አማላጅነት
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ጥቅምት ፲፬፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? ትምህርት እንዴት ነው? በርትታችሁ እየተማራችሁ ነውን? ጥናቱንም ከወዲሁ ጀምሩ! ያልገባችሁንም ጠይቁ! መንፈሳዊ ትምህርትንም በዕረፍት ቀናችሁ ተማሩ፤
ወደፊት ለመሆን የምትፈልጉትን ለመሆን አሁን በርትታችሁ ተማሩ! ቤት ስትገቡ የቤት ሥራችሁን ብቻ ሳይሆን መሥራት ያለባችሁ የተማራችሁትንም መከለስ ነው! ከዚያም ያልተረዳችሁትን መምህራችሁን ጠይቁ፤ መልካም!
ባለፈው ትምህርታችን ጥያቄዎች አቅርበንላችሁ ምላሶቹን ልካችሁልን ነበር፤ እኛም ትክክለኛ የሆኑትን ምላሾች ነግረናቹኋል፤ ለዛሬ ደግሞ “አማላጅነት” በሚል ርእስ እንማራለን! ተከታተሉን!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ስለ አማላጅነት ከመንገራችን በፊት ጥቂት ስለ ምልጃ እንንገራችሁ፤ ምልጃ “ጸሎት፣ ልመና” የሚል ፍቺ አለው፡፡ አማላጅ ማለት ደግሞ “ስለ ሌላው የሚጸልይ፣ የሚለምን” ማለት ነው፤ በምልጃ ውስጥ የሚለመን፣ የሚለምን እና የሚለመንለት አለ፤ (ይቅርታ የሚጠየቅ፣ ይቅርታን የሚጠይቅ፣ ይቅርታን የሚጠይቅለት አለ)
የማማለድ፣ የማስታረቅ ጸጋ ያላቸው ቅዱሳን ናቸው፡፡ ያማልዳሉ ስንል በኃጥአን ፈንታ ስለ ኃጥአን ወደ እግዚአብሔር ምልጃን ያቀርባሉ፡፡ የሚማለደው (የሚለመነው) እግዚአብሔር የአማላጁን (የቅዱሳንን) ጸሎት፣ ልመና ተቀብሎ የፈቃዱንና የቸርነቱን ሥራ ለሚማለድላቸው ሰዎች ያደርጋል፤ የሚማለድለት ሰው በአማላጅነት ሥራ ውስጥ የራሱ ድርሻ አለው፡፡ ይኸውም በአማላጁ (በቅዱሳኑ) ጸሎት በተማላጁ (በእግዚአብሔር) ቸርነት ማመንና ከሚሠራው ኃጢአት የሚመለስ፣ ንስሐ የሚገባ (ተነሣሒ) ልቡና ያለው መሆን አለበት፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የአማላጅነትን ጸጋ የሰጠው (የፈቀደው) እግዚአብሔር ነው፤ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላው መልእክት ‹‹…በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን …›› በማለት እንደገለጸው ቅዱሳን ሰዎችን በማማለድ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲያስታርቁ፣ የሰዎችን ልመና ከፈጣሪ እንዲያደርሱ የማማለድን ጸጋ እንደሰጣቸው እንመለከታለን፡፡ (፪ኛ ቆሮ. ፭፥፲፱)
ለአብነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎችን እንመልከት፤ ጌራራ በሚባል አገር ንጉሥ የነበረ አቤሜሌክ የተባለን ሰው እግዚአብሔር በሕልሙ ተገልጾ ጥፋት እንዳያጠፋ ነገረው፤ ሊሠራ ስላሰበው በደል ግን አብርሃም የተባለው እግዚአብሔር ወዳጅ ስለእርሱ እንዲጸልይለት ነገረው፡፡ ‹‹ነቢይ ነውና ስለአንተም ይጸልያል፤ ትድናለህም..፡፡›› (ዘፍ.፳፥፯)
የጻድቁ ኢዮብ ጓደኞችም በበደሉ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር መልካም የሆነን (ቅን) ነገርን ባልተናሩና በበደሉ ሰዓት ሊቀጡ በነበሩበት ጊዜ ጻዲቁ ኢዮብ ወደ እግዚአብሔር ለእነርሱ እንዲለምንላቸው ወደ ኢዮብ እንዲሄዱ ገለጸላቸው፤ ‹‹…ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፤ እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለው፡፡ …›› (ኢዮ.፵፪፥፯-፱)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለማስረጃ ያህል ለግንዛቤ እነዚህን ገለጽንላችሁ፤ ቅዱሳን ለኃጥአን እንዲለምኑና ኃጥአን ደግሞ ከበደላቸው ተመልሰው ከእርሱ ጋር እንዲታረቁ የፈቀደው (የማማለድን ጸጋ) የሰጠው እግዚአብሔር ነው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የቅዱሳን አማላጅነት ያስፈለገበት ምክንያት እግዚአብሔር ከኃጥአን ጸሎት ይልቅ የወዳጆቹ የቅዱሳንን ጸሎት ስለሚቀበል፣ ጸሎታችን በፍጥነት ወደ እግዚአብሔር እንዲደርስልንና ፈጣሪያችንም ስለ እነርሱ ሲል ቸርነቱን ስለሚያደርግልን ነው፡፡ እግዚአብሔር የቅዱሳንን ጸሎት እንደሚሰማና ምልጃቸውም ግዳጅ ፈጻሚ መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጿል፤ ‹‹…ኢዮብም ስለ ወዳጆቹ በጸለየ ጊዜ እግዚአብሔር ምርኮውን መለሰለት…››እንዲል፡፡(ኢዮ. ፵፪፥፲)
ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊትም በመዝሙሩ እንዲህ ይመሰክርልናል፤ ‹‹…የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮችም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና…፡፡›› (መዝ.፴፫፥፲፭)
እንግዲህ የቅዱሳን አማላጅነት ያስፈለገበት ምክንያት ቅዱሳን እግዚአብሔር ወዳጆች ስለሆኑ ነው፤ ቅድስናቸውም በተጋድሏቸው ጽናት ከእግዚአብሔር በጸጋ የተሰጣቸው ነው፤ የቅዱሳን ሕይወት የእግዚአብሔር መገለጪያ ነው፤ ለሰዎች ምሕረቱንና ቸርነቱን በቅዱሳን አማካኝነት ያደርጋል፤ ‹‹…እግዚአብሔር በጻድቁ እንደተገለጠ ዕወቁ…›› እንዲል፡፡ (መዝ.፬፥፫)
ቅዱስ ያዕቆብም በመልእክቱ ‹‹የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ ኃይልን ታደርጋለችና›› በማለት ገልጾልናል፡፡ (ያዕ.፭፥፲፫-፳)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ስለ ምልጃ ምንነት፣ ለምን እንዳስፈለገ፣ ማን እንደፈቀደው በመጠኑ ተመልክተናል፤ በሚቀጥለው ትምህርታችን ስለ እመቤታችን፣ ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ስለ ቅዱሳን አባችና እናቶቻችንን አማላጅነት እንማራለን፡፡
ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በዘመናዊ ትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ፤ ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡
ቸር ይግጠመን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!