‹‹ሽማግሌዎች ከአደባባይ፥ ጎልማሳዎች ከበገናቸው ተሻሩ›› (ሰቆ.ኤር.፭፥፲፬)
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ኅዳር ፳፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
መከራ በሰው ልጆች ዘመን ሁሉ አብሮ የኖረ የሰው ልጆች ሕይወት አንድ አካል ነው፡፡ ሰዎች ሰው ሠራሽም ሆነ ተፈጥሮአዊም በሆኑ ምክንያቶች ሕይወታቸውን የሚያመሰቃቅል፣ ሰውነታቸውን የሚያጎሳቁል፣ ሰላማቸውን የሚነፍግ ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡
ረኃብ፣ ስደት፣ መፈናቀል፣ በባዕድ ሀገር በግዞት መያዝ በባርነት መወሰድ፣ አካልን፣ ሕይወትን፣ ቤተሰብን፣ ሀብትን፣ ንብረትን ማጣት ወዘተ… ብዙ ብዙ ፈተና የመጋፈጥ ዕጣ ፈንታ በብዙዎች ላይ በየዘመኑ እንዳጋጠመ መጽሐፍ ቅዱስ አስረጅ ነው፡፡
በርካታ የነቢያት መጻሕፍትን ስናነብ የምንመለከተው ወይም የምንረዳው እንዴት ከዘመናችን ጋር የሚመሳሰል ዘመን እና እኛን የገጠመንን መከራ ገጥሟቸው እንደ ነበር ነው፡፡ በርግጥ በነቢያት ዘመን የተነገረው ሁሉ በነርሱ ዘመን የደረሰ የተፈጸመ ነው ማለት አይደለም፡፡ ነቢይ ማለት ‹‹አፈ እግዚአብሔር፣ ኃላፍያትን ፣መጻእያትን የሚናገር›› ማለት ስለሆነ ከእነርሱም ዘመን ቀድሞ ከእነርሱም ዘመን ዘግይቶ የሚመጣውን ነገር ሁሉ በትንቢት አይተው ይናገራሉና፡፡
ሆኖም ግን አብዛኛውን ነገር ስንመረምር ብዙዎቹ እንዲህ እንደኛ ዘመን መከራ የበዛበት፣ ሰቆቃ በሰው ልጆች ላይ የተስፋፋበት፣ ሕዝብ እንጀራውን በእንባው አርሶ የበላበት፣ በሥጋም በመንፈስም የተፈተነበት ጊዜ መሆኑን እንረዳለን፡፡
ነቢዩ ኤርምያስ የተናገረው ‹‹ሽማግሌዎች ከአደባባይ፥ ጎልማሳዎች ከበገናቸው ተሻሩ›› የሚለው ቃልና እንደ ርእሰ ጉዳይ አድርገን የተነሣንበት ጥቅስ ግን እጅግ የእኛን አሁናዊ ሁኔታ ገልጦ የሚያሳይ ነው፡፡ (ሰቆ.ኤር.፭፥፲፬) ሽማግሌዎቻችን ክብር ሞገስ እንዳጡ፣ ለፍርድም እንደማይቀመጡ፣ ማንንም እንደማይዳኙ ሰላምና ፍትሕ እንደማያሰፍኑ፣ ክብርና ሞገስ፣ መታፈርና መከበር ሁሉ ከእነርሱ እንደተወሰደ፣ የተጣሉትን ሊያስታርቁ፣ የተቀማን ሊያስመልሱ፣ የተበደለን ሊያስክሱ፣ ለምስኪኑ ሊፈርዱለት ለዓመፀኛው ሊፈርዱበት፣ ለድሃ አደጉ ለእጓለ ማውታው ሊራሩ፣ ክፉዎችን ሊገሥጹ፣ ፍትሕ ርትዕ ሊያሰፍኑ በአደባባይ በሸንጎ አይቀመጡም፤ ግፍን አልተጸየፉምና፤ ለሽበታቸው አልተገሩም፤ ለክብራቸው አላደሩም፤ ከተበደለው ጎን አልቆሙም፤ ሰሚ ጆሮም አላገኙም፤ ለዚያ እንደሚገባ አልሆኑምና፡፡
ጎልማሶችም በበገናቸው ሊዘምሩ፣ በደስታ ሐሴት አድርገው ሊያመሰግኑ፣ እንደ ልጅነታቸው ሊቦርቁ፣ ሊፈነድቁ፣ እንደ ጉልምስናቸው ሊደምቁ እንደማይችሉ፣ ይልቁንስ ልምላሜያቸው ጠውልጎ፣ ሰውነታቸው ጎስቁሎ፣ ተስፋቸው ተመናምኖ፣ ሳቃቸው ልቅሶ፣ ዘፈናቸው እንጉርጉሮ ሆኖባቸው ተመልክቷል፤ ይህ በዚህ ዘመን በየቦታው ይታያል፡፡ ‹‹ሽማግሌዎች ከአደባባይ ጎልማሶች ከበገናቸው ተሻሩ፤ የልባችን ደስታ ቀርቷል፤ ዘፈናችን ወደ ለቅሶ ተለውጧል፤ አክሊል ከራሳችን ወድቋል ኃጢአት ሠርተናልና ወዮልን›› እንዳለ ነቢዩ ክፉ ቀን ላይ ነንና፡፡ (ሰቆ.ኤር.፭፥፲፭)
የክፉ ቀን ክፋቱ ካህን በክህነቱ፣ ሽማግሌ በሽበቱ እንዳይከበር ማድረጉ ነው፡፡ የክፉ ቀን ክፋቱ ዐዋቂዎች እንዳላዋቂ የሚቆጠሩበት አላዋቂዎች የሚደነቁበት መሆኑ ነው፡፡ የክፉ ቀን ክፋቱ የልጆች ተወዳጀነት፣ የዐዋቂዎች ዕውቀት፣ የታላቆች መከበር፣ መፈራት፣ የሀገር ፍቅር፣የዘውድ ክብር፣ ከብዙዎች ልብ ሩቅ እንዲሆን ማድረጉ ነው፡፡ የክፉ ቀን ክፋቱ የተከበረውን ያዋርዳል፤ ተቀደሰውን ያረክሳል፤ ሰነፎች ባለሟል ይሆናሉ፤ ብርቱዎች ይናቃሉ፡፡ የክፉ ቀን ክፋቱ ተገልጋዩን አገልጋይ፣ አገልጋዩን ተገልጋይ፣ ጻድቁን ኃጥእ፣ ኃጥኡን ጻድቅ ማሰኘቱ ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ መከራ በሀገር፣ በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በሕዝብ ላይ ይመጣል፤ ጨካኞች ይበዛሉ፤ ደም በከንቱ ይፈሳል፤ ግፈኞች በግፋቸው ይገፉበታል፤ የሰው ልጅ ሰቆቃ ይበዛል፤ ምድሪቱ መከራ የሚዘራባትና ሞት የሚታጨድባት ትሆናለች፡፡ (ኢሳ.፭፥፳)
በኤርምያስ ዘመን የሆነው እንዲህ ነበር፡፡ ልክ እንደ ዛሬው ክፉዎች ሠልጥነው ነበር፤ ከመከራቸው የተነሣ ልጆች፣ ድሃ አደጎችና አባት እናት የሌላቸው ሕፃናት ብዙዎች ነበሩ፤ እናቶች እንደ መበለቶች ሆነው ነበር፡፡ ውኃቸውን በብር እንጨቶቻቸውን፣ በዋጋ ገዝተው የተጠቀሙበት ጊዜ ነበር፡፡
እንጀራን ለመጥገብ እጃቸውን ለግብጻውያንና፣ ለአሦራውያን የሰጡበት፣ ጠላት በላያቸው ላይ ሠልጥኖ የሚታደጋቸው ያጡበት፣ ረኃብ የተነሣ የሰውነታቸው ቆዳ እንደ ምድጃ የጠቆረበት፣ ጎልማሶቻቸው ወፍጮን የተሸከሙበት፣ ልጆቻቸው ከዕንጨት በታች የተሰናከሉበት፣ ሽማግሌዎቻቸው ከአደባባይ፣ ጎልማሶቻቸው ከበገና የተሻሩበት፣ አለቆቻቸው በራሳቸው የተሰቀሉበት፣ የሽማግሌዎቻቸው ፊት ያልታፈረበት ነበር፡፡ ይህም ስለ ኃጢአታቸው ዋጋ ተከፈላቸው ነበር፡፡
ዛሬ እኛም እንዲሁ ሆነናል፡፡ የሕፃናት ልቅሶ ጆሮቻችንን አደንቁሮታል፡፡ ብዙዎች እጓለ ማውታ ሆነዋልና፡፡ ብዙዎች እናቶች ቆዳቸው ደርቋል፤ አንጀታቸው ታጥፏል፤ ወገባቸውን በጠፍር ታጥቀዋል፤ ዐይናቸው በእንባ ፈዝዟል፤ ጉልበታቸው በኀዘን ብዛት ዝሏል፤ ወገባቸው ጎብጧል፤ እንደ መበልትም ሆነዋል፡፡
ምድሪቱ በደም ርሳለች፤ የምታበቅለው መከራ ነው፤ የሚታጨደው ሞት ነው፤ ሰማይ ከምድር ርቋል፤ የሚታጠነው ማዕጠንት፣ የሚሠዋው መሥዋዕት የሚቆመው ማኅሌት ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ግዳጅ መፈጸም ተስኖታል፡፡
አባቶች በሽበታቸው አይከበሩም፤ አይከብሩም፤ ካህናት አይመክሩም፤ መምህራን አያስተምሩም፤ መናንያን ከበዓታቸው፣ ተማሪዎች ከጉባኤያቸው ወጥተዋል፤ ዳኞች ፍትሕ አያሰፍኑም፤ እረኞች መንጋቸውን አያሰማሩም፤ በጎቹን ወደ በረት፣ ግልገሎቹን ወደ ጋጥ የሚሰበስብ የለም፡፡ ‹‹ነቢያት›› እውነተኛ ትንቢት፣ ‹‹ሐዋርያት›› እውነተኛ ትምህርት አይናገሩም፡፡
እንጀራን እንጠግብ ዘንድ በማሰብ እጃችንን አሳልፈን ለዓለምና ለዓለማዊነት በፈቃዳችን ሰጥተናል፡፡ ሁላችንም ከጸጋው ተናጥበናል፤ የተቀዳጀነውን አክሊል አውልቀን ጥለናል፡፡ ከዕጣኑ በፊት ራሳችንን የተወደደ መዓዛ ያለው ዕጣን አድርገን አላቀረብንምና፤ ከመሥዋዕቱ በፊት ሰውነታችንን የተወደደ መሥዋዕት አደርገን አላዘጋጀነውምና ከሁሉ ይልቅ የሚቀድመውና የተወደደው መሥዋዕት ሰውነትን ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ነውና፡፡ (ሮሜ ፲፪፥፩)
ነቢዩ ለዚህ ነበር ‹‹ኃጢአት ሠርተናልና ወዮልን›› ማለቱ፡፡ ይህ ሁሉ መከራ በኃጢአት ምክንያት እንደ ደረሰባቸው ያውቃልና፡፡ እነርሱ ከእኛ የተሻሉ ነበሩ፡፡ መከራቸውን አስበዋል፤ በኃጢአታቸው ምክንያት መከራው እንደ መጣባቸውም ዐውቀዋል፤ ጥፋተኛነታቸውንም አምነዋል፤ ራሳቸውንም ወቅሰው ይቅርታን ለምነዋል፡፡ የሆነባቸውንም ሁሉ እንዲያስብ፣ስድባቸውንም እንዲመለከት ‹‹አቤቱ የሆነብንን አስብ፤ ስድባችንንም እይ›› በማለት አሳስበዋል፡፡ (ሰቆ.ኤር.፭፥፩)
እኛ ግን ኃጢአታችንን አላመንንም፤ ምድሪቱ በግፍ ስትሞላ፣ የንጹሐን ደም እንደ ጅረት ሲፈስ፣ ሚሊዮኖች በረኃብና በጥም በእርዛት ሲገረፉ፣ ሰላም በነፍስ ሰላም በመንፈስ አጥተው ሲቅበዘበዙ እያየን፣ ወጥቶ መግባት፣ ሠርቶ መብላት፣ ለፍቶ ማደር ለብዙዎች ብርቅ ሆኖ ሀገር በጦርነት ስትታመስ፣ ንጹሐን እንደ በግ ሲታረዱ፣ እንደ ሣር ሲታጨዱ፣ ጩኸታቸው የማይረብሸን፣ ደማቸው የማይጎፈንነን ሆነናል፤ ካህናት ሲታረዱ፣ አብያተ ክርስቲያነት ሲነድዱ ልባችን አይደነግጥም፤ ወደ ቀልባችን ለመመለስ አልቻልንም፡፡
ክፋትን ለማውገዝ፣ የሚያስችል ትንሽ የሞራል እንጥፍጣፊ ያልቀረልን፣ ክፋትን የተለማመድን፣ ሞት የማያስደነግጠን፣ እየሆነብን ያለውን እንኳን በውል የማንረዳ አሳዛኝ ፍጥረቶች ሆነናልና ወዮልን!
እንደ ነቢዩ ኤርምያስ እና እንደ ዘመኑ ሰዎች የመከራ ገፈት ቀማሽ እንደ መሆናችን መፍትሔው እንደ ኤርምያስና ዘመኑ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መጮህ ‹‹አድነን፤ አስበን›› ማለት ብቻ ነው፡፡ ‹‹አቤቱ የሆነብንን አስብ፤ ተመልከተንም›› ብሎ መጮህ ይገባል፤ ያድነን ዘንድ፡፡ የሆነብንን ያስብ ዘንድ፡፡ የመከራችን ምክንያት ሁሉ ግን ኃጢአታችን፣ በደላችን መሆኑን ማመንና ወዮልን ማለት ያስፈልጋል፡፡
‹‹አቤቱ የሆነብንን አስብ!››
ወስብሐት ለእግዚአብሔር! አሜን!