመው ይልቅ የበለጠ ጠንክራችሁ በመማር ዕውቀትን በመሸመት ጥሩ ውጤትን ለማምጣት እየጣራችሁ እንደሆነ ተስፋችን ነው!
ልጆች! ዐቢይ ጾምን አንድ ብለን እየጀመርን ነው፤ እንደ ዐቅማችሁ ለመጾም እንደምትጥሩም እምነታችን ነው፤ በርቱ! ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም መማርም እንዳትዘነጉ፤ መልካም! ልጆች ለዛሬ ስለ መታዘዝ እንማራለን፡፡
መታዘዝ “እሺ ማለት፣ የተሰጠን ኃላፊነት መፈጸም” ነው፡፡ በትእዛዝ ውስጥ “አድርጉ እና አታድርጉ” የሚሉ መልእክቶች (መመሪያዎች) አሉ፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር እንድንፈጽመው (እንድናደርገው) ያዘዘን እንዳለ ሁሉ እንዳናደርገው ያዘዘን ትእዛዝም አለ፡፡ ለምሳሌ ብንወስድ “አትስረቅ” የሚል ትእዛዝ እንዳናደርገው (ስርቆትን እንዳንፈጽመው) የተከለከልነው ትእዛዝ ነው፡፡ እንድናደርገው ከታዘዝነው ትእዛዝ ለአብነት (ለምሳሌ) ብንመለከት፡፡ ‹‹ሰንበትን አክብር፤ ….ባልንጀራህን ውደድ…፡፡›› እነዚህን የመሳሰሉ ደግሞ ልናደርጋቸው የሚገቡ ትእዛዛት ናቸው፡፡ (ዘጸአት ፳፥፰፣ማቴ.፳፪፥፴፱)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የታዘዙትን መፈጸም በረከትን ያሰጣል፤ አለመፈጸም ደግሞ መርገምን (መከራን) ያመጣል፤ በቅዱስ መጽሐፍ የመታዘዝን ጥቅምና ያለመታዘዝን ጉዳት እንዲህ ተጽፎልናል፤ ‹‹…እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብትሉ ግን ብታምፁ ሰይፍ ይበላችኋል፤ እግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሯልና፡፡›› (ኢሳይያስ ፩፥፲፱)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! መታዘዝ ዋጋው እንጂ ታላቅ ነውና ታላላቆቻችን የሚያዙንን ብንፈጽም እነርሱም ለእኛ የሚያስፈልገንን ሁሉ ያደርጋሉ፤ እኛም የምንፈልገውን መልካም ነገር እናገኛለን፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ኤፌሶን በምትባል አገር ላሉ ምእመናን ጽፎ በላከላቸው አባታዊ ምክሩ ልጆች ለወላጆቻችንን መታዘዝ እንዳለብን መክሮናል፤ ‹‹ልጆች ሆይ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ…›› (ኤፌሶን ፮፥፭) እንዲል፤ ለወላጅ መታዘዝ ምርቃትን ያሰጣል፤ ለወለዱን እኛን ተንከባክበው የሚያስፈልገንን እያሟሉ፣ ለሚያሳድጉን ወላጆቻችንን “እሺ” ብለን መታዘዝ ይገባል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ተጽፎልናል፡- ‹‹ያባት ምርቃት የልጅን ቤት ያጸናልና የእናት እርግማን ግን ሥር መሠረትን ይነቅላል…፡፡›› (መጽሐፈ ሲራክ ፫፥፲) ጠቢቡ ሰሎሞን እናትና አባቱን አክባሪ ትእዛዛቸውን ፈጻሚ ልጅ እንደነበረና ያገኘውን ጥቅም እንዲህ ሲል ይነግረናል (ይመክረናል)፡፡ ‹‹..እኔ አባቴን የምሰማ ልጅ ነበርሁና በእናቴም ዘንድ እወደድ ነበር፤ ያስተምረኝም ነበር፤ እንዲህም ይለኝ ነበር፤ “ልብህ ቃሌን ይቀበል፤ ትእዛዜን ጠብቅ፤ በሕይወትም ትኖራለህ”…›› (ምሳሌ ፬፥፫)
‹‹..እነሆ መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል፡፡›› (መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ፲፭፥፳፩)፤ አያችሁ ልጆች! እግዚአብሔር ያዘዘንን እንዲሁም ወላጆቻችን ያዘዙን ሳንፈጽም ቀርተን በራሳችን ፍላጎት እኛ መልካም ነው (ጥሩ ነው) የምንለውን ብንፈጽም ከመመስገን ይልቅ የሚጠብቀን ወቀሳ ነውና፤ ስንታዘዝ የእኛን ፍላጎትና (ሐሳብ) ሳይሆን ያዘዙንን የታላላቆቻችንን ትእዛዝ ማስቀደም አለብን፡፡
በታዛዥነታቸው አብነት ከሚሆኑን ቅዱሳን የተወሰኑትን እንመልከት
ሀ) አባታችን ኖኅ
አባታችን ኖኅ በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበር፤ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፤ ሴም፣ ካም፣ ያፌት የሚባሉ ሦስት ልጆችም ነበሩት፤ ኖኅ በነበረበት ዘመን ሕዝቡ ሁሉ በደሉና እግዚአብሔር ከጥፋታቸው እንዲመለሱ ነገራቸው (አዘዛቸው)፡፡ ካልተመለሱ ግን እንደሚቀጣቸው አስጠነቀቃቸው፤ እነርሱ ግን እንቢ አንታዘዝም አሉ፡፡
ኖኅ ግን ሕገ እግዚአብሔር በመጠበቅ ይኖር ነበርና ከሚመጣው ቅጣት እንዲያመልጥ መርከብ ሥራ ተብሎ ታዘዘ፤ ኖኅም በእምነት (አምኖ) ታዞ መርከብን ሠራ፡፡ ለጥፋተኞቹ መቅጪያ የሚሆን ውኃ ከሰማይ በመጣ ጊዜ ምድርን አጥለቀለቃት (ሞላት) ኖኅ በሠራው መርከብ እርሱና ቤተ ሰቡ እንዲሆም ከእንሰሳቱ፣ ከአራዊቱ ይዞ በመግባት ከጥፋት ውኃ ዳኑ፡፡
በመታዘዙ አድርግ የተባለውን በማድረጉ ከመከራ ዳነ፡፡ (ዘፍጥረት ፮፥፲፫-፳፪፣ ፯፥፩-፳፬) ‹‹… ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ሰቦዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፤ በዚህም ዓለምን ኮነነ፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ፡፡›› (ዕብራውያን ፲፩፥፯)
ለ) ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለታዛዥነት ምሳሌ ከሚሆኑ አባቶቻችን አንዱ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ነው፤ የተወለደው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምድረ ግብጽ ነው፤ ቁመቱም በጣም አጭር ጽድቁ ግን ከሰማይ የደረሰ ታላቅ ቅዱስ አባት ነው፡፡ ወላጆቹ መልካም የክርስትና ሕይወትን፣ ሃይማኖትን፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርን እያስተማሩት አደገ፤ ዐሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላው የታላቁ አባ ባይሞን ደቀ መዝሙር ሆኖ ተጋድሎንና ትምህርትን ተማረ፤ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር በወቅቱ ከነበሩት ቅዱሳን በትሕትናው፣ በትዕግሥቱ፣ በመታዘዙ ይታወቅ ነበር፡፡
መምህሩ አባ ባይሞን ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ጠርቶ ተፈልጦ የደቀቀ ደረቅ እንጨት ሰጠው ‹‹ምን ላድርገው?›› ቢለው ‹‹ትከለውና ውኃ አጠጣው፤ እንዲያፈራም አድርገው፤ ከዚያም ፍሬውን አምጥተህ አብላኝ!›› አለው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ‹‹እሺ›› ብሎ ወስዶ ተከለው ለሁለት ዓመታትም ሳይታክት ውኃ አጠጣው ውኃውን የሚያመጣበት ቦታ ከገዳሙ ዐሥር ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ነበረው፤ ላቡ ጠብ እስኪል ተሸክሞ እያመጣ የተከለውን ደረቅ እንጨት ውኃ ማጠጣት ቀጠለ፤ በሦስተኛው ዓመት ለምልሞ አበበ፤ ፍሬም አፈራ፡፡
ከፈራው ፍሬም ለመምህሩ ለአባ ባይሞን ወስዶ ‹‹አባቴ እንካ ብላ›› ብሎ ሰጠው፤ አባ ባይሞን ማመን አልቻለም፤ እጅግ አደነቀ፤ አለቀሰም፡፡ ወዲያው ያንን ፍሬ ታቅፎ ወስዶ ለገዳሙ መነኮሳት ‹‹ውሰዱ፤ ብሉ፤ በረከትም አግኙ፤ ይህ የዛፍ ሳሆን የመታዘዝ ፍሬ ነው›› በማለት ሰጣቸው፡፡ አባ ባይሞን በታመመ ጊዜ ለዐሥራ ሁለት ዓመታት አስታሞታል፤ ሊያርፍ ባለጊዜ መነኮሳቱን ሰብስቦ የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር እጅ አስጨበጣቸው፤ ‹‹ይህ የያዛችሁት እጅ የሰው ሳይሆን የመላእክት እጅ ነው›› ብሏቸው ዐርፏል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የታላላቆቻችን ትእዛዝ ሁል ጊዜ ማክበርና መፈጸም አለብን፤ ያ መታዘዛችንን ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ እግዚአብሔርም ይመለከተናል፤ ከሰዎች ምርቃትን ከእግዚአብሔር በረከትን እናገኝበታለን፡፡
ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በዘመናዊ ትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ! ለወላጆቻችሁ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ! በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡
ቸር ይግጠመን!
ይቆየን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!