ወርኃ የካቲት
መምህር ተስፋ ማርያም ክንዴ
ጥር ፴፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ስድስተኛው ወር “የካቲት” ተብሎ ይታወቃል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ውስጥ የዚህን ወር ቃል “ከተተ” ከሚለው ግስ ከወጣው “ከቲት፣ ከቲቶት” ከሚል ንኡስ አንቀጽ የተገኘ ሲሆን በቁሙ “የወር ስም፣ ስድስተኛ ወር፣ የመከር ጫፍ (መካተቻ)፣ የበልግ መባቻ ማለት ነው” ብለው ተርጉመውታል። (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፭፻፲፭)
ሌሎችም ጸሐፍያን “የካቲት” የሚለው ቃል “ከቲት፣ ከቲቶት” ከሚል የግእዝ ንኡስ አንቀጽ የተገኘ ሲሆን “መውቃት፣ ማምረት፣ መሰብሰብ፣ መክተት” የሚል ትርጉም ይኖረዋል ካሉ በኋላ ይህንም ስም ያገኘው የካቲት ወር አዝመራ (ምርት) ወደ ጎተራ የሚከተትበት ወራት በመሆኑ ነው ብለዋል። (ኅብረ ኢትዮጵያ፣ ከቴዎድሮስ በየነ፣ አዲስ አበባ ፲፱፻፺፱ ዓ.ም፡፡ አንድሮ ሜዳ፣ ገጽ ፫፻፺፭፣ አቡሻክር የጊዜ ቀመር፣ በኢንጅነር አብርሃም አብደላ ገጽ ፵፱) በቁጥር ትምህርት አንዱ ወር በባተበት የትኛው ወር እንደሚብት በቃል የሚጠና ሲሆን የካቲት በባተችበትም ጳጕሜን እንዲሁም የካቲት በባተበት ሳኒታ ሰኔ ይብታል፡፡
በሮማውያን ይህች ወር ሁለተኛ ወራቸው ስትሆን አጭሯ ወር ናት። የቀን ብዛቷም በሦስቱ ዓመት ፳፰ ትሆንና በአራተኛው ዓመት አንድ ጊዜ የጳጉሜን የዕለት ጭማሪ ተከትላ ፳፱ ትሆናለች። ይህማ እንዳይሆን በሮማውያን መቼ ጳጉሜን ለብቻ ትከበራለች? የሚል ቢኖር ልዩነቱ ኢትዮጵያ ከ፲፪ቱ ወር ውጭ ያለውን ትርፍ ዕለት ወይም ፀሐይ ከመውጣቷና ከመግባቷ በፊት ያለውን ብርሃን ለብቻ በኬክሮስ፣ በካልዒትና ከዚያም ባነሱ የጊዜ መስፈሪያ አሐዶች ቀምራ፣ ሰፍራና ቆጥራ ስታውል ምዕራባውያን ግን በዘፈቀደ ከወራቸው ጋር ጨምረው ስለሚያውሏት እንጂ ቀኑስ በሁሉም አለ። ምክንያቱም የምታበራው አንድ ፀሐይ ነውና፡፡ የሮማውያን የዘመን አቆጣጠር ምንም እንኳን መነሻው የሮም ከተማ የተመሠረተችበትን መሠረት ያደረገ ቢሆንም በየጊዜው የተነሡ ነገሥታት እንደቀያየሩትና የወራቱንም ስም በየስማቸው እንደቀየሩት ታሪክ ይነግረናል።
በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ግን ወራቶች ሁሌም ፴ ስለሚሆኑ እንዲህ ዓይነት መለዋወጥ ሳይኖርባት ትከበራለች። በአቡሻክር ትምህርት ፀሐይ የምትወጣባቸውን የምትገባባቸው በምሥራቅ ስድስት በምዕራብ ስድስት መስኮቶች አሉ። አንዱ መስኮት ፴ ከንትሮስ ስላለው ፀሐይ አንዱን ወር ሙሉ በአንዱ መስኮት ትወጣና በቀጣይ ወር ደግሞ ወደ ቀጣዩ መስኮት ትሸጋገራለች። መስኮቱ የሚጀምረው በደቡብ በኩል ነው። ለዚህም ምስክሩ ፀሐይና ጨረቃ በአራተኛው መስኮት በወርኃ ሚያዚያ በመፈጠራቸው ይታወቃል። (አቡሻክር ሰዒድ ወልደ በጥሪቅ ገጽ ፯፻፸፩)
ከላይ እንዳልነው የፀሐይ መስኮት በደቡብ በኩል ሆኖ ፀሐይ ጥርና ታኅሣሥ በደቡብ በኩል ባለው በመጀመሪያው መስኮት፣ የካቲትና ኅዳር በሁለተኛው መስኮት፣ መጋቢትና ጥቅምት በሦስተኛው መስኮት፣ ሚያዚያና መስከረም በአራተኛው መስኮት፣ ግንቦትና ነሐሴ በአምስተኛው መስኮት፣ ሰኔና ሐምሌ በስድስተኛው መስኮት ትወጣና ትገባለች፡፡ ከዚህ በኋላ እንደገና ወደ ደቡብ ትመለሳለች። በዚህ አረዳድ በየካቲት ወር ፀሐይ በሁለተኛው መስኮት ትወጣለች፡፡ የየካቲት ወር ፀሐይ በሁለተኛው መስኮት የምትወጣበትና የምትገባበት ሲሆን የፀሐይ መስኮት የሚጀምረው በደቡብ ባለው መስኮት ነው። ይህም ፀሐይና ጨረቃ በአራተኛው መስኮት በወርኃ ሚያዝያ በመፈጠራቸው እንደሆነ ይታወቃል። (አቡሻክር፣ ሰዒድ ወልደ በጥሪቅ፣ ገጽ ፯፻፸፩) በመሆኑም የካቲት ወር በኢትዮጵያ ዘንድ መዓልቱ እየጨመረ ሌሊቱ እያጠረ የሚሄድ ሲሆን የመዓልቱ ርዝመት ፲፫ ሰዓት፣ የሌሊቱ ርዝመት ደግሞ ፲፩ ሰዓት ይሆናል። በክፍል በሚቆጥረው በሄኖክ አቆጣጠር ደግሞ የካቲት ወር መዓልቱ ስምንት ክፍል ሌሊቱ ፲ ክፍል ነው።
ጨረቃ ወራቱን ተከትላ በየቀኑ በስድስቱ የፀሐይ መስኮቶች የምትፈራረቅ ሲሆን በየካትት ወር በሁለተኛው መስኮት አንድ ቀን፣ በሦስተኛው መስኮት አንድ ቀን፣ በአራተኛው መስኮት አንድ ቀን፣ በአምስተኛው መስኮት አንድ ቀን፣ በስድስተኛው መስኮት ስምንት ቀን፣ በአምስተኛው መስኮት ሁለት ቀን፣ በአራተኛው መስኮት ሁለት ቀን፣ በሦስተኛው መስኮት ሁለት ቀን፣ በሁለተኛው መስኮት ሁለት ቀን በመጀመሪያው መስኮት ስምንት ቀንና ከፀሐይ ጋር ታድራለች፡፡ (መጽሐፈ አቡሻክር፣ ያልታተመ የእጅ ጽሑፍ፣ ብርሃነ አእምሮ መጽሏፈ አቡሻኽር)
በኢትዮጵያ የወቅቶች አከፋፈል መሠረት ከታኅሣሥ ፳፮-መጋቢት ፳፭ ዘመነ ሀጋይ (በጋ) ስለሚባል ይህችም ወር በበጋ ወራት ውስጥ የምትካተትና ናርኤል በሚባል ዐቢይ ኮከብ የምትመገብ ወራት እንደሆነች የአቡሻክር ልሂቃን ይናገራሉ። (ባሕረ ኀሳብ አለቃ ያሬድ ፈንታ)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን መሠረት አድርጋ የቅዱሳን በዓላት በዓመትና በወር የምታዘክር ሲሆን በየቀኑ የሚታሰቡትን የወርና የዓመት የቅዱሳንን በዓላት ስንክሳር ላይ የተጻፈ ስለሆነ እርሱን እንድትመለከቱ እየጋበዝን በዋናነት ግን በዚህ ወር በጎላና በተረዳ የካቲት ፲፮ የምትከበረውን የእመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓል እንዘክራለን፡፡ በየካቲት ፲፮ ቀን ስሟን ለሚጠራ ለድሆችና ለችግረኞች እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ከተወደደ ልጅዋ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳን የተቀበለችበት ቀን ነውና የከበረ በዓልን እናደርጋለን።
በየካቲት ወር ሁሌም የማንዘነገው ሌላው ታሪክ የአድዋ ድል ነው። የአደዋ ጦርነት በየካቲት ፳፫ ቀን ፲፰፻፹፰ ዓ.ም. በኢትዮጵያና ጣሊያን ሀገራት መካከል የተካሄደ ውጊያ ሲሆን ኢትዮጵያ በዓለም የታወቀችበትና የጥቁሮች ነጻነት የታወጀበት ድል ነው። ሰው ታሪክ ሲያውቅ መንፈሳዊም ጀግናም ይሆናል፡፡ ታሪክ የማያውቅ ሰው ግን እንኳንስ መንፈሳዊና ጀግና ሊሆን ከብዙ ሴቶች መካከል እናቱን ለይቶ በማያውቅ ልጅን ይመሰላል። ታሪክ የማያውቅ ሰው የመጣበትንም ብቻ ሳይሆን የሚሄድበትንም አያውቅም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን በየካቲት ወር የተከናወነውን የአድዋን ድል ታሪክ እያስታወሱ መርሕ ሊያደርጉትና ለትውልድም ሊያስተላልፉት ስለሚገባ በሚል ሐሳብ በመጠኑ ዘክረነዋል።
በእርግጥ እንደ መጽሐፈ ስንክሳር በሁሉም ዕለት የሚታሰቡ ቅዱሳን ቢኖሩም በመቀጠል ከእነዚህ በጣም የሚታወቁትን ብቻ እናነሣለን፡፡
፩ኛ የካቲት ሁለት የአባ ጳውሊ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡
፪ኛ የካቲት ሦስት የሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ፍልሰተ ሥጋ ነው፡፡
፫ኛ የካቲት ስድስት ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሽቶ የቀባቸው ማርያም የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው፡፡
፬ኛ የካቲት ስምንት ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከከበረ ልደቱ ከአርባ ቀኖች በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት ነው፡፡ የነቢይት ሐናም የዕረፍት በዓል ነው፡፡
፭ኛ የካቲት ዐሥር ቀን ሐዋርያው ያዕቆብ በሰማዕትነት ያረፈበት ነው፡፡
፮ኛ የካቲት ዐሥራ አምስት ቀን ከዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ነቢዩ ዘካርያስ ያረፈበት ነው፡፡
፯ኛ የካቲት ዐሥራ ስድስት ቀን የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እናት ቅድስት ኤልሳቤጥ ያረፈችበት ነው፡፡
፰ኛ የካቲት ሃያ ስድስት ቀን ዖዚያ ይባል የነበረ እውነተኛ ነቢይ ሆሴዕ ያረፈበት ነው፡፡
፱ኛ የካቲት ሃያ ሰባት ቀን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለቱ መታሰቢያ “ጥንተ ስቅለት” ነው፡፡
፲ኛ የካቲት ሃያ ዘጠኝ ቀን ለክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ በዓል “ጥንተ ልደት” መታሰቢያ ነው፡፡
፲፩ኛ የካቲት ሠላሳ ቀን መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሄሮድስ በግፍ አንገቱን ካስቆረጠው በኋላ ቅድስት ራሱ ለ ፲፭ ዓመታት ዙራ አስተምራ ያረፈችበት (የተገኘችበት) ነው:
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!