“የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል” (ማቴ.፳፬፥፯)
መምህር ቢትወደድ ወርቁ
ጥቅምት ፲፯፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
የምድር መናወጥ ወይም መንቀጥቀጥ በታሪክ መመዝገብ ከተጀመረበት ዘመን አንሥቶ እስከደረስንበት ዘመን ድረስ ከባድ የሚባል በሬክተር ስኬል ሰባት ነጥብ ሁለት እና ከዚያ በላይ በዐሥርት ዓመታት ቢበዛ አንድ ጊዜ ነበር የሚከሠተው፡፡ ከ፲፱፻ ዓ.ም ወዲህ ግን ክብደቱም ብዛቱም የሚያደርሰውም ሰብአዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና መሠረተ ልማታዊ ውድመቱና ጥፋቱ ጨምሯል፡፡ ከ ፲፱፻ እስከ ፲፱፻፵፱ በየዐሥርት ዓመቱ የሚደርሰው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ሦስት እና ከዚያ በላይ ሆኗል፡፡ በ፲፱፻፶ዎቹ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ዘጠኝ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጦች ደርሰዋል፡፡ በ፲፱፻፸ዎቹ ፻፳፭ አደገኛ የመሬት መንቀጥቀጦች ደርሰዋል፡፡ (Grant Jefferey, The signature of God, Wheaton, I11: Tyndale publishing, 1996, 194) ይህንን ሁኔታ ስንመለከተው ምድራችን በመሬት መንቀጥቀጥ ብዛትና ክብደት እየፈረሰች መሄዷ የማይቀር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
የመሬት ንዝረት፣ የአፈር መቅለጥ፣ የመሬት መንሸራተት፣ የመሬት መሰንጠቅ፣ የመሬት ናዳ፣ ሰደድ እሳትና ሱናሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ምልክቶች ሆነው ይነሣሉ፡፡ የምድር መናወጥ ድንገተኛና ሳይጠበቅ የሚከሰት ከመሆኑ አንጻር የሚያደርሰውም ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ሰዎች እጅግ ተጠጋግተው በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሲከሰት ደግሞ ጥፋቱ በዚያው አንጻር ይጨምራል፡፡ የምድር መናወጥን በተመለከተ የሳይንስ ሰዎች ራሱን የቻለ ትንታኔ የሚሰጡ መሆኑና እስካሁንም እየሰጡ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም ከፍጻሜ ዘመን ምልክቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል” በማለት ተናግሯል፡፡ (ማቴ.፳፬፥፯)
የምድር መናወጥ እምብዛም አይሰማባት የነበረች ሀገራችን ኢትዮጵያ እንኳን በዚህ አዲስ ዓመት በልዩ ልዩ ስፍራዎቿ ክስተቱን አስተናግዳለች፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት የምድር መናወጥ አንዱ የእግዚአብሔር ቁጣ መገለጫ መሆኑ ተነግሮናል፡፡ ይህንንም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ሲገልጥ “ሰባተኛውም መልአክ ጽዋውን በአየር ላይ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ፡- ተፈጽሞአል የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ ወጣ፡፡ መብረቅና ድምፅም ነጓድጓድም ሆኑ ትልቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው ከምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ መናወጥ ከቶ አልነበረም፤ ከሁሉ በለጠ” ብሏል፡፡ (ራእይ ፲፮፥፲፯-፲፰፣ ፲፩፥፲፫)
የዮሐንስ ራእይን የተረጎሙ ቀደምት ሊቃውንት እንደሚያስተምሩን በምድር ላይ ዓመፃን የሚከተሉትንና በንስሐ የማይመለሱ ሰዎችን ለመምታት ከሚላኩ ክስተቶች አንዱ የምድር መናወጥ ነው፡፡ የሐሳዌ መሲሕ ክፉ መንግሥት እንደሚፈራርስ ሁሉ በዚህ ዓለምም የእርሱን መንገድ ለመጥረግ ያንኑ መንገድ የሚከተሉ ሰዎችና ቡድኖችም መፈራረሳቸው አይቀርም፡፡ የመሬት መናወጥ የሚያገኘው ስፍራ፣ ከተማና ሀገር እንዳልነበረ እንደሚሆን ሁሉ የሐሳዌ መሢሕና የመንገድ ጠራጊዎቹም ስኬት ከፍታና ታላቅነት ይፈራርሳል፡፡
በዘመናችን እንደሚስተዋለው የዓለማችን ኃይላት ይገለባበጣሉ፤ የሚረጋም ነገር የለም፡፡ ይናወጣሉ፤ መናወጣቸውም እንዳይመለሱ ሆነው ነው፡፡ በፍፃሜ ዘመን እግዚአብሔርን የሚክድ የሚያስክድ፣ ሃይማኖትና ሞራል አልባ የሆነ በሥጋ ፍላጎትና ፍትወት ብቻ የሚመራ ሥርዓት በዓለም ላይ ይነግሣል፡፡ ይህም ክፉ የዓለም ሥርዓት እንደታወከና ዓለምን እንዳተራመሰ ይህ መቅሠፍት ማሳያ ነው፡፡
በዚህ ዘመን ለማንኛውም ጉዳይ ግድ የማይሰጠን ለዘብተኞች፣ ታላቁን የእግዚአብሔር ቃል ቅዱስ መጽሐፍን እየጠቀስን ኃጢአትን የምንሠራ ተጠራጣሪዎች፣ ማንኛውንም የሞራል። የባህል። የእምነት እና የሕሊና ሕግ ወደ ኋላ ብለን ልቅነትን የምናበረታታና የምናስፋፋ ዐመፀኞች ሰዎችም እንበዛለን፡፡
“እግዚአብሔር ቸር ከሆነ ለምን ይቆጣናል?” የምንል ሰዎች በዝተን እየታየን ቢሆንም እየሠራን ያለው ግፍ፣ በሰዎች መካከል መለያየቶችንና ጠብን ለመፍጠር የምንዘራው የነገር ዘር፣ ፍርድ ማጓደልና ደሀ መበደል፣ ጉቦ መማለጃና እጅ መንሻ እየተቀበልን የምናጣምመው ፍርድ፣ ዝሙትና ግብረ ሰዶማዊነት በዝቶ፣ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረ የሰውን ልጅ የመናቃችንና የማቃለላችን ከፍታ፣ ሥጋዊ ጥቅም ለማግኘት ስንል የምናፈሰው ደምና የመሳሰሉት ግብሮቻችን የእግዚአብሔርን ቁጣ የሚያመጡ ናቸው፡፡
የፍርድ ቤት ክሶችና ችሎቶች ለምን በዙ? ግብረ ሰዶማዊነትና አንዳችን በሌላችን ላይ የምንወስዳቸው የበቀል እርምጃዎች ለምን ተበራከቱ? አንዱ በሌላው ላይ ፈጸመ እየተባለ በሚነገረን ክፉ ነገር መበሳጨታችንና ኀዘናችን ለምን በዛ? የራሳችን ክፉ ግብር ራሳችንን ሳይቀር የሚያስቆጣ መሆኑን አያመለክትምን? መሬት ሳትቀር ክፉ ሥራችንን ተጠይፋ ስትሸሽ፣ ስትንሸራተትና ስትናወጥ፣ “እንዲህ የሆነውና እየሆነ፣ ያለው ወደፊትም የሚሆነው በእኛ ኃጢአትና ክፉ ሥራ ምክንያት ነው፤ ፈጣሪያችንን ስላሳዘነው ነው” ብለን ንስሐ ከመግባት ይልቅ “እግዚአብሔር ጨካኝ ስለሆነ ነው” አልያም “እንዲህና እንዲህ የሚባል የተፈጥሮ ነገር ስለተከሠተ ነው፤ በመሬት ውስጥ ያሉ ዐለቶች መገፋፋት ስለጀመሩ ነው” የሚሉ የዐመፅና ሳይንሳዊ መላ ምቶችን እንሰጣለን፡፡
ክርስትና ሳይንስ እንደ ሳይንስ ከሚሰጣቸው ምክንያቶች ጋር ጠብ ባይኖረውም ትንተናውን ለጊዜው አቆይተን ንስሐ እንድንገባ ግን ዘወትር ያስተምረናል፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “አደመጥሁ ሰማሁም፤ ቅንን ነገር አልተናገሩም፤ማናቸውም ምን አድርጌሃለሁ ብሎ ከክፋቱ ንስሐ የገባ የለም፤ ወደ ሰልፍም እንደሚሮጥ ፈረስ እያንዳንዱ በየመንገዱ ይሄዳል፡፡” (ኤር.፰፥፮)
ስለሆነም እግዚአብሔር “ጨካኝ ነው” የሚለውን ስንዝር የሚያስኬደንን ጽርፈት ትተን ሳይንሳዊ ያልነውን ትንታኔ ገታ አድርገን ንስሐ እንግባ፡፡ ተስፋ የሚኖረን ንስሐ ስንገባ ነው፤ ነገ በሚመጣውና በሚያስፈራን ነገር ውስጥ ያለ ፍርሃት ልንሻገር የምንችለው ንስሐ ገብተን ፈጣሪያችንን ጥግ ስናደርግ ነው፡፡ እርሱን መጠጊያ የሚያደርጉ የመሬት መናወጥን፣ የመሬት መንሸራተትን፣ የሱናሚና የመሳሰሉትን ሁሉ አይፈሩም፡፡ “በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ እንኳን ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉውን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል” በማለት ነቢዩ እንደመሰከረው፡፡ (መዝ.፳፪፥፬) በኃጢአት ከሚመጣብን ቅጣትና ፍርሃት ለመዳን ዝሙትን እንተው፤ ዘረኝነት ይቅርብን፤ ተንኮልና ሤራዎች ከእኛ ይወገዱ፤ የጉቦና የዘመድ አዝማድ አሠራር ከእኛ ፈቀቅ ይበል፤ በሰዎች መካከል ጠብ መዝራት በእኛ ዘንድ አይሰማ!
ይቆየን!
የአምላካችን የእግዚአብሔር ቸርነት እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን!