ቃና ዘገሊላ

                      ዲያቆን ዘሚካኤል ቸርነት
ጥር፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም

የቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት ታሪክ በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ብቻ ከተጻፉ ተአምራት አንዱ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት ከነበሩት ደቀ መዛሙርት አንዱ በመሆኑ በዚያ ለተደረገው ተአምር የዓይን ምስክር ነው፡፡ ከአራቱ ወንጌላውያንም ውስጥ በዚህ ሰርግ  ቤት ተገኝቶ  የነበረው  እርሱ  ብቻ ነው፡፡ እናም  ይህ  ሐዋርያ  ያዩትን  ከመናገር  ዝም ለማለት  ከማይችሉ  ሐዋርያት  አንዱ በመሆኑና እርሱም ደጋግሞ ያየውን እንነግራችኋለን ሲል የነበረ በመሆኑ የቃናውን ሰርግ ቤት ተአምር መዝግቦልናል፡፡ (ሐዋ.፬፥፳)

ቅዱስ ዮሐንስ ስለዚህ ሰርግ ቤት እንዲጽፍ የሚያስችለው ሌላ ምክንያትም አለ፡፡ “በቃና ሰርግ ነበረ” ካለ በኋላ አያይዞ “የኢየሱስ እናት በዚያ ነበረች” ብሏል፡፡ የዚህ ሰርግ ቤት ተአምር ምክንያት የነበረችውን እመቤታችንን ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ ከመስቀል ሥር በአደራ ተቀብሎ ወደ  ቤቱ ወስዷት  ነበር።  ከእርስዋም ጋር ለዐሥራ  አራት ዓመታት  ኖሮአል፡፡  በእነዚህ  ዓመታት  ውስጥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በልብዋ ትጠብቀው የነበረውን ምሥጢር ሁሉ ለዮሐንስ ገልጣ ነግራዋለች፡፡ እመቤታችን ብዙ ስትናገር አልተሰማችም።  ነገር ግን በእርስዋ ልብ ውስጥ ብዙ ምሥጢር ነበር፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ከእርስዋ ጋር በመኖሩ ጥልቅ መንፈሳዊ መጻሕፍትን  ለመጻፍ  ችሏል፡፡  መላእክት ተገልጸው ተው የማትጨርሰውን አትጀምር“ እስኪሉት  ድረስ ጥልቅ የሆነ ነገረ መለኮትን የተረዳው የምሥጢር መዝገብ የሆነች እመቤታችን ከእርሱ ጋር ስለነበረች ነው፡፡ ከእነዚህ ምሥጢራት በተጨማሪ ስለ ቃናው ሰርግ እሱ ያልሰማው ነገር ቢኖር እንኳን ከእመቤታችን አንደበት ለመስማት እና የእናትና ልጅን ንግግር አጥርቶ ለመጻፍ ከዮሐንስ ወንጌላዊ የተሻለ ሰው የለም፡፡

ሌላው ነገር የቃናውን ሰርግ በወንጌል ከወንጌልም ጥልቅ ነገረ መለኮት በተጻፈበት በዮሐንስ ወንጌል እንዲጻፍ ያደረገውስ ምንድን ነው?  የሚለው  ነው:: ወንጌላዊው ዮሐንስ  ከታሪኮች  ይልቅ  ነገረ  መለኮት ላይ  የሚያተኩር ጸሐፊ  ሆኖ  እያለ  በሌሎች  ወንጌላት ስላልተጻፈው  ስለዚህ  የሰርግ ቤት ተአምር  መጻፉ  ለምንድን ነው?  ሙሽሮቹ  ስማቸው የገነነ ስለሆነ  ነው እንዳንል  በታሪኩ ላይ ስማቸው እንኳን አልተጻፈም፡፡ ባለ ጸጎች  ናቸው እንዳንል  የጠሩትን እንግዳ እንኳን የሚሸኝ የወይን ጠጅ ያላዘጋጁ ድሆች  ነበሩ፡፡ ይህ  ጋብቻ  እንዲህ  ትኩረት  የሳበው  የምድር  የሰማይ ፈጣሪ  መድኃኔዓለም  ክርስቶስ  ከቅድስት  እናቱ እና ከደቀ መዛሙርቱ  ጋር ስለተገኘበት ነው፡፡

“በሦስተኛውም  ቀን  በገሊላ  ቃና ሰርግ  ነበረ፥  የኢየሱስም  እናት በዚያ  ነበረች፤ ኢየሱስም  ደግሞ  ደቀ  መዛሙርቱም ወደ  ሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት፦ የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው። ኢየሱስም፦ “አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?  ጊዜዬ  ገና  አልደረሰም”  አላት። እናቱም  “ለአገልጋዮቹ፦   የሚላችሁን  ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው። አይሁድም  እንደሚያደርጉት የማንጻት  ልማድ   ስድስት  የድንጋይ  ጋኖች   በዚያ  ተቀምጠው  ነበር፥   እያንዳንዳቸውም  ሁለት ወይም  ሦስት   እንስራ   ይይዙ ነበር። ኢየሱስም፦ “ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው” አላቸው። “እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው” አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው።  “አሁን ቀድታችሁ  ለአሳዳሪው  ስጡት”  አላቸው፤  ሰጡትም። አሳዳሪውም  የወይን ጠጅ  የሆነውን  ውኃ  በቀመሰ ጊዜ  ከወዴት  እንደ  መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች  ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ ፦ሰው  ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን  የወይን ጠጅ  ያቀርባል፥  ከሰከሩም  በኋላ  መናኛውን፤ አንተስ  መልካሙን  የወይን  ጠጅ  እስከ  አሁን  አቆይተሃል”  አለው። ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።” (ዮሐ.፪፥፩-፲፩)

ሦስተኛ ቀን ለእስራኤላውያንም ታሪካዊ  ትርጒም  ያለው  ቀን  ነው፡፡ እግዚአብሔር   በሲና ተራራ ለእስራኤል ሊገለጥ  ሲል “በሦስተኛው ቀን ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩ እግዚአብሔር  በሲና ተራራ ላይ ይወርዳልና  ለሦስተኛው ቀን ይዘጋጁ” ብሎ ነበር። (ዘጸ.፲፱፥፲፩)  በሐዲስ  ኪዳንም  በቃና  ዘገሊላ  የመጀመሪያ ተአምሩን  አድርጎ  ራሱን የገለጠው  በሦስተኛው  ቀን መሆኑ  አወጣጡ  ከቀድሞ ጀምሮ ለዘለዓለም የሆኑ በቅድምና የነበረው አምላክ እርሱ መሆኑን ያስረዳናል። (ሚኪ.፭)

በመጽሐፈ  ኢያሱም  እንዲሁ  ሦስተኛ  ቀን  ታሪካዊ  ክስተት  ተፈጽሞበታል፡፡  ራሳቸውን  ሰውረው  ወደ  እስራኤላውያን  የተጠጉት አሕዛብ /የገባዖን ሰዎች/ ማንነታቸው ታውቆ ከእስራኤል  ጋር ተቀላቅለው  መኖር የጀመሩት በሦስተኛው  ቀን ነበር፡፡ (ኢያ.፱፥፩-፲፯) እስራኤል  የሚያርቋቸውን አሕዛብ በሦስተኛው ቀን አቅርበው ማኖር እንደ ጀመሩ ጌታችንም በሦስተኛው ቀን አሕዛብ በሚኖሩበት የገሊላ ከተማ ተአምራቱን በማድረግ አሕዛብን ወደ እርሱ ሳባቸው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ “በሦስተኛው ቀን” በማለት የጻፈውን ዕለት የተለያዩ ሊቃውንት  በሦስት ዓይነት አተረጓጎም  ይቆጥሩታል፡፡ አንደኛው ጌታችን  ፊልጶስን  አግኝቶ  “ተከተለኝ  ካለበትና  ፊልጰስም  ጓደኛውን  ናትናኤልን  ከጠራበት  ዕለት  ሦስት  ቀን በኋላ ተአምሩን አደረገ የሚል ነው፡፡ (ዮሐ.፩፥፵፬)  ሁለተኛው  አቆጣጠር ደግሞ በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር! ያለውን እሑድ (ቁ.፴፭)፣ በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና ተከተለኝ አለው» (ቁ.፵፬) ያለውን ሰኞ ብሎ በመተርጐም ማክሰኞ  ተአምሩን  በቃና  አደረገ  የሚል  ነው፡፡ ሦስተኛው  እና የእኛ ቤተ ክርስቲያን  የበለጠ  የምታስተምረው አገባብ ደግሞ ጌታችን  በዮሐንስ  እጅ ከተጠመቀ በኋላ  ሳይውል  ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሔዶ የጾመውን አርባ  ቀንና አርባ ሌሊት  እንደ  አንድ  ቀን በመቁጠር ከዚያ  መልስ  ተአምራቱን አደረገ  የሚል  ነው፡፡

አርባ  ቀንና ሌሊት  እንደ  አንድ  ቀን እንዴት ይቆጠራል? ቢባል ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ልማድ ስለሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ማቴዎስ “ጌታችን ከግብፅ ስደት መልስ ወደ ናዝሬት መጥቶ ኖረ” ብሎ ከጻፈ በኋላ ቀጥሎ በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ።  መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ ብሎ ጽፎአል፡፡ (ማቴ.፪፥፳፫፤፫፥፩)

በሁለቱ ዓረፍተ ነገሮች መካከል የሃያ አምስት ዓመታት ልዩነት  አለ፡፡ ብዙውን እንደ አንድ መቁጠር የመጻሕፍት ልማድ ስለሆነ ግን “በዚያ ወራት” ብሎ ጻፈ፡፡ ይህ የትርጓሜ አገባብ የበለጠ ትርጒም የሚሰጥ ነው፡፡ ከማንኛውም መንፈሳዊ  አገልግሎትና   ተአምራት  በፊት  መጾምና  መጸለይ  እንደሚቀድም  ያስተማረንም  ከቃናው  ተአምር  በፊት በገዳመ ቆሮንቶስ በመቆየቱ ነው፡፡ “እመቤታችን  አስቀድማ  ነበር”  ሲል ደግሞ እመቤታችን  ጌታችን  ኢየሱስ  ክርስቶስን  በሥጋዊ  እድገቱ  እንደምትቀድመው  ነው፡፡ እንኳን  የእርሱ  እናት ትቅርና  ዮሐንስ  መጥምቁም በስድስት  ወር  ይቀድመው  ነበር፡፡  እንግዲህ  እናትን  ሳያውቁ  ልጅን  ቢጠይቁ ያስቸግራል፡፡

አስቀድማ የነበረችውን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ከመሆን በፊት አብራን የኖረችውን ድንግል ማርያምን ሳናውቅ ኢየሱስ ብንል ትርፉ ድካም ብቻ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን  “ኢየሱስ” ከማለት በፊት አስቀድመን እርሷን “አማልጅን” እንበላት፡፡ ነገረ ድኅነትን  ስናስብ በሕሊናችን  አስቀድመን እርሷን  መሳል  አለብን፤  ነገረ  ማርያም የምሥጢረ  ሥጋዌ  መቅድም (መጀመሪያ)፣ የነገረ ድኅነት መሠረት ነውና፡፡ “ጌታችን ተወለደ፤ ተሰደደ፤ አስተማረ፤ ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተነሣ፤ ዐረገ፤ ዳግም ይመጣል” ሲባል  በድንግል ማርያም ሥጋ ነው፡፡ በነገራችን ሁሉ እርሷን ማስቀደም እንዳለብን  እንረዳለን፡፡

ወይኑ  ባለቀ  ጊዜ  “ወይን የላቸውም” አለች፡፡ የወይኑን  ማለቅ  ለእመቤታችን  ማን ነገራት? ሙሽራው  ወይስ ከሠርገኞቹ  መካከል አንዱ?  ለዚህ ምንም ዓይነት  መልስ  እንደማይሰጥ ግልጽ  ነው፡፡ ቅድስት ድንግል  ማርያም ግን  እራሷ  ነበር  ያወቀችው፡፡ ቅዱስ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ ካመሰገኗት በኋላ “ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ  ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል”  ማለቷ ወደፊት ስለሚመጣው ትውልድ  ነበር የተናገረችውና፡፡ (ሉቃ. ፩፥፵፰-፵፱)

ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ በምዕራፍ ስምንት ቊጥር አንድ “ወደ ነቢይቱ ሄድኩ፤ ፀንሳም ነበር” የሚላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ነው፡፡ በ፪ኛ ነገሥት ምዕራፍ ፮ ቊጥር ስምንት ላይ በሶርያ የነበረው ንጉሥ በኢየሩሳሌም ያለውን ንጉሥ ሊወጋ (ሊገድል)  በፈለገ ጊዜ በእልፍኝ  ሆኖ የሚመክረውን ምክር  ነቢዩ ኤልሳዕ  ኢየሩሳሌም  ሆኖ  ይመለከትና  ያውቅ  እንደነበር ተገልጾአል፤  ኢየሩሳሌም  ሆኖ  በሶርያ  የሚደረገውን  እያየ  ነበር፡፡  ስለዚህም የኢየሩሳሌሙን ንጉሥ  “ከቤትህ  እንዳትወጣ ሶርያውያን ሊገድሉህ  ይፈልጋሉ”  እያለ ይመክረው ነበር፡፡

ምን ዓይነት  ጸጋ እንደሆነ አስቡት! ኢየሩሳሌም ሆኖ በሶርያ የሚደረገውን ነገር ማወቅ! ታዲያ በዘመነ ብሉይ የነበሩ ነቢያት እንዲህ የርቀቱን ነገር የሚያውቁ ከሆነ እመቤታችን  ቅድስት  ድንግል  ማርያም የዶኪማስን  የቤት  ችግር፣  የወይን ማለቅ ብታውቅ፣  ብትረዳ  ምን ይደንቅ? የመለኮት እናትም እንዴት ጸጋው ይበዛላት? እንደ እመቤታችንስ  ጸጋው  የበዛለት በዘመነ ብሉይ ማን ነበር? “ጸጋን የተመላሽ ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ” የተባለች ድንግል ማርያም አይደለችምን? እግዚአብሔር ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን፡፡ “ከአንቺ  ጋር ምን  አለኝ›”  ያላትስ   ምን  ማለቱ   ነበር?  ወግጅልኝ፤  ሂጂልኝ” ማለቱ  ሳይሆን  “ያልሽኝን  እንዳልፈጽምልሽ   ምን የሚከለክለኝ ነገር አለ” ሲል ነው፡፡ “እናትና አባትህን አክብር፤ ለእናትና ለአባትህ ታዘዝ” ያለ አምላክ እናቱን ሂጂልኝ፤  “ወግጅልኝ” አላት ሲባል አያሳፍርም? ይህማ እንዳይሆን “ለእናቱ እየታዘዘ አደገ” ወንጌል ይል የለምን፡፡ (ሉቃ.፪፥፶፩) “ጊዜዬ ገና አልደረሰም” ያለው ወይኑ ከእንስራው በደንብ ካለቀ በኋላ ውኃ ሞልተው የጌታን ተአምር እንዲታይ ለማድረግ ነው፡፡ ወይኑ በደንብ ሳያልቅ ከዚያው ላይ ቢሞላው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተአምር አይታወቅምና፤ረድኤት አሳደረበት ይባላል አንጂ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወይኑ ሁሉ ካለቀ በኋላ ግን ውኃ ተሞልቶ ወይን ሲሆን ተአምሩ ይታወቃል፤  ይገለጻል፡፡ “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያውን ተአምር በቃና አደረገ”  የሚባለው ለዚህም ነው፡፡ (ሌላም ሰፊ ምሥጢር ቢኖርም ለዚህ እትም ግን ይህን አቅርበናል፡፡) የሰርገኛው ቤት ብቻ አይደለም፤ ሁላችንም ወይን የለንም፤ የሕይወት እንሥራችን ጎደሎ ነው፡፡ ይህ እንስራ (ጋን)  የሚሞላው በእመ ብርሃን አማካኝነት ነው፡፡ እርሷ  ከሌለችበት  በፍጹም ሊሞላ አይችልም፤  በመሆኑም ለሁሉም ሰው  ለማስገንዘብ  የምንወደው  በቅድሚያ  ጸጋ የበዛበት  እመቤት  መያዝ  እንዳለብን፣  ለምን እግዚአብሔር   ከእርሷ  ጋር ነውና፡፡

መልአኩ  ቅዱስ  ገብርኤል  “እግዚአብሔር  ከአንቺ  ጋር ነውና” ብሏታል፤ ያለ እርሷ እንስራችን  አይሞላም፤ ለዘመናት  ደክመናል፤  ነገር  ግን  እንስራችን  ባዶ  ነው፡፡ “እመቤቴ ከቤቴ  ግቢ፤  ቤቴ ባዶ  ነው”  እንበላት፤ ትመጣለች፤ ያን ጊዜ ቤታችን ይሞላል፡፡ የፍቅር ወይን፣ የቸርነት  ወይን፣ የሰላም ወይን፣ የመተማመን ወይን በቤታችን  ጎድሎብናል፡፡ ስለዚህ እመቤታችን በምልጃዋ ትሙላልን፤ ፍቅሯን ታሳድርብን፤ አሜን፡፡

በቤተ  ክርስቲያናችን  ከጥንት ጀምሮ የቃናው ተአምር ትልቅ  ትኩረት  የሚሰጠው ነው፡፡ በሮም  ካታኮምብ /ግበ  ምድር/  ከተገኙ ኀምሳ ሁለት ጥንታዊያን የዋሻ ውስጥ የግድግዳ ሥዕላት ከዐሥራ ስድስት የሚበልጡት የቃና ዘገሊላን ተአምር የሚያሳዩ መሆናቸው በዚያ የጭንቅ ዘመን የነበሩ የጥንት ክርስቲያኖች ስለዚህ ሠርግ ቤት ተአምር የነበራቸውን ትኩረት የሚያሳይ ነው::

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የቃና ዘገሊላ  ተአምር የተፈጸመበት ጥንተ ዕለት የካቲት ፳፫  እንደሆነ  ያስረዳሉ፡፡‛ ሆኖም የካቲት  ፳፫ ዕለት በጾም ወቅት ስለሚውል በዓሉን በደስታ ለማክበር እንዲሁም የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር አንድ ለማድረግ ከጌታችን በዓለ ጥምቀት ማግሥት ጥር ፲፪ ዕለት ከቅዱስ ሚካኤል በዓል ጋር እንዲከበር አድርገዋል፡፡

የቃና ዘገሊላ በዓል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሀብት በሆነው በቅኔ ታሪክ ውስጥም የሚታወስ ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከቅኔ መንገዶች አንዱ  ጉባኤ  ቃና ተብሎ  ይጠራል፡፡  ታሪኩ  እንዲህ  ነው፡፡ እንደሚታወቀው  የቅኔ ጀማሪ ኢትዮጵያዊው  ቅዱስ  ያሬድ ነው፡፡ ይህን  የቅዱስ  ያሬድ  ቅኔ  መንገድ እግዚአብሔር  እንዲገልጥለት  በ፲፱፻፰ ዓም ዮሐንስ  ገብላዊ የተባለ  ሊቅ  ደብረ  ታቦር በሚባል ተራራ ሱባኤ ይገባል፡፡ በዚህም ሱባኤ ምሥጢሩ ከነቤቱ ተገልጾለት  ከቅዱስ ያሬድ አያይዞ ደርሶታል፡፡ ይህንን ቅኔውንም ለአባ ወልደ ገብርኤል አስተማረ።

አባ ወልደ ገብርኤል ለሠምረ አብ ያስተምራሉ፡፡ ሠምረ አብ ቅኔን ሲያስተምር በወቅቱ (በ፲፱፻፸ዓ.ም.) የነበረው ንጉሥ በዕደ ማርያም ነበር፡፡ ንጉሡ ቅኔውን በሰማ ጊዜ ሠምረ አብን “አንተ ከነአባትህ  ትለፈልፋለህ  እንጂ ቅኔን ከየት አገኘኸው?”  ይለዋል፡፡ መምህሩ ሠምረ አብም በትሕትና  ቃል “ይህንን ካልህስ  እንዲገለጽልን  ስለምን ሱባኤ  አንገባም?” አለው፡፡ ንጉሡም  “እሺ” ብሎ  ተያይዘው  ሱባኤ  ገቡ፡፡ እግዚአብሔርም  ነገሩ  ከእርሱ  እንደሆነ  ይታወቅ  ዘንድ  በሱባኤው  ወቅት የንጉሡን ልብ ብሩህ አደረገለትና ቅኔ ተናገረ፡፡ “ሸክላ (ሰብእናችን) ከተሰበረ በኋላ ሽኸላ ሠሪው ከርስቶስ በአዲሲቱ ጥምቀት ውኃ አጸናው፤” (ሠራው) ይህን ቅኔ  የመራበት (የተቀኘበት)  ዕለት የቃና  ዘገሊላ  ዕለት በመሆኑም ስመ ጉባኤ ቃና ተባለ፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ጌታችን ካደረጋቸው  እጅግ ብዙ ተአምራት መካከል በዓል አድርጋ  የምታከብረው የቃና ዘገሊላውን ተአምር ነው፡፡ጌታችን መጻጉዕን የፈወሰበትን፣ አልዓዛርን  ከሞት ያስነሣበትን፣ ዓይን ያበራበትን፣ በአጋንንት እስራት የተያዙትን ነጻ ያወጣበትን፣ ዕለት በክብረ በዓል ደረጃ ሳታከብር የቃናው ተአምር ከጌታችን ንዑሳን በዓላት ውስጥ ተደምሮ እንዲከበር ያደረገችበት ጥልቅ ምሥጢርን ስለያዘና ስላዘለ ነው፡፡ ይህ ሰርግ የሚደረገው  ጌታችን  ከአእላፋት  መላእክቱ  ጋር በሚመጣበት  በዕለተ  ምጽአት  ነው፡፡ ዕለተ  ምጽአት  ሙሽራዪቱ  ቅድስት  ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳን ምግባር አጊጣ  የምትታይበት፣ የጽድቅ ዘይት ይዘው መገኘት የቻሉ ልባሞች  ከቤተ  ክርስቲያን ጋር ሰርጉን የሚታደሙበት፣ እንደ ቃናው ደስታ በሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት  መላእከት በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ  በኵራት ማኅበር፥  የሁሉም  ዳኛ ወደሚሆን ወደ  እግዚአብሔር፥  ፍጹማንም ወደ ሆኑት  ወደ ጻድቃን  መንፈሳት የምንደርስበት ዕለት ነው፡፡ (ዕብ.፲፱፥፳፪)

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ የቃናን ሰርግ ከሰማያዊው ሰርግ ጋር አሰናስሎ ሲያመስግን እንዲህ ይላል፡፡ “ወደ ሰርግ በዓልዋ ዕለት ደስታን ይዘህላት ስለመጣህ ቃና ታመስግንህ! አክብረኸዋልና ሙሽራው የደፋው ዘውድ አንተን ያከብርሃል።  የሙሽራዋ አክሊልም የአንተን ድንቅ ሥራ ያደንቃል፡፡  ቤተ ክርስቲያንህን በሙሽራዋ መስለሃታልና  በቃና  መስታወትነት  ምሳሌዎች ሁሉ ትርጒማቸውን  አገኙ፡፡ የቃናዎቹ እንግዶች ደግሞ አንተ የመረጥሃቸው (ወደ  ሰማያዊው ራት) የጠራሃቸው  ናቸው::  ምጽአትህንም በሰርግ  ቤቱ ደስታ መሰልከው::”

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንደ ሙሽራ አጊጣ፣ ለበጉ ሰርግ ያለ እድፍና ያለ ነውር ውብ ሆና ተዘጋጅታ በምትቀርብበት በዚያ ሰማያዊ ሰርግ ለመገኘትና ወደ በጉ ሰርግ ራት ገብተን፣ ካጌጡ ቅዱሳን ጋር ለመቀመጥና ለመብላት የበቃን ያድርገን፡፡

ምንጭ፡- ትርጓሜ ወንጌል እና “ቃና ዘገሊላ በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ