ወርኃ ጥቅምት
ዲያቆን ዘካርያስ ነገደ
መስከረም ፴፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
የጥቅምት ወርን በተመለከተ መጽሐፈ ስንክሳር በወርኃ ጥቅምት ንባብ መግቢያው “የጥቅምት ወር የቀኑ ሰዓት ዐሥራ አንድ ነው፤ ከዚህም በኋላ ይቀንሳል” ይላል፤ ይህም ማለት በቀን ውስጥ ካለው ሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የሌሊቱ ሰዓት ዐሥራ ሦስቱን ሲይዝ የቀኑ ጊዜ ደግሞ ዐሥራ አንዱን ሰዓት ይይዛል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በጥቅምት ወር የሌሊቱ ጊዜ ቀኑ ጊዜ ይረዝማል ማለት ነው፡፡
ጥቅምት ቃሉ “ጠቂም ጠቂሞት” ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም “የተሠራች፣ ሥር” ማለት ነው፤ ዓለም የተፈጠረው በዚህ ወር በመሆኑ “ጥንተ ግብር (የሥራ መጀመሪያ)” ማለት ነው፡
ጥቅምት የሚለውን ቃል ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲተረጉሙ “ስመ ወርኅ፣ ካልእ መስከረም፣ ጽጌውን መደብ አድርጎ ፍሬ፣ ወርኃ ፍሬ፣ መዋዕለ ሰዊት ይሰኛል” ይላሉ፡፡ (መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ፭፻፰)
ጥቅምት፡- የአበባ ወር
ወርኃ ጥቅምት የአበባ ወር መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቅዱስ ያሬድ የዜማ ይትበሃል ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፭ ያለው ጊዜ ወርኃ ጽጌ በመባል ይታወቃል፡፡ ሰፊው የወርኃ ጽጌ ክፍል ደግሞ የጥቅምት ወርን ያማከለ ነው፡፡
ወርኃ ጽጌ የአበባ ጊዜ ማለት ነው፡፡ ሁሉን የማስደሰት ፍላጎት ያለው ጌታ በመጀመሪያ ጊዜ ኮከብን ለሰማይ ውበት፣ ጽጌን ለምድር ጌጥና ሽልማት ሰጠ፡፡ ከዚህ የተነሣ ኮከብ ሰማይን፣ ጽጌ ምድርን ያስጌጣሉ፡፡ ኮከብ ሰማይን አበባ ምድርን በባሕርያቸው ምክንያት እንደሚያስውቡ ራሳቸውንና ገንዘባቸውን የተወደደና ያማረ መሥዋዕት አድርገው ለአምላካቸው የሚሰጡ ምእመናን ገድል እንዲሁ ለቤተ ክርስቲያን የመወደድ ጌጥን ይሰጣታል፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን የአበባን ውበት በተመለከተ “እነሆ ክረምት አለፈ፤ ዝናሙም ተመለሰ፤ አበባዎች በምድራችን ተገለጡ፤ የአጨዳ ጊዜ ደረሰ፤ በለስ ጎመራ፤ ወይኖችም አበቡ፤ መዓዛቸውንም ሰጡ” በማለት ሲዘምር በምሥጢር ደግሞ ፍዳና መርገም እንዳለፈ አበባ ክርስቶስ እንደተገለጠ፣ የምሕረትና የቸርነት ጊዜ ደረሰ በማለት ያስረዳል፡፡ (መኃ.፪፥፲፩-፲፫)
ጽጌ የዓይን ማረፊያ፣ የመልካም ፍሬ መገኛ በመሆኑ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም፣ የመስቀል፣ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡
ሀ. ጽጌ የጌታ ምሳሌ
ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን እውነተኛ መብልና መጠጥ አድርጎ በመስጠቱ፣ የፍሬ መገኛ በሆነው አበባ ተመስሏል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ይህንኑ ሲብራራ “ትወፅእ በትር እምሥርወ ዕሤይ ወየዐርግ ጽጌ ይእቲ በትር አምሳለ ማርያም ቅድስት ይእቲ ወጽጌ ዘወፅአ እምኔሃ አምሳሉ ለወልድ ኀደረ፤ ከዕሤይ ሥር በትር ትወጣለች፤ ከእርሷም አበባ ይወጣል፤ ይህችም በትር የማርያም አምሳል ናት፤ ከእርሷ የተገኘው አበባም የወልድ አምሳል ነው” እንዳለ፡፡
አትክልትና ለአዝርዕት እንዳያብቡና እንዳያፈሩ የሚያደርጉ ብዙ መሰናክሎች እንደ አሉ ሁሉ የክርስቶስ የሆኑት ሁሉ ከብዙ መከራ በኋላ ወደ መንግሥቱ እንደገቡ ከዚህ ሁሉ መሰናክል አልፎ የተገኘ አበባ ነው፡፡ (ማቴ.፲፫፥፩)
ለ. አበባ የእመቤታችን ምሳሌ
አበባን ተወዳጅነት የሚያድለው ማራኪ የሆነው ውጫዊ ገጽታው ብቻ ሳይሆን ሰውም ሆነ እንስሳት በተስፋ የሚጠበቀው የፍሬ መገኛ ስለሆነ ጭምር ነው፡፡ እናም እመቤታችን የእውነተኛ ፍሬ መገኛ በመሆኗ በአበባ ትመሰላለች፤ በፍጡራን አንደበትም ልዩ በሆነ ስጦታዋ ትደነቃለች፡፡ “እስመ ርእየ ሕማማ ለዓመቱ ወገብረ ኃይለ በመዝራዕቱ መዝገቡ ለቃል ጽጌ እንተ ኢትትነገፍ መድኀኒተ ሕዝብ” ያገልጋዩን መዋረድ ዐይቷልና ኃይልን በክንዱ አደረገ፤ የቃልን ማደሪያ የማትረግፈውን አበባ የዓለም መድኃኒት እንድትሆን አደላት፡፡” (ድጓ ዘጽጌ)
ሐ. አበባ የመስቀል ምሳሌ
ንቦች አንድ ሆነው ማር ለመሥራት በአበባ ላይ እንዲሰፍሩ ሕዝብና አሕዛብ በአንድነት የተሰበሰቡበት የዕለተ ዓርቡ የክርስቶስ መስቀል በአበባ ይመሰላል፡፡ “በከመ ይቤ ሰሎሞን በእንተ ማርያም ንዑ ትፈጋዕ ወኢይልኀፈነ ጽጌ ደመና መስቀል ዘዮም አብርሃ በሥነ ማርያም፤ ሰሎሞን ስለ ማርያም ሲናገር እነሆ ክረምቱ አልፎ በረከት ተተካ እንዳለ የክርስቶስ መስቀል በማርያም ባሕርይ ዛሬ አብቧልና የበረከት አበባ ሳያልፈን ኑ እንደሰት” እንዲል፡፡ (ድጓ ዘጽጌ)
መ. አበባ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ
ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው አዲስ ሁኖ በሚታየው አበባ ትመሰላለች፡፡ ይኸውም ቅዱስ ያሬድ “ልዑለ ረሰዮ ለመሠረትኪ አረፋትኪ ዘመረግድ ደቂቅኪ ምሁራን በኀበ እግዚአብሔር ቆዓ ትፄኑ ቆዓ ጽጌ ወይን ወታፈሪ ለነ አስካለ በረከት ጽዮን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጽጌ ደንጎላት ዘውስተ ቆላት፤ የተለየሽ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሆይ መሠረትሽን ከፍ ከፍ አደረገው፤ ግድግዳዎችሽን በመረግድ ደመደማቸው፤ ልጆችሽ በእግዚአብሔር ዘንድ የሠለጠኑ ናቸው በምድረ በዳ እንዳለች የሱፍ አበባ ለጋ የሆነ የወይን አበባ ሽታን ትሸቻለሽ፤ የበረከትንም ፍሬን ታፈሪያለሽ” ባለው ይታወቃል፡፡ (ድጓ ዘጽጌ)
ጥቅምት፡- መዋዕለ ሰዊት
እስራኤል ግብፅን ለቀው ወደ ምድረ ከነዓን ከገቡ በኋላ ክረምቱ አልፎ በጋው ሲተካ አበባው ሲያብብ፣ ሰማዩ ሲገለጥ በዓለ ሰዊትን /የእሸት በዓልን/ ያከብሩ ነበር፡፡ ሲያከበሩም ከዕፅዋትና ከአትክልት ወገን ለዐይን የሚያስደስተውን፣ መዓዛው በጎ የሆነ የአበባ ጕንጕን ይዘው ያከብሩ ነበር፤ ከእህሉም ነዶውን እሸቱን ወደ ቤተ መቅደስ ወስደው ለሊቀ ካህናቱ ያቀርቡና ጸሎት ያስደርጉ፣ መሥዋዕት ያስቀርቡ፣ ቡራኬ ይቀበሉ ነበር፡፡ (ዘኁ.፳፰፥፳፮)
ይህን በዓል የሚያከብሩት ከግብፅ ወጥተው ባሕረ ኤርትራን በተሻገሩበት የሚያዝያ ወር ላይ የቂጣ በዓልን ባከበሩ በሃምሳኛው ቀን ነው፡፡ በሀገራቸው ክረምቱ አልፎ መጸው የተተካበት የአበባ፣ የእሸት፣ የፍሬ ወቅት በመሆኑ በዓላቸውን በዚያ ያደርጋሉ፡፡
በሀገራችን ደግሞ እሸት የሚደርስበት ወቅት ዘመነ መጸው ከገባበት ከመስከረም ፳፮ ቀን በኋላ በተለይም በወርኃ ጥቅምት በመሆኑ ወሩን መዋዕለ ሰዊት (የእሸት ወቅት) በማለት እንጠራዋለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!