መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ!

የዲያብሎስን የፈተና ወጥመዶች በጣጥሶ በድል አድራጊነት የተገለጠው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺህ ዐሥራ ሰባት ዓመተ ምሕረት የጾመ ኢየሱስ ሱባኤ አደረሰን፤ አደረሳችሁ!

“አኮ በኅብስት ክመ ዘየሓዩ ሰብእ አላ በኵሉ ቃል ዘይወፅእ እምኣፉሁ ለእግዚአብሔር፡- ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ ኣይኖርም” (ማቴ.፬÷፬)፤

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወዲያውኑ ወደ በረኻ በመሄድ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾመ፡፡

በአርባዎቹ ቀናት ሁሉ በቀንም ሆነ በሌሊት ምንም አልበላም ነበር፤ ካርባ ቀንም በኋላ ተራበ፤ በመብል ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ማጣላት ልማዱ የሆነ ዲያብሎስም መራቡን ኣይቶ ለምን ትራባለህ?

እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ ይሁኑ ብለህ እዘዝና ብላ፤ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለህምን? ይህንን ማድረግ ኣያቅትህም ብሎ በመብል ምክንያት የሱ ታዛዥ እንዲሆን ፈተነው::

በዚህ ጊዜ የጌታችን መልስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” የሚል ነበረ፤

ጌታችን በዚህ አባባሉ የዲያብሎስን ክፉ ሐሳብ የሚንድ እንጂ የእሱ ታዛዥ አለመሆኑን ኣሳየ፤ ዲያብሎስ በዚህ ሳያበቃ በትዕቢት በፍቅረ ንዋይና በባዕድ አምልኮ ሊጥለው ደጋግሞ ሙከራ አደረገ፤ ግን አልተሳካለትም፤

በመጨረሻም ጌታ “ሑር እምድኅሬየ ሰይጣን፣ ሰይጣን ከኋላዬ ወግድ” ብሎ እኩይ ተግባሩን ውድቅ አድርጎበታል፤

እርሱም ተስፋ ቆርጦና በጌታችን መንፈሳዊ ልእልና ተሸንፎ ሂዶአል::

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

ከጌታችን ጾም የምንወስደው ብዙ ትምህርት አለ፤ ከሁሉ በፊት ሰው በሕይወት መኖር የሚችለው በእንጀራ ብቻ ኣይደለም ብሎናል፤ ይህ ኣባባል በሕይወት ለመኖር እንጀራ አያስፈልግም ማለት ኣይደለም፤

ሕይወትን ማኖር የሚቻለው በእንጀራ ብቻ እንደ ሆነ አድርገን እንዳናስብ ግን ቃሉ ያስተምራል፤ይህም በዓለማችን በየዕለቱ የምናውቀው ሓቅ ነው፤ ብዙ ሰዎች እንጀራን ሳያጡ በየዕለቱ ሕይወትን ያጣሉ፤ ምክንያቱም በሕይወት ለመኖር የእግዚአብሔር ቃልም እንጂ እንጀራ ብቻው በቂ አይደለምና ነው::

ዓለማት ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል ሁኑ ተብለው በቃሉ እንደተፈጠሩ፤ በቃሉም ጸንተው እንደሚኖሩ ኋላም በቃሉ እንደሚያልፉ ሁሉ የሰው ሕይወትም በዚህ ቃል ይወሰናል፤

እንጀራ ኖረም አልኖረ ቃሉ በቃ ካለ ያበቃል፤ ኑር ካለ ደግሞ እንጀራ ባይኖርም ይኖራል፤ ስለዚህ በሕይወታችን ወሳኝ ሥልጣን ያለው የእግዚአብሔር ቃል እንጂ፣ እንጀራ ብቻ ኣለመሆኑ ጌታችን በዚህ ኣስተምሮናል::

ከዚህም ሌላ የዲያብሎስን ፈተናዎች እንዴት በድል ማለፍ እንደምንችል ጌታችን በተግባር ኣሳይቶናል፤ ጌታችን ዲያብሎስን ያሸነበፈበት ስልት በመንፈስ ልዕልና እንጂ በዱላም፣ በካባድ መሳሪያም ኣይደለም፤ አለመሆኑንም የድርጊቱ ሂደት በግልጽ ያመለክታል፤ እንግዲያውስ እኛም ዲያብሎስን የምናሸንፈው በዚህ የመንፈስ  ልዕልና ነው ማለት ነው::

ይህም ማለት በእግዚአብሔር የተከለከሉትን ግብረ ኃጣውእ እንድንፈጽም ዲያብሎስ ኅሊናችንን ሲገፋፋው፣ ያን ጊዜ ዲያብሎስ ሊፈትነን እየከጀለ እንደሆነ መንቃት  ያስፈልገናል::

ጌታችን እንዳሳየንም ለክፉው ግብረ ኃጢኣት የእሺታ መልስ ሳይሆን የእንቢታ ግብረ መልስ መስጠት ይገባናል ማለት ነው፤ ይህንን ኣቅዋም የሕይወታችን ቀዋሚ መርሕ ካደረግን፤ ዲያብሎስ እየተሸነፈ፣ እኛም እያሸነፍን እንኖራለን፤ ይህንን ስንለማመድ ሓሳባችን ወይም መንፈሳችን ከዲያብሎስ በላይ የላቀና የተራቀቀ ይሆናል፤

ዲያብሎስ ረቂቅ ነው፤ የሚጣላንም ረቂቁን አእምሮኣችን በመጠቀም ነው፤ እኛም እሱን መዋጋትና ማሸነፍ የምንችለው ረቂቁ ኣእምሮኣችን ከሱ የላቀና የረቀቀ ኣድርገን በመጠቀም መሆኑን መገንዘብ ይገባል፤ይህን ካደረግን እሱ በኛ ላይ  ዓቅም ኣይኖረውም::

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

ጾመ ኢየሱስ እያልን በየዓመቱ የምንጾመው የታላቁ ጾማችን ዓላማ ዲያብሎስን ለማሸነፍ ነው፤ የዲያብሎስ ማሸነፊያ ስልት የመልካም ኅሊና ልዕልና ነው፤

ሰውነታችን በመብልና በመጠጥ ሲደነድን መልካም ኅሊና በውስጣችን ዓቅም ያጥረዋል፤ መልካም ኅሊና ሲያጥረን ዲያብሎስ ዘው ብሎ ይገባና ወደ ክፉ ኅሊና፣ ከዚያም ወደ ግብረ ኃጢኣት ይወስደናል፤ በዚህ ጊዜ እኛ ተሸናፊዎች እሱ አሸናፊ ይሆናል፤

በአንጻሩ ደግሞ ሰውነታችን ከመብልና ከመጠጥ ሲለይ መልካም ኅሊና፣ ቊጥብነት፣ ማስተዋልና ማመዛዘን በውስጣችን ትልቅ ጉልበት ያገኛሉ፤

እነሱ ጐለበቱ ማለት ዲያብሎስ መግቢያ አጣ ማለት ነው፤ እሱ ካልገባ ግብረ ኃጢኣት አንፈጽምም፤ በዚህ ጊዜ ዲያብሎስ ተሸናፊ እኛ አሸናፊዎች እንሆናለን፤ ስለሆነም ጾምን የምንጾመው በዚህ ስልት ዲያብሎስንና ግብረ ኃጢአትን ለማሸነፍ  ነው::

ከዚህ አኳያ ዲያብሎስን ለማሸነፍ መጾም ግድ ስለሆነ ጌታችን በከፈተልንና ባሳየን መንገድ እንጾማለን፤ እንግዲህ በወርኃ ጾም ከመልካም ኅሊና የሚመነጭ መልካም ስራ ማከናወን ግድ ይለናል፤

ምክንያቱም ጾምን የምንጾመው መልካም ኅሊና ኖሮን ለእግዚአብሔር ለመታዘዝና ለመገዛት፣ ከዚያም ከቃሉ በተነገረን መሠረት የተራቡትን ልንመግብ፣ የተራቈቱትን ልናለብስ፣ የተጣሉትን ልናስታርቅ፣ ፍትሕ ያጡትን ፍትሕ እንዲያገኙ ልናደርግ፣ ለንኡሳን የሕብረተ ሰብ ክፍሎች የተለየ ትኵረት ልንሰጥ፤ እኩልና ፍትሓዊ የሀብት ክፍፍል በሰው ልጆች መካከል ልናረጋግጥ፣ ሰብኣዊ ክብር እንዳይነካ ጦርነት፣ ጥላቻ፣ አደገኛ የቃላት ውርወራና መነቃቀፍ እንዲቀር ልናደርግ ነው፤

በዚህ መንፈስ ጾሙን ከጾምን ጾማችን ግቡን መትቶአል፤ ዲያብሎስም ተሸንፎአል ማለት ነው፤ ስለሆነም በዚህ መንፈስ ጾሙን ልንጾም ይገባል፡፡

በመጨረሻም፡-

ወርኀ ጾሙን የተራበውን በመመገብ የተራቈተውን በማልበስ በኃላፊነት ያለን የኅብረተሰብ መሪዎችም ፍትሕንና እኩልነትን በማስፈንና ከነገሮች ሁሉ በፊት ለሰላምና ለአንድነት ቅድሚያ በመስጠት ጾሙን እንድናሳልፍ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን::

መልካም ወርኀ ጾም ያድርግልን!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አሜን!!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ   ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት

የካቲት ፲፯ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ምንጭ የኢ/ኦ/ተ/ ቤተ ክርስቲያን  ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ