የአቋም መግለጫ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ፵፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ መደበኛ ጉባኤ የአቋም መግለጫ
“ትውልደ ትውልድ ይንእዱ ምግባሪከ ወይዜንዉ ኃይለከ፤ የልጅ ልጅ ሥራህን ይናገራሉ፤ ያመሰግናሉ፣ ከሃሊነትህን ይናገራሉ ያስተምራሉ፡፡” (መዝ. ፻፵፬፥፬)
፩. በጉባኤው መክፈቻ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ያስተላለፉፉልንን ቃለ ምዕዳንና ቃለ ቡራኬ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ተቀብሎታል፣ ለተግባራዊነቱ ቃል ይገባል፡፡
፪. ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ ያስተላለፉልንን አባታዊ መልእክት ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡
፫. በብዙ የሀገራችን ክፍል ባለው የሰላም እጦት የተፈጠሩት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ምክንያት የካህናት፣ የመነኮሳትና የምእመናን ሞትና ስደት በጥብቅ እያወገዝን በዚህ ታሪክ የማይረሳው በምድር ወንጀል፣ በመንፈሳዊው ዓለምና በሰማይ ኃጥያት የሆነ እኩይ ተግባር የተሰማራችሁ ሁሉ ወደ ርኃራኄ ልብ እንድተመለሱ ጉባኤው በአጽንኦት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
፬. የሰላም ዕጦት ጉዳይ ምንም እንኳ ዓለም አቀፍ ቢሆንም ሀገራችንም በተከሰተው ግጭትና ጦርነት ምክንያት ሰላም ካጣች ሰንብታለች፣ ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ በዓለም የሚደነቅ፣ ለሀገር ተገን የሚሆን አስደነቂ ውሳኔ እንደሚወስን ተስፋችን ጽኑ ነው፣ ጸሎታችንም ነው፤ የአገልጋዮች እንባ የሚታበስበት፣ ለነገ ታሪክ የትውልድ ተወቃሽ ከመሆን ይልቅ፤ የሰላምና እርቅ ምሳሌ የምንሆንበት ከፍተኛ የሰላም ሥራ ልዩ የሆነ የሰላም ኮሚቴ ተቋቁሞ ዘላቂ ሰላምን ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የሚያመጣ ሥራ እንዲሠራ ጉባኤው ያሳስባል፡፡
፭. የዚህን ዓለም ተድላ ንቀው፣ ዳዋ ለብሰው ጤዛ ልሰው በገዳም ተወስነው ድምጸ አራዊቱን ግርማ ሌሊቱን ታግሰው ለመላው የሰው ዘር የሚጸልዩ ይህን ይደግፋሉ ያንን ይቃወማሉ የማይባሉ ገዳማውያን መነኮሳት ከየበዓታቸው ተጎትተው ወጥተው የተገደሉበት ሁኔታ በሀገራችን መከሰቱ ጉባኤውን እጅግ አሳዝኖታል፤ ይህ ጉዳይ ቀጣይነቱ እየታየ ስለሆነ የሚመለከታቸው ሁሉ ተገቢውን የሕግ ሥራ በመሥራት የሰው ልጅ ከአምላክ የተሰጠውን የመኖር መብት፣ የእምነት ነፃነት፣ የመዘዋር ተፈጥሯዊና ሰብዓዊ መብት በሀገራች እንዲከበር ያሳስባል፡፡
፮. በታሪካችን ያላየነው ከአባቶቻችን ያልሰማነው በመጻሕፍት ያላነበብነው ከኢትዮጵያ ባሕልና ሥነ ልቡና ውጪ በሆነ መንገድ ሰዎችን ለገንዘብ ሲባል ማገት በተለይም ፊትና ኋላ፣ ግራና ቀኝ፣ እሳትና ውኃ ያለዩ ሕጻናት በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው፣ ወጣቶችና አረጋውያን ሳይቀር እያተገቱ የሚሰቃዩበትና የሚደፈሩበት ሁኔታ የገጠመንን ፈተና ክብደቱን የሚያሳይ መሆኑ ይህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሔ እንዲበጅለት ጉባኤው ጥሪውን ያቀርባል፡፡
፯. ጥላቻና የጥፋት ቅስቀሳዎች፣ በዜጎች መካከል አለመተማመንና መለያየት፣ ለሀገር አንድነትና የሕዝብ አብሮነት ጠንቅ፣ ለወደፊቱ አስጊ የሆኑ እንቅስቃሴዎች የበዙበት፣ የትውልዱ የወደፊት በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ የመኖር ዋስትና እየጠፋ፣ በርካታ ወጣቶች በስደትና በመፈናቀል ላይ ያሉበት ሁኔታ በመኖሩ የጥላች ንግግር፣ ዘለፋና ያልተገባ ትችትና መናናቅ ማንንም የማያንጽ ክፉ ትምህርት፣ ለሀገርም፣ ለሕዝብም የማይጠቅም ሁሉንም የሚያጠፋ ስለሆነ በእንዲህ ያለ ተግባር መገናኛ ብዙኃን በመጠቀም የተሰማራችሁ፣ ሁሉ በሚያፋቅርና በሚያዋድድ ተግባር እንድትሰማሩ ጉባኤው ጥሪውን ያቀርባል፣ ቅዱስ ሲኖዶስም ለዚሁ ትኩረት ሰጥቶ መመሪያና ውሳኔ ያወጣ ዘንድ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡
፰. በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 20 በእንተ ሰማዕታት የጌታችንን ትምህርት መሠረት በማድረግ በተሠራው ቀኖና ካህናትና ምእመናን ሰማዕትነትን የተቀበሉበትን ቀን መዘከርና ማክበር፣ የከበረ አጽማቸውን በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን በክብር ማስቀመጥ፣ ቤተሰቦቻቸውንና በእነሱ ሥራ ይተዳደሩ የነበሩ የሰማእታት ቤተሰብ በሚል መርዳት የተደነገገ ቀኖና ነው፤ ይህን በማድረግ የሰማዕትነት ዋጋን እናገኛለን፣ ቤተ ክርስቲያነን እናጸናለን፤ በዚህ ቀኖና መሠረትና ከሰብዓዊ ርኅራሄ በመነሣት በሰማዕትነት የተለዩን ወገኖች መታሰቢያቸው እንዲደረግ፣ ቤተሰቦቻቸውና ጉዳተኞችን ወላጆቻውን ያጡ የካህነትና የምእመንና ጨቅላ ሕጻናትና ያልደረሱ ልጆች፣ ያለጧሪ የቀሩ አረጋውያን የቤተ ክርስቲያንን እንክብካቤ በጥብቅ ይፈልጋሉ፤ ለዚህ መፍትሔ እንዲሆን በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ አህጉረ ሰብከት ያካተተ አስቸኳይ ዓለም አቀፍ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲሰጥበት እያሳሰብን ለተግባራዊነቱም ሁላችንም ቃል እንገባለን፡፡
፱. በአንዳንድ አካባቢዎች ሕግንና የአምልኮ ነፃነት ሰብዓዊ መብትን በመጣስ የመስቀል ደመራና የባሕረ ጥምቀት ቦታ መወሰድ ሃይማኖታዊ አለባበስና መስቀል መያዝን በመከልከል የአንገት ማዕተብን መበጠስ፣ በኦርቶዶክሳውያን ላይ እንግልትና ወከባ መፍጠር አሳዛኝ በመሆኑ ድገርጊቱን አጥብቀን እየተቃወመን በቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ውይይት እንዲደረግበት ጉባኤው ያሳስባል፡፡
፲. ቤተ ክርስቲያን እንኳንስ ተናግራ ሰማች ሲባል የሚያስደነግጥ ግርማና መታፈር፣ መከበርና መወደድ የነበራት በመሠረተችው ሀገር የምትሳደድበት፣ የመሪዎቿ አባቶች ጥሪ የማይከበርበት፣ የሰላም ጥሪ ድምጽዋ የማይሰመባት፣ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በመፈተሸ ክብርና ልዕልናዋ እንዲመለስ በቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ውይይትና ጥልቅ ምክክር እንዲደረግ መፍትሔም እንዲፈለግለት ጉባኤ ያሳስባል፡፡
፲፩. ሙስና፣ ዘረኝነት፣ ጎሠኝነት፣ ቡድነኝነት፣ አድሎዓዊነትና ግለኝት በተመለከተ በጋራ በአንድ ድምጽ በመነሣት ይህንን ክብረ ነክና አጋላጭ፣ ለቤተ ክርስቲያን እድገትና ለሐዋርያዊ ተልእኮ እንቅፋት፣ የቤተ ክርስቲያን ማንነት ለሌላቸው ግለሰቦች መደበቂያ፣ በጥቂት ግለሰቦች በደልና ጥፋት በንጽሕና በቅድስና የሚያገለግሉ፣ ካህናትንና ሠራተኞችን የሚያሳፍሩ፣ ምእመናንን የሚያሸማቅቁ
በመሆናቸው እነዚህን ክፉ ደዌያት ስም አጠራራቸውን ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለማስወገድ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በጥናትና በቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተ፣ የጥፋት በራቸውን በዘላቂነት የሚዘጋ ሥልት እንዲቀይስ ጉባኤው ያሳስባል፡፡
፲፪. በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት እስከ አሁን ቤተ ክርስቲያን በፈረሱባት ሕንጻዎችና ቤቶች ምትክ ቦታ በመስጠት ጉዳቷን ለመቀነሰ የተደረገውን ጥረት ጉባኤው እያደነቀ፤ በተሰጡት ይዞታዎች ላይ በአጭር ጊዜ ግንባታውን በማካሄድ የአባቶችቻንን አሻራ መልሶ በመትከል፣ ይዞታውን ማስከበርና የተቋረጠውን ገቢ ማስቀጠል እንዲቻል ብርቱ ጥረት እንዲደረግ ጉባኤው እያሳሰበ፤ የኮሪደር ልማት የተባለው ጉዳይ በሌሎች የክልል ከተሞችም እየተስፋፋ ስለሆነ በቀጣይ ለሚነሡ የይዞታ ጥያቄዎች ለሚከሰቱ ችግሮች ከወዲሁ ዝግጅት እንዲደረግ፡፡
፲፫. አዳዲስ አማኞችን አሳምኖ ለሥላሴ ልጅነት ማብቃት፣ የአዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት መተከል፣ መታነጽና መባረክ የታየው ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ እመርታ ሁሉን ያስደሰተ በመሆኑ ከዚህ በበለጠ አጠናክረን ለመሥራት ቃል እንገባን፡፡
፲፬. የቅዱስ ባኮስ የቅድስና ዕውቅና ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ስትዘግበው የቆየ ቢሆንም ጽላት ተቀርፆ እንዲከበር መደረጉ አስደሳች ሲሆን ለሀገር በረከት፣ ለትውልድ የመንፈሳዊ ሕይወት አርአያ፣ ለቅድስና ፍኖት የሆኑ ነገርግን የማይታወቁ የሌሎች ኢትዮጵያውያንን ቅዱሳን ታሪክና ገድል በማጥናት እንዲዘከሩ እንዲደረግ ጉባኤው ያሳስባል፡፡
፲፭. በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የተከፈቱ መንፈሳውያን ኮሌጆችና የካህናት ማሠልጠኛዎችም በአጥጋቢ ሁኔታ ሥራ መጀመራቸው፣ በዚህ ዘርፍ በእጥፍ እየጨመረ የመጣው ዕድገትና ውጤት ጉባኤው ያደነቀ ሲሆን ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ ያሉት በርካታ መንፈሳዊ ኮሌጆች እየተስፋፉ ያሉ የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ ዘመናዊ የትምህርት ተቋማት በአጠቃላይ ሁሉም ትምህርትን የሚመለከት ጉዳይ በትምህርት ኮሚሽን ተቋቁሞ ጥናት በማድረግ እንዲስፋፉ ጉባኤው ያሳስባል፡፡
፲፮. በሰላም መታጣትና በቀኖና ጥሰት ምክንያት መላው ወለጋ አህጉረ ስብከት ለበርካታ ወራት ከማእከሉ ጋር ያለው ግንኙነት ተቋርጦ ከቆየ በኋላ በቅርቡ በሀገረ ሰብከቱ ሊቀ ጳጳስ ወደ መዋቅር መመለሳቸው ጉባኤውን በእጅጉ አስደስቷል፤ ስለሆነም ቀሪ ሥራዎች ተጠናቀው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር እንዲጠበቅ፣ በሌሎችም አካባቢዎች ለተፈጠሩት የመዋቅር ጥሰቶች ቀኖናዊ መፍትሔ እንዲበጅለት ጉባኤ ያሳስባል፡፡
፲፯. ሐዋርያዊትና የክርስቶስ አገልጋይ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ቋንቋን በማክበር ታገለግልበታለች እንጅ በቋንቋም አትገደብም፤ ስለዚህ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ሐዋርያዊ ተልእኮ መፈጸሟ እንደተጠበቀ ሆኖ ለወደፊት የሁሉም መዓረገ ክህነት ሢመት፣ በየደረጃው ያሉ የአስተዳደር ሥራ የኀላፊነት ምደባዎች፣ መሠረት እምነትን፣ ቀኖና ቤተክርስቲያንን፣ ዕውቀትና ሙያዊ ብቃትን ብቻ መሠረት ያደረገ ይሆን ዘንድ ጉባኤው በጥብቅ ያሳስባል፡፡
፲፰. ሰበካ ጉባኤን ማጠናከር፣ ሰንበት ትምህርት ቤትን ማደራጀት፣ አብነት ትምህርት ቤቶች ማጎልበትና ማስፋፋት፣ ሕጎችና ደንቦችን በማዘጋጀት የተደረገውን ጥረት የሚያስመሰግን ሆኖ አሁን ወቅቱን የጠበቁ ሕጎችና ደንቦችን በማውጣት ሁሉም እንዲሠራበት ማድረግን፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ የራስ አገዝ ልማትን ማሳደግና በገቢ ራስን መቻል፣ በጸደቀው የዐሥር ዓመቱ መሪ ዕቅድ መሥራት የቤተ ክርስቲያናችን ዓይነተኛ ተልእኮ በመሆኑ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ለመፈጸም ቃል እንገባለን፡፡
፲፱. የቤተ ክርስቲያናችን የውጭ ሀገር አገልግሎት እየሰፋና እያደገ መምጣቱ በጉልህ የሚታይ ሲሆን ይህ እድገትና አደረጃጀት እንዲጠናከር፤ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሳትፎ የበለጠ እንዲያድግ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ ጉባኤው ያሳስባል፡፡
፳. ከውይይትና ከብፁዓን አበው መልእክቶች እንደተሰጠው መመሪያ የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና ለመመለስ፣ ለሀገራንችን ሰላምና ደኅንነት ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ግንኙነት የጋራ ጸሎት በኅብረት ይደረግ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እንዲሰጥበት ጉባኤ በአክብሮት ይጠይቃል፡፡
በመጨረሻም እስከ ዛሬ ስንሰበሰብበት ከነበረው መቃረቢያ አዳራሽ ወጥተን ይህ ዛሬ የተገኘንበት አዳራሽ በአጭር ጊዜ አሁን ባለበት ደረጃ እንዲህ ጸድቶና ተውቦ የ፵፫ኛውን አጠቃላይ ጉበኤ እንዲከናወንበት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አመራር መስጠታቸው ቁርጠኝነት ካለ ብዙ መሥራት እንደሚቻል ያሳየ፣ የሥራ ክትትልና አፈጻጸም አድናቆታችንን በመግለጽ ሐዋርያው እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖርና እንዳለው የአዳራሹ ቀሪው ሥራ ተጠናቆ በቅርቡ እንደሚመረቅ ተስፋችንን እንገልጻለን፡፡
ይህ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጸም ያደረጉ በቅዱስነታቸው አባታዊ ርእሰ መንበርነት፣ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በሳልና የተረጋጋ አመራር ሁሉም መርሐ ግብሮች በተያዘላቸው ሰዓትና ጊዜ ተጠናቀው እንዲፈጸሉ የመሩንን አባቶች በረከታችሁ ይድረሰን እያልን፡፡
የጉባአው ዋና አዘጋጅ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ኀላፊና መላው ሠራተኞች፣ ሁሉም ተባባሪ አካላት በገንዘብም በጉልበትም ትብብር ያደረጉ ሁሉ በአጠቃላይ ጉባኤው አመስግኗል፡፡
ከሁሉም በላይ ለዚህ ለ፵፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ መደበኛ ጉባኤ ያደረሰንና ያስፈጸመን የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአሔር ምስጋና ይግባው አሜን ሎቱ ስብሐት ወባርኰት ወጥበብ፣ ወአኰቴት፣ ወኃይል ወጽንዕ ለአምላክነ ለዓለመ ዓለም፤ አሜን!