አገልግሎቴን አከብራለሁ!

ታኅሣሥ  ፬፳፻፲  .

በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ “አገልግሎት” የሚለው ቃል በተለያየ መልኩ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ሰው በግሉ፣ ከቤተ ሰቡ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር ከሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ “አገልግሎቴ” ብሎ የሚያስባቸው ምግባሮች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ለዚህም ዕውቀት ይኑረው አይኑረው ለማወቅ ቢያዳግትም ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ግን አገልግሎትን ማወቅ፣ መረዳትና መተግበር እንዲችል ግንዛቤ መፍጠር ተገቢ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ መጣ” በማለት በቅዱስ ወንጌል እንደ ነገረን ክርስቶስን የምንመስልበት፣ እርሱን ወደ መምሰል የምናድግበት፣ ነፍሳችንን ለእርሱ የምንሰጥበት የሕይወት መንገድ ነው። (ማቴ. ፳፥፳፰) ስለ ብዙዎቹ በሥጋም፣ በነፍስም፣ በመንፈስም መዛል ራስን ቤዛ አድርጎ በመስጠት የሰዎችን መንፈሳዊ ብስለት፣ ሥጋዊ ጥንካሬ እንዲያገኙ እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኝበትና ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት ሕይወት ነው። በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የምናገለግለው ሌሎችን ሰዎች ነው። ለሊሎች መኖር ሌሎችን ማገልገል ደግሞ ክርስቶስን መምሰል ነው።

ከምንም በላይ አስቀድሞ አገልግሎት ለአምላካችን እግዚአብሔር የሚፈጸም ነው፤ ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ሲፈጥረው በምስጋናና በውዳሴ ከመላእክት ጋር አንድ ሆነው ስሙን እንዲቀድሱ ክብሩን እንዲወርሱ ነው፡፡ ስለዚህም ሕገ እግዚአብሔርን እየጠበቅን፣ ሥርዓቱን እየፈጸምንና በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ለራስም ሆነ ለሌሎች የምናከናውነው በጎ ምግባር አገልግሎት እንለዋለን፡፡ ከጸሎት ጀምሮ የምንጾመው ጾም፣ የምንሰግደው ስግደት፣ የምንመጸውተው ምጽዋትና ለቤተ ክርስቲያን የምናቀርበው መባ ሁሉ ለፈጣሪያችን የሚቀርብ ነውና አገልግሎት ነው፡፡

በመንፈሳዊ ሕይወታችን በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት በጎውን አስበን ልንተገብር የምንችልው ስለ እግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ማወቅና ተግባራዊ ክርስትናን መረዳት ስንችል ነው፡፡ በመሆኑም ከሁሉም ነገር በፊት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ጠንቅቆ ማወቅ ይገባል፡፡ የፈጣሪያችንን ቅዱስ ፈቃድና ትእዛዝ ለመፈጸም የሚረዳንን አገልግሎታችንን ልናውቅና ልናከብርም ይገባናል፡፡

 

ለአገልግሎት የሚሰጥ ክብር

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ “ለእናንተም ለአሕዛብ እናገራለሁ። እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ በሆንሁ መጠን ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ አገልግሎቴን አከብራለሁ” በማለት እንደተናገረው በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትና ተወዳጅነት ያለውን አገልግሎት እናከብር ዘንድ አለን፡፡ (ሮሜ ፲፩፥፲፫)

“አገልግሎቴን አከብራለሁ” ስንልም አገልግሎት የተሰጠን ሹመት ስለሆነ ሹመትን አለማክበር ደግሞ ከክብር ያወርዳል፤ ቅጣት ያመጣል፤ ከንጉሡ ማዕድና ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት የሚለይ ስለሆነ አገልግሎትን ማክበር መንፈሳዊ ግዴታ ነው።  የቂስ ልጅ የሚሆን ሳኦል ምንም እንኳን ሹመትን ወድዶ፣ ፈልጎ የተሾመ ባይሆንም የጠፉትን የአባቶቹን አህዮች ለመፈለግ እንደሄደ በእግዚአብሔር ፈቃድ በነቢዩ ሳሙኤል ተቀብቶ ቢነግሥም ከቅጣት እንዳልዳነ መጽሐፍ ቅዱስ በ፩ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ ፱ ይነግረናል።

የቂስ ልጅ ሳኦል እግዚአብሔር በትልቅ ሕዝብ ላይ ሹሞት ሳለ ሹመቱን በአግባቡ ባለ መጠቀሙ እግዚአብሔር ናቀው፤ አቃለለው፤ መንግሥቱን አሳልፎ ሰጠበት። ዛሬም እግዚአብሔር እኔና እናንተን መርጦ በራሳችን ላይ እንዲሁም በሌሎች ሰዎች ላይ እንደ እየ አቅማችን መጠን ሹሞናል። ለዚህ ከመረጠን ደግሞ ሹመትን አክብሮ መታዘዝና ማገልገል የሁላችን ግዴታ ነው።

አገልግሎት ክርስቶስ ለእርሱ ላለን ፍቅር ማረጋገጫ አድርጎ ያቀረበልን ነው። ቅዱስ ጴጥሮስን ትወደኛለህ? በማለት ሦስት ጊዜ በመጠየቅ “ከወደድከኝ በጎቼን ጠብቅ” እንዳለው ሁሉ እኛም በአገልግሎት አባግዕ የተባሉ ምእመናንን ራሳችንን ጨምሮ በመጠበቅ (ጠብቆም ላልቶም ይነበብ) የተሰጠንን ኃላፊነት ልንወጣ ይገባናል። (ዮሐ.፳፩፥፲፯)

የማያነግሡት ንጉሥ, የማያከብሩት ክቡር, ማንም የማያበድረው ባለ ጸጋ ሲሆን አገልግሎታችንን ባናከብር ለእግዚአብሔር የሚቀርበት ኖሮ ሳይሆን  እንድናገለግል የፈቀደልን፣ ኃይሉን፣ ጥበቡን፣ ማስተዋሉን የሰጠን፣ አበው በእራት ላይ ዳረጎት እንዲሉ በጸጋ ላይ ጸጋ በክብር ላይ ክብር የሚጨምርልን ከፍጹም ፍቅሩ የተነሣ ነው።

ይቆየን!