ምድር እስከ መቼ ታለቅሳለች?

ክፍል ሁለት
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ታኅሣሥ ፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ተወዳጆች እንደምን ሰነበታችሁ? የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን፤ አሜን! ባለፈው ሳምንት “ምድር እስከ መቼ ታለቅሳለች?” በሚል ርእስ አጭር ጽሑፍ አድርሰናችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ከዚያው የቀጠለ ክፍል ሁለትን አቅርበንላችኋል፤ መልካም ንባብ!

ሰዎች በምድር ላይ ሲኖሩ ምድርን እንዲንከባከቧት እና በፍቅር በሰላም ወጥተው፣ ወርደው ልብሳቸውም፣ ጉርሳቸውም ሆና እንዲኖሩባት፣ ከዚህ ዓለም በሥጋ ሲለዩም አጽማቸው እንዲያርፍባት የተፈጠረች መሆኑን ነገር ግን በርሷ ላይ እየኖሩ ግፈኞች በመሆናቸው እግዚአብሔርን የሚበድሉ የንጹሑን ሰው ደም በከንቱ የሚያፈሱ፣ ለድሃው፣ ለጾም አዳሪው ለምስኪኑ የማይራሩ ጨካኞችና ክፉዎች እየሆኑ በመምጣታቸው ምድር አብዝታ እንደምታለቅስ፣ እያለቀሰች እንደሆነ፣ እስከ መቼስ እያለቀሰች እንደምትኖር ጥያቄ ሆኖበት ነቢዩ ኤርምያስ ይህንን ጥያቄ ማንሣቱን እንገነዘባለን፡፡

ዛሬም ምድር ሰው አምርራ እያለቀሰች ነው፤ እንባዋን ጨርሳ ደም እያነባች ነው፡፡ ከሰው ልጆች ክፋት የተነሣ ብዙዎች እንደ አቤል በወንድሞቻቸው ዛሬም ተገድለዋል፤ በየዕለቱም ይገደላሉ፡፡ ዛሬም ብዙዎች እንደ አዳም ልጆቻቸው ሞተውባቸው አብዝተው ያለቅሳሉ፤ ዛሬም ብዙዎች እንደ ሔዋን የወለደ አንጀታቸው በኀዘን ተኮማትሯል፤ ዛሬም ምድር እንደ አቤል በግፍ የተገደሉ ደም እየጠጣች ነው፤ ዛሬም ባለ መሥዋዕቱ አቤል በወንድሙ ይገደላል፤ ዛሬም ባለ ማዕጠንቱ ዘካርያስ በቤተ መቅደስ ደሙ በከንቱ ፈስሷል፤ ዛሬም ብዙዎች እንደ ዮሴፍ በወንድሞቻቸው ለባዕድ ይሸጣሉ፤ ዛሬም  ክርስቶስን ደቀ መዛሙርቱ በ፴ ብር ደጋግመው ይሸጡታል፡፡

እነዚያ የእግዚአብሔር ዓይኖች ካህናት፣ እነዚያ በደሙ አጥቦ ያነጻቸው፣ በዋጋ የገዛቸው፣ አካሉ ያደረጋቸው ምእመናን ዛሬም በግፍ በገፍ ይሞታሉ፤ ይገደላሉና፤ ደማቸውንም ምድር መሸከም አልተቻላትምና ግፍ በምድር ላይ ሞልቶ ይፈሳል፡፡ ሰዎች ከግፍ ላይ ግፍን እየጨመሩ የንጹሑን ሰው ደም ከማፍሰስ አልፈው በምድር ያለችን የእግዚአብሔርን ማደሪያ አርክሰዋልና፤ “በዓላቶቹንም ከምድር እንሻር” ብለው ተማምለዋልና ግፍን መቋቋም ተስኗት ምድር ታለቅሳለች፡፡ (መዝ.፸፫፥፯-፰)

ዛሬስ ምድር ለምን ታለቅሳለች?  ‹‹ድሆችን ከምድር ላይ፣ ችግረኞችንም ከሰው መካከል ያጠፋና ይጨርስ ዘንድ ጥርሶቹ ሰይፍ መንጋጋዎቹም ካራ የሆኑ ትውልድ ተፈጥሯልና›› ምድር ታለቅሳለች፡፡ (ምሳ. ተግሣ.  ፮፥፲፬) ይህ ትንቢታዊ ቃል ሁሉ ዛሬ በኛ ላይ የየዕለት ተግባር ሆኗል፡፡ ዛሬ ክፋት አይሏል፤ ወንድም በወንድሙ ላይ በህፉ ሕሊና ተነሥቶበታል፤ ካህኑን በመቅደሱ መናኙን በበዓቱ፣ ምእመኑን በጎጆው በእርሻው ላይ በከንቱ ደማቸውን የሚያፈሱ፣ ጥርሳቸው ሰይፍ መንጋጋቸው ካራ የሆኑ በዝተዋል፡፡ በድሆችና በችግረኞች ላይ የሚጨክኑ ግፈኞችን ምድር መሸከም ከብዷታል፤ ደማቸው አስጨንቋታል፤ አስከሬናቸው ሸቷታል፤ በዚህም መተንፈስ ተስኗት እያቃተተች እንባዋ ደርቆ ደም እያነባች አሁንም ታለቅሳለች፡፡

ዛሬ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ምሕረቱን ነፍጎናል፤ ዛሬ አምላካችን በንጹሐን ደም ምክንያት እንደ ቃየል እንድንቅበዘበዝ ፈርዶብናል፤ ዛሬ የችግረኞችና የምስኪኖች፣ የቅኖችና የሰማዕታቱ ደማቸው ይካሰሳልና አምላካቸው ምድርን እየተበቀላት ነው፡፡ ምድርም ከቁጣው የተነሣ ተቃጥላለች፤ ሕዝቡም እሳት እንደሚበላው እንጨት ሆኗል፤ ሰውም ለወንድሙ አልራራምና፡፡ ዛሬ በመዓቱ እየተጎበኘን ነው፤ዛሬ ምድር እንደ ሰካራም ሰው እየተንገዳገደች ነው፤ እንደ ዳስም እየተወዛወዘች ነው፤ መተላለፏም ከብዷታል፡፡ ምክንያቱም የቅዱሳኑን፣ የካህናቱን፣ የመናንያኑን፣ የሕፃነቱን፣ የአዛውንቱን፣ ደም ጠጥታ ሰክራለችና፡፡ (ኢሳ.፱፥፲፱፣፲፫፥፲፫፣፳፬፥፳)

ዛሬም ምድር ታለቅሳለች፡፡ እነዚህ ደማቸው በወንድሞቻቸው በከንቱ የፈሰሰና በግፍ የተገደሉ ሁሉ ነፍሳቸው ዘወትር ወደላይ ትከሳለችና፡፡ ነቢዩ ሄኖክ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን እንዲህ ጠይቆት መልሶለታል፤ ‹‹ቃሉ እስከ ሰማይ ድረስ የሚደርስ የሚከስ ይህ ነፍስ የማን ነው ነፍስ? ብየ ጠየቅሁት፡፡ ይህ ነፍስ ወንድሙ ቃየል በግፍ ከገደለው ሰው ከአቤል የወጣ ነፍስ ነው፡፡ ልጁ  ከዚህ ዓለም እስኪጠፋ የልጅ ልጁም ከሰው ልጅ ተለይቶ እስኪጠፋ ቃየልን ይከሳል ብሎ መለሰልኝ፡፡›› (ሄኖ ፮፥፳፯-፳፰)

እውነት ነው! ደም በከንቱ ፈስሶ አይቀርም፡፡ የንጹሐን ደም ዋጋ ያስከፍላል፤ ልጅን የልጅ ልጅን ያጠፋል፤ ከርስት ከጉልት ይነቅላል፤ እሳትና ዲን ያዘንማል፤ ምድርንም ያቃጥላል፡፡ እነዚህ ሁሉ ዛሬ እንደዘበት የሚገደሉ ነፍሳት ሁሉ ክሳቸው አይቋረጥም፤ ቃላቸውም እስከ ሰማየ ሰማያት ያስተጋባል፤ የገዳዮች ልጆች ከዚህ ምድር እስኪጠፉ፣ የልጅ ልጆቻቸውም ከሰው ልጅ ተለይቶ እስኪጠፋ ትውልዳቸውም እስኪደመሰስ ነፍሳት ይካሰሳሉ፤ የነፍሳት ጌታም እውነተኛ ዳኛ ነውና፤ ፍትሕ ርትዕ አያጎድልምና፤ ፍርዱን በምድርና በውስጧ ባለን በሁላችን ላይ ያመጣል፡፡ ሰማያትን ይለጉማል፤ ምድርን ያናውጣታል፤ ጠለ ምሕረትን እክለ በረከትን እንዳታስገኝ ፣ የመዓት ነፋሳት እንዲነፍሱና መቅሠፍት እንዲሆኑ፣ ዝናማት በረዶ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ልንመለስ አልወደድንምና፡፡

ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ እንዲሁ ነፍሳት በሰማይ በልዑል መንበር ምድርንና በምድር ያሉትን ሁሉ ሲከሱ ተመልክቷል፡፡ ‹‹ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያው በታች አየሁ፡፡ በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ›› ይለናል፡፡ (ራእ ፮፥፱)

ምድር ለምን እንደምታለቅስ በደንብ እንደተረዳን እናስባለን፡፡ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ፈራጅና ዳኛ አምላካችን ደማቸው በግፍ ስለ ፈሰሰ ቅዱሳን ምድርንና በምድር ያለነውን ሁሉ እየተበቀለን፣ እየፈረደብን፣ እየቀጣን መሆኑ የታመነ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ! እስከ መቼ በእኛ ኃጢአት ምድር ታልቅስ? እስከ መቼስ በግፍ እንቀጥላለን? እስከ መቼስ የንጹሐን ደም በከንቱ ይፈሳል? እስከ መቼስ የእነዚህ ሁሉ ቅዱሳንና ንጹሐን ነፍስ ምድርንና በምድር ያለን ሁላችንን ሲከሱ ይኖራሉ? ምድርስ እስከመቸ ታለቅሳለች? እነሆ የማስተዋል ጊዜ አሁን ነው፡፡

የመመለስ ጊዜ አሁን ነው፡፡ የመጸጸት ጊዜ አሁን ነው፡፡ እንመለስ፤ እንጸጸት፤ ስለ በደላችን አምርረን እናልቅስ፤ ንስሓ እንግባ፤ እጃችንን እንታጠብ፤ ምድርም ከደም ትጽዳ፤ በደም ፈንታ ጠልና ዝናም ይፍሰስባት፤ በሞት ፈንታ ሕይወት ይብቀልባት፤ እሺ እንበል፡፡ ያኔ ምድር እሺ ትላለች፤ የማያልቅ ብዕሏን በረከቷንም እንበላለን፡፡ የደረቀው የምድረ በዳውም ሳር ይለምልም፤ በዝማሬያቸው የሚያነቁን፣ በውበታቸው የሚያስደንቁን አዕዋፋትና እንስሳት  አይለቁ፤ ሕፃናት አይሙቱ፤ አንመለስ!

እሺ ማለት ብንችል ግን በገጸ ምድር በከርሠ ምድር ያለውን በረከቷን ልትሰጠን ምድር እሺ ትላለች፡፡ እምቢ ብንል ግን ሰይፍ እንደሚበላን ተነግሮናል፡፡ አምላካችን  ይህንን ይናገራል፤ ‹‹እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉ ግን ብታምጹም ሰይፍ ይበላችኋል፡፡›› (ኢሳ.፩፥፲፱)  ይህን የተናገረው እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህ ቃል ከአምላካችን አንደበት የወጣና የታመነ ቃል ነውና እሺ ብለን እንመለስ!

እሺ በጎ ማለትን ያድለን፤ አሜን!