ዘመነ ጽጌ

ካለፈው የቀጠለ

ዲያቆን ዘካርያስ ነገደ
መስከረም ፳፬፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከመስከረም ፳፮ ጀምሮ ያለው ጊዜ ዘመነ ጽጌ፣ ወርኃ ጽጌ እየተባለ ይጠራል፡፡ ጽጌ ማለት አበባ ማለት ሲሆን በእነዚህ ሰሞናት የሚዘመሩ መዝሙራት፣ የሚነበቡ ምንባባት ምድር በጽጌያት ማሸብረቁን የሚገልጡ ናቸው፡፡

መስከረም ፳፮ ቀን የዘመነ መጸው መጀመሪያ ቀን ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድም ይህንን ሲገልጥ “ኀለፈ ክረምት ቆመ በረከት ተሠርገወት ምድር በሥነ ጽጌያት ሎቱ ይደሉ ስብሐት ለአምላከ ምሕረት ኀለፈ ክረምት ወገብዓ ዝናም ድኅሬሁ ወአስተርአዩ ጽጌያተ ገዳም አዕደወ እክል ወበጽሐ ጊዜሁ ለማዕረር፡፡ ክረምት አለፈ፤ በረከት ተተካ፤ ምድር በአበቦች ውበት ተሸለመች፣ ተጌጠች፤ ለምሕረት አባት ለእርሱ ክብር ምስጋና ይገባል፤ ክረምት አለፈ፤ ዝናብም ወደ ኋላው ሄደ፤ የገዳማት አበቦች ታዩ ተገለጡ፤ የእህል እጆች የአዝመራ ጊዜው ደረሰ” በማለት ዘምሯል፡፡ (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)

ማጠቃለያ

ወርኃ መስከረም የዘመን መለወጫ ርእሰ ዐውደ ዓመት የሚከበርበት ቢሆንም እንኳ እንደ ቅዱስ ያሬድ አስተምህሮ ከላይ ከዘረዘርናቸው አግባብ ወሩ ተከፋፍሎ ልዩ ልዩ መታሰቢያዎች ይደረጉበታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በወሩ ውስጥ የሚከበሩ ልዩ ልዩ በዓላት በመጽሐፈ ስንክሳር የመስከረም ወር ንባብ ተዘርዝሯል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

መስከረም ፩ ጻድቁ ኢዮብ በፈሳሽ ውኃ ታጥቦ ከደዌው የተፈወሰበት፤ ሐዋርያው ታዴዎስ ሰማዕትነት የተቀበለበት፣

መስከረም ፪ ቅዱስ ዮሐንስ በሄሮድስ እጅ አንገቱ የተቆረጠበት፣

መስከረም ፯ የእመቤታችን ማርያም እናት ቅድስት ሐና የተወለደችበት፣ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እናት ቅድስት ኤልሳቤጥ ያረፈችበት፤

መስከረም ፰ የበራክዩ ልጅ ካህንና ነቢይ ዘካርያስ በሄሮድስ እጅ ሰማዕትነት የተቀበለበት፤

መስከረም ፲ ጼዴንያ በምትባል ሀገር ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ተአምር የተገለጠበት

መስከረም ፲፭ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋ የፈለሰበት

መስከረም ፲፯ በዓለ መስቀል

መስከረም ፲፰ የቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ዕረፍት

መስከረም ፳፩ የኒቅያ ጉባኤ የተካሄደበት

መስከረም ፳፭ ፀአተ ክረምት /የክረምት መውጣት/ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!