አገልግሎቴን አከብራለሁ!

ክፍል ሁለት
ጥር ፭፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

በዘመነ ሥጋዌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርተ ወንጌልን በቃሉ አስተምሮ እንዲሁም ለሐዋርያት ቃሉን በዓለም እንዲዘሩ ‹‹ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ለፍጥረትም ሁሉ ወንጌልን ስበኩ›› ብሎ ባዘዛቸው መሠረት ወንጌል በምንኖርባት ምድር ለዘመናት ስትሰበክ ኖራለች፡፡ (ማር.፲፮፥፲፭) ጻድቃን አባቶቻችንም ለእኛ ሐዲስ ኪዳን ሰዎች ቃሉን በአደራ እንዳስረከቡንም በተመሳሳይ መልኩ ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን የእግዚአብሔርን ቃል አስተምረን በሃይማኖትና በክርስቲያናዊ ምግባር ኮትኩተን ማሳደግ ኃላፊነችን ነው፡፡

ስብከተ ወንጌል በስፋት ከሚሰጥባቸው ቀናት ክብረ በዓላት ቀደምት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴውን ተከትሎና በክብረ ታቦተ ፊት የሚሰበከው ወንጌል ለብዙ ምእመናን ተደራሽ ነው፡፡ የሕዝበ ክርስቲያኑ ስብስብ እጅጉን የሚበዛባቸው በዓላት ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት እጅግ የላቀ ሚና አላቸው፡፡ ጳጳሳት፣ ሊቀ ጳጳሳት፣ ቀሳውስት፣ ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን ሰባክያነ ወንጌልና መምህራን በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቱ በመገኘት ቅዱስ ቃሉን በተገቢው መንገድ ለሕዝብ ያስተምራሉ፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ የሠርክ ጉባኤ የተጀመረው በ፲፱፻፸፯ ዓመተ ምሕረት ነው፤ በዚያን ዘመን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታዮች አመሻሽ ላይ ቤተ ክርስቲያንን ማዘውተር ቢያንስ መሳለምን አያስታጉልም ነበር፡፡ በተለይም ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከጨረሱ ከሰዓት በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ያዘወትራሉ፤ ሁሉም በየፊናው ጸሎት አድርሶ ይሄዳል፤ በዚያን ጊዜ የመናፍቃን እንቅስቃሴ በከተማው እንዲሁም በዩኒቨርስቲዎች ላይ ተሰራጭቶም ስለነበር ተማሪዎቹ ችግር እንደገጠማቸው በታሪክ የተመዘገበ ነው፤ የከፍተኛ ደረጃና ተቋማት አስተማሪዎች መናፍቃን መሆን ደግሞ ሁኔታውን እንዳባባሰው ይታመናል፡፡

በዚህም ጊዜ ተማሪዎቹ ስለነበረባቸው ውዝግብና ጥርጣሬ ለአገልግሎት የመጡትን እንደ ቀሲስ ደጀኔ ሽፋረውን (የማኅበረ ቅዱሳን መሥራች፤ በአሁኑ ወቅት የሰሜን አሜሪካ የዴንቨር ደብረ ሰላም መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ናቸው) ያሉ ካህናትን ጥያቄዎች በመጠየቅ ቀስ በቀስም ካህናቱና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያናቱ ወጣቶቹን ሰብስበው ያስተምሩና ይመክሩ ነበር፤ ያም ስብስብ ሰፍቶ ወደ ዐውደ ምሕረት ጉባኤ አደገ፡፡ በዚህም ረገድ የማኅበረ ቅዱሳን አገልጋዮች ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ከሥር መሠረቱ ሰባኪያነ ወንጌል መምህራንን በማሠልጠን ለመንፈሳዊ ጉባኤያት ብቁ የሆኑ አገልጋዮችን በየክፍለ ሀገራቱ አሠማርቶ በዓላት ላይ የሚታደመውን ምእመንን የእግዚአብሔር ቃል ይመግባሉ፡፡ ወንጌል በመንፈሳዊ ጉባኤያት ላይ ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ የማኅበረ ቅዱሳን ትሩፋት አገልጋዮች በተለይም በበዓላትና በሰንበት ያለማቋረጥ ሙሉውን ቀን ያስተምሩ ነበር፡፡ የማኅበሩ ቀደምት አገልጋዮች እንደ መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራሁ፣ መልአከ አርያም ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና፣ ቀሲሰ እሸቱ ታደሰ፣ ሊቀ ልሣናት ቀሲስ ከፍያለሁ ጥላሁን፣ ቀሲስ ይግዛው መኮንን፣ መምህር ፍቃዱ ሳህሌ እና ሌሎችም በትሩፋት የሚያገለግሉ መምህራን ለስብከተ ወንጌልና ለመንፈሳዊ ጉባኤ መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ለምሳሌ በባሕር ዳር ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታላላቅ ጉባኤያት ይደረጉ ነበር፡፡ በእንደ አሁኑ ጊዜ ከሰርክ ሰዓት እስከ ምሽት ድረስ ሳይሆን ጥዋት ከዐራት እስከ ሰባት ሰዓት ደረስ ምእመናን እንደየአስፈላጊነቱ ወቅታዊ በሆኑ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሲያስተምሩ ከቆዩ በኋላ ከምሳ በኋላ ደግሞ ከስምንት ወይም ዘጠኝ ሰዓት ጅምሮ እስከ ዐሥራ አንድ ሰዓት ድረስ ትምህርተ ወንጌል በሰፊው ይሰጥ ነበር፡፡ እነዚህ መንፈሳዊ ጉባኤያት አብዛኛው ይሸፈኑ የነበረው በማኅበረ ቅዱሳን መምህራን ነው፡፡

በዚያን ጊዜ የነበረው ሰው ሰንበትም ሆነ በዓላት ቀናት ላይ ከጥዋቱ ጉባኤ በተጨማሪ ከሰዓት በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ለመማር ፈቃደኛ ነበር፡፡ ስለዚህም መንፈሳዊ ጉባኤው የሚካሄደው እንደ አሁኑ ጊዜ ሰርክ ላይ ብቻ አልነበርም፡፡ በተለይም ዐበይት ጉባኤያት የሚካሄድ የነበረው ሙሉ ቀን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች እና ሠራተኞች በተገኙበት ነበር፡፡ ደቡብ አካባቢም በተመሳሳይ መልኩ መንፈሳዊ ጉባኤያት ተካሂደዋል፡፡ በሐዋሳ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ዋና ግቢ ጉባኤ ማለትም ሐዋሳ ደብረ ሰላም ቅድስት ሥላሴ የተማሪው የቁጥር ብዛት እጅግ ብዙ ስለነበር የእግዚአብሔር ቃል ለናፈቀው ወጣት ወንጌልን ከማስተማርና ቤተ ክርስቲያንን ከማስተዋወቅ አንጻር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ተግዳሮት ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ መምህር ሃያ አምስት ተማሪዎች በሚማሩበት ጊዜ ትምህርተ ወንጌል እጅጉን ተናፋቂ ስለነበር ይህንን ተልእኮ ለመፈጸም የመምህራኑ አበርክቶ ታላቅ ነው፡፡ በመንፈሳዊ ጉባኤ ላይም መምህራን ከሐዋሳ እስከ ሞያሌ፣ አርባ ምንጭ፣ ጋሞ ጎፋ ዞን እየሄዱ ያገለግሉ ነበር፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ጉባኤያትን የሚያዘጋጁት ከአድባራቱ ጋር ነበር፤ ድጋፍ ሰጪዎችና የስብከተ ወንጌል ኮሚቴዎች አባላት ሆኖም የሚያገልግሉበት ጉባኤም ስለነበር የትሩፋት አገልጋዮች ተሳትፈዋል፡፡ እነዚህ አገልጋዮች በሙሉ ከደቡብ ኢትዮጵያ አስከ ሞልያ ኬንያ ጠረፍ ድንበር ድረስ የሚደርስ አገልግሎት ይሰጡም ነበር፡፡ ምክንያቱም ወንጌል ያልተዳረሰባቸው ቦታዎች ላይ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የማኅበሩ ትሩፋት መምህራን ወጥተዋል፤ ወርደዋል፤ ብዙም ለፍተዋል፡፡ በዚህም መልኩ ከከተማ እስከ ገጠር፣ በወረዳ ማእከላት ከዚህም አልፎ ተርፎ በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በውጭ ሀገራት ማለትም በአሜሪካና በአውሮፓ ባሉ ማእከላት ባለው የመዋቅር ሰንሰለት ከዋናው ማእከል እስከ ግንኙነት ጣቢያ አንድ ወይም ሁለት አባላት አስካሉበት ድረስ የወንጌል ጉባኤያት ይዘጋጃሉ፡፡

ጉባኤያትን ከማስፋፋትና ምእመናን ከማስተማር አንጻር በመምህርን የሚዘጋጁ ጉባኤያት ሰፊና ብዙ አካባቢዎችን ያዳረሱ፣ ሰዎችን ከድንቁርና ጨለማ ያወጡ፣ ፈጣሪያቸውን እንዲያውቁ፣ ወደ አምላካቸው እግዚአብሔር እንዲቀርቡ፣ ሥርዓተ ጋብቻቸውን በቅዱስ ቁርባንና በሥርዓተ ተክሊል እንዲፈጽሙ ወጣቶችን የልቦናቸውን ዓይን ያበሩ መንፈሳዊ ጉባኤያትን በማዘጋጀት የማኅበሩ አበርክቶ የላቀ ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በትሩፋት የሚያገልግሉ ብዙ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ሰባክያነ ወንጌል አሉት፤ ከዚህም በተጨማሪ በየዓመቱ ከግቢ ጉባኤያት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ በዝዋይ፣ በጅማ፣ በመላ የሀገሪቱ የካህናት ማሠልጠኛዎች ውስጥ ያስመርቃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የተወሰኑት በወንጌል አገልግሎት ተሠማርተዋል፡፡ እነዚህ አገልግሎቶች ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ሚና ያበረከቱ ስለሆኑ በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም፡፡

የዋናው ማእከል መደበኛ መምህራን እንደዛሬው የተመቻቸ መጓጓዣ ባልነበረበት እንደ ዓባይ ዘመንና ሌሎች ምቾት ያላቸው ባሶች ባልተፈበረኩበት ጊዜና አስፓልት ባልተዘረጋበት ሁለትና ሦስት ቀን መንገድ ላይ እያደሩ፣ የሚበሉትና የሚጠጡት ሲያጡና የጤንነት እክል ሲገጥማቸውም እንኳን አገልግሎቱን ሳያስታጉሉ ወንጌልን ተደራሽ አድርገዋል፡፡ እነዚህ መደበኛ መምህራን በመዲናችን አዲስ አበባም በወርኃዊና በዓመታዊ በዓላት፣ በሰርክ ጉባኤ ላይ በየአጥቢያዎቹ ተጋብዘው ያስተምራሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በዋናው ማእከል የሚካሄዱ ሐዊረ ሕይወት ጉዞዎች አሉ፤ሐዊረ ሕይወት የማኅበረ ቅዱሳን ትልቅ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መታወቂያ (ብራንድ) ነው፡፡ በአንድ ጉዙ ከስምንት እስከ ዐሥራ አምስር ሺህ ሕዝብ በማሳተፍ ብዙ ምእመናን በወንጌል እንዲረኩ የብዙዎች ጥያቄዎች በምክረ አበው መርሐ ግብር አማካኝነት እንዲመለሱ በማድረግ ታላቅ የስብከተ ወንጌል ሥራ አከናውኗል፡፡ ሌላው በዋናው ማእከል የሚከናወነው የሐዋርዊ ጉዞ ነው፡፡ ከሠላሳ ያላነሠ ሰው የሚሳተፍባቸው ናቸው፤ መደበኛ መምህራንንና ዘመርያንን በማካተት፣ በትንሹ ዐሥራ አምስት ቀን የሚፈጅ ጉዞ በማድረግ እስከ ሰባት የሚደርሱ ከተሞችን አካሎ የሚመለስ የመንፈሳዊ ጉባኤ ያደርጋል፤ በሐዋርያዊው ጉዞ ላይም መምህራኑ ስብከተ ወንጌልን ከዝማሬ ጋር ታጅበው ያቀርባሉ፡፡ እነዚህ አገልጋዮች የዓመት ፈቃዳቸውን ጭምር በመጠቀም ለወንጌል መስፋፋት ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ ከሀገር ውጭ ያለውን የማኅበረ ቅዱሳን የወንጌል አገልግሎት ወይም የመንፈሳዊ ጉባኤ አድማስ አርቀን ብንመለከተው በጣም ሰፊ ነው፡፡ በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያ፣ በአረብ እና በአውሮፓ ሀገራት ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ወንጌልን በጽሑፍ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን በቅዱስ ቃሉ እንዳስተማረን ሁሉ ሐዋርያት የእርሱን ስብከት እና ያደረገውን ተአምራት በሙሉ ለትውልድ ትውልድ ለማሸጋገር በአምላካችን ቅዱስ ፍቃድና ትእዛዝ በጽሑፍ አስተላልፈውልናል፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስም በተጨማሪ አዋልድ መጻሕፍትን ጨምሮ ቅዱሳት መጻሕፍትንም በአደራ አስረክበውናል፡፡ ስለዚህም ይህን አደራ ለመወጣት ማኅበረ ቅዱሳን ዓላማዬ ብሎ ከሚተገብራቸው መንፈሳዊ ተግባራት መካከል አድረጎ የስብከተ ወንጌልን ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡

፩. ሐመር መጽሔት

የዐውደ ምሕረት ጉባኤያት ባልተስፋፋበት ፲፱፻፹፱ ዓ.ም. አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል የእግዚአብሔርን አለመኖር አምኖ የተቀበለ ትውልድ ስለነበር ከአለማመን ወደ ማመን የተሸጋገረበት ጊዜ በመሆኑ የመናፍቃን ወጀብና የምእመናን ጥያቄ ተደማመሮ ያንገላታው ሕዝብ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣ ነበር፡፡
በዓለም ደረጃም የመጽሔት እና የጋዜጣ ኅትመትና ሥርጭት የተስፋፋበት ጊዜ በመሆኑ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ወንጌል፣ ሥርዓት፣ ዶግማና ትውፊት በኅትመት መገናኛ ብዙኃናት እንደ አንድ ማሠራጫ መንገድ በማሰብ ማኅበሩ በቀዳሚነት የሐመር መጽሔት ኅትመትን ጀመረ፡፡ ለዚህ ኅትመት መጀመር በማኅበሩ ሐሳቡና የጽሑፍ ዝግጅቱ ቢኖርም የማሳተሚያ አቅም ግን አልነበረም፡፡ መጽሔቱ ተዘጋጅቶ ለማሳተም በወቅቱ ለገጠመን የፋይናንስ ችግር ከግል ገንዘባቸው ብር ሰጥተው በማበደር ለመጀመሪያዋ የሐመር መጽሔት እትም ገበያ ላይ እንድትውል ያደረጉትን አቶ ሉልሰገድንና ባለቤታው ወ/ሮ ትበርህን ማስታወስ ተገቢ ነው፡ ይህም ወቅት መሠረታዊ የሆነውን ሃይማኖትና ቤተ ክርስቲያን ለማወቅና ለመረዳት ትምህርተ ወንጌልን ማስተማር፣ አገልግሎቱንና መንፈሳዊ ሕይወቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል የማድረግ ሥራ ባስፈለገበት ወሳኝ ጊዜ የመጀመሪያው የሐመር ኀትመት በቤተ ክህነት ሊቃውንት ጉባኤ ታይቶ በመጽደቁ ለገበያ ዋለ፡፡

ቀደምት አገልጋዮችም እነ መምህር ብርሃኑ ጎበና፣ ቀሲስ እሸቱ ታደሰ ሙኃዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት፣ ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ፣ ግርማ ወለድ ሩፋኤል እንዲሁም መልእከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራውና ሌሎችም የተካፈሉበት የመጽሔቱ ዝግጅት በሺዎች የሚቆጠሩ አንባብያንን በወንጌል ለማነጽ የቻለ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜም ከትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በተጓዳኝ ተወዳጅ የሆኑ ዐምዶችን እንደ ‹እናስተዋቃችሁ፣ ዓምደ ወራዙት፣ መንገደኞቹ፣ እንደሁም ኪነ ጥበብ› ይዞ በመምጣቱ የበርካቶች አስተያየትና ጥያቄ ወደ ማኅበሩ ኅትመት ዝጅግት ክፍል ይጎርፍ ነበር፡፡

በተሐድሶና በመናፍቃን ቅሠጣ ይሠቃይ የነበረው የዚያን ጊዜው ምእመናን በእምነቱና በሃይማኖቱ እጅጉን ይፈተን ስለነበር ለነበራቸው ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ በመሻት ወደ ዝግጅት ክፍሉ በአካል በመምጣትም ሆነ ስልክ በመደወል እንዲሁም ደብዳቤ በመጻፍ በቂ ትምህርት ያገኙ ነበር፡፡ሐመር መጽሔት የወቅቱን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ እና በዐምዶቹ ውስጥ በማካተት ለአንባብያኑ ተደራሽ ያደረግ ነበር፡፡አንድ ሰው ክርስቲያናዊ ሕይወቱን በምን መልኩ መምራት እንዳለበት፣ማኅበራዊ ሕይወቱ መንፈሳዊነቱን ጠብቆ እንዴት ሊሄድ እንደሚችል ለምእመናን ለማስተማርና ለማሳወቅ መርዳት የሚችልበትን መንገድም ቀይሶ የተነሣ መጽሔት በመሆኑ እጅግ አስፈላጊ ሆነ፡፡ መጽሔቱም በአግባቡ ወቅቱን ጠብቆ በየሁለት ወሩ መታተም ቀጠለ፡፡በዚህም ሂደት ከተጓዘ በኋላ በአሁኑ ጊዜ መጽሔቱ በየወሩ ይታተማል፡፡

፪. ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ

በማኅበሩ የምሥረታ ታሪክ አንድ ሌላ የስብከተ ወንጌል መንገድ ተዘረጋ፤ የ፲፱፻፹፭ ዓ.ም. የመጀመሪያው የስምዐ ጽድቅ ኅትመት ለምእመኑ ደረሰ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ እና ዙሪያዋ በሚያጋጥሙ ችግሮችና ፈተናዎች፣ መልካም ተግባራትና እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ልማት ለምእመኑ ለማሳወቅ እንደሚያስፈልግ በማመን በዘገባ መልክ፣ ማኅበራዊ ጉዳዮች ተኮር የሆኑ ጽሑፎችና በማዘጋጀት እንዲሁም በአገልግሎታቸውና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው አርአያ የሆኑ የቤተ ክርስቲያንና የሃይማኖት አባቶችን በእንግዳነት በማስተናገድ መረጃ መስጠት ላይ ያተኮረ ወርኃዊ ጋዜጣም ማሳተሙን በቋሚነት ያዘ፡፡

ከዐምዶቹ መካከልም ‹‹ዜና፣ መልእክተ ስምዐ ጽድቅ፣ ድብዳቤቆቻችሁ፣ ኅብረ ነገር፣ ክርስቲያናዊ ሕይወት፣ እርስዎስ ምን ይላሉ?፣ ሕይወትን የሚፈቅድስ ሰው ማን ነው?፣ የአብርሃም ቤት እንግዳ፣ ምሥጢሬን ላካፍላችሁ›› የተሰኙት ይገኙበታል፡፡ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በተለይም ስብከተ ወንጌልን ከማሠራጨት እንዲሁም አስተዳደራዊ ችግሮችን ከመፍታትና ክፍተቶችን ከመሙላት አንጻር ሰፊ አበርክቶ አለው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም የጋዜጣው ተፈላጊነት ሲጨምር በየሁለት ሳምንት የሚታተም ሆነ፡፡
በሃይማኖት ፍቅርና ጽናት እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል በቁጭት ተነሣሽነት የነበረው የዚያን ጊዜው አገልጋይ የማኅበሩ ትልቅ ኃይል ነበር፡፡ የወቅቱን ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ችግሮች በመቋቋም የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝቡ አስተምረዋል፡፡ በቂ አገልጋይና መሣሪያዎች ባልነበሩበት እንዲሁም የገንዝብ አቅም አጥረት በነበረበት ጊዜ እንኳን የአንባብያንን ፍላጎት ላለማስተጓጎል በከፍተኛ ጥረትና አገልግሎት ሠርተዋል፡፡

፫. መጻሕፍት

ቅዱሳት መጻሕፍት መንፈሳዊ ዕውቀትን ለማጎልመስ ከሚረዱን ንዋያተ ቅዱሳት ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ የትምህርተ ሃይማኖት እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ሥርዓትና ትውፊት፣ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮን ያካተቱ መጻሕፍት ለመንፈሳዊ ሕይወታችንና ለአገልግሎታችን የሚያስፈልጉ በመሆናቸው እንደ የአስፈላጊነታቻው በታተሙበት ዓመታት መሠረት ሸምተን መገልገል ያሻል፡፡ይህንን እውነታ በመረዳት ማኅበሩ በ፲፱፻፹ ዓ.ም መጨረሻዎቹ አካባቢ የቅዱሳት መጻሕፍት መሸጫ መደብር ከፍቶ ስብከተ ወንጌልን ከማስፋፋት ባሻገር ከሚያገኘው ገቢ የማኅበሩን አገልግሎት እያገዘ ይገኛል፡፡ በተለያዩ ዘመናት በበቁ መምህራንን የተዘጋጁትን ቅዱሳት መጻሕፈት በተመጣጣኝ ዋጋ ለአንባቢያን ያቀርባል፡፡

በተለይም ምእመናን ቅዱሳት መጻሕፍትን ሸምተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ማኅበሩ በልማት ተቋማት አስተዳደር ሥር የንዋያተ ቅዱሳት መሸጫ መደብር በመክፈት ከቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓትና ትውፊት ጋር የማይጋጩ ጠቃሚና ማሳያ የሆኑ ምርቶችና አገልግሎቶችን በስፋት እና በተሻለ ጥራት እያመረተ ያቀርባል፡፡ በዚህም ለምእመኑ ስብከተ ወንጌልን ከማሠራጨቱም ባሻገር ከገቢው በሚገኝ ገቢ የማኅበሩን አገልግሎት እንዲረዱም ያደርጋል፡፡

ማኅበሩ ካሳተማቸው መጻሕፍት መካከልም የምእመናንን መንፈሳዊ ሕይወትና ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የሚረዱና የሚያጠናክሩ የጸሎት መጻሕፍትን ማለትም የውዳሴ ማርያም፣መዝሙረ ዳዊት፣ እና የእመቤታችን ምሥጋና አርጋኖን፣ (በአባ እንየው ውቤ) ስለ በዓላት አከባበር (በመምህር ብርሃኑ አድማስ)፣ ፍኖተ ቅዱሳን (ያረጋል አበጋዝ) የኢትዮጵያን ቅዱሳን አባቶች (መምህር ተመስገን ዘገየ) እንዲሁም ሌሎች መጻሕፍት ተጠቃሾ ናቸው፡፡

፬. መጽሔተ ተልእኮ ዘማኅበረ ቅዱሳን

ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎቱን ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ አገልግለቱን ለማስተዋወቅ የብዙ ዓመት ምኞቱ ስለነበር በ፲፱፻፺፯ ዓ.ም. እንደ ድልድይ የተጠቀመባትን መጽሔት አሳተመ፡፡ ስያሜዋንም ‹‹መጽሔተ ተልእኮ ዘማኅበረ ቅዱሳን›› በማለት በማኅበሩ ጽሕፈት ቤት፣ በንዑሳን ማእከላት፣ በወረዳ ማእከላት እና ግቢ ጉባኤያት የተከናወኑ አገልግሎቶቹን የሚያስተዋውቁ ዓምዶችን አካቶ በዓመት ሁለት ጊዜ አሳትሞ ማሰራጨት ጀመረ፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ግን አንድ ችግር ከፊት ለፊት ተጋረጠበት፡፡ መጽሔቱ በነጻ የሚሠራጭ እንደመሆኑ ለማኅበሩ ዋና ማእከላት፣ ለግቢ ጉባኤያት እንዲሁም ወረዳ ማእከላት፣ለቤተ ክህነትና ለባለ ድርሻ አካላት፣ለተለያዩ ተቋማት እና አካለትም ሆነ ለምእመኑ የሚደርሰው ከ ፭፲፻ (አመስት ሺህ) ያልበለጠ ቅጂ በቂ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ የገቢ ምንጫችን አነስተኛ መሆንና ማስታወቂያም ስላልተሠራለት ነበር፡፡ አንባብያኑ የሚደርሻቸው ቅጂ በቂ እንዳልነበር በየጊዜው ይገልጹ ነበር፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ግን ማኅበሩ በመጽሔቱ የአንባብያንን አስተያየት ጥያቄዎች ለማካተት ይረዳ ዘንድ ‹‹ደብዳቤዎቻችሁ›› በሚል ዓምድ በመክፈት ክፍተቱን ለመሙላት ጥሯል፡፡ የመጽሔቱ አገልግሎት ተደራሽነት እየሰፋ ሲሄድም በሕዝብ ግንኙነትና ትብብር አገልግሎት ማስተባበሪያ ስር ሆኖ በዓመት ሦስት ጊዜ በየዐራት ወራት ልዩነት መታተምና መሠራጨቱን ቀጠለ፡፡

ይቆየን!