ሥርዓተ ጾም
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
መስከረም ፳፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? በአዲሱ ዓመት ከአሁኑ ጀምራችሁ መምህራን የሚነግሯችሁን በንቃት ሁናችሁ በመከታተል፣ ያልገባችሁን በመጠየቅ ትናንት ከነበራችሁ ዕውቀት ተጨማሪ ዕውቀትን ጥበብን ልትቀስሙ ያስፈልጋል! ልጆች! ቤተ ክርስቲያን በመሄድም መንፈሳዊውን ትምህርት በመማር በሥነ ምግባር ልትታነጹ ያስፈልጋል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አሁን ያለንበት ወቅት ወርኃ ጽጌ ይሰኛል፤ (የአበባ ወቅት ነው) በዚህ ወቅት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን አምላካችን ፈጣሪያችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ታቅፋ ሄሮድስ የተባለ ጨካኝ ንጉሥ ልጇን እንዳይገድልባት ወደ ግብጽ የተሰደደችበት ወቅት መታሰቢያ ነው፤ ወላጆቻችንን ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚያድሩ ከሆነ እኛም አብረናቸው በመሄድ በማኅሌቱ ሥርዓት መሳተፍ እንዳለብን እናስገነዝባለን! መልካም!!!
ባለፈው የትምህርት ጊዜ ስለ በዓላት አከባበር መማራችን ይታወሳል! አሁን ደግሞ ስለ ሥርዓተ ጾም እንማማራለን፤ ጾም ማለት ለተወሰነ ጊዜ ከምግብና ከውኃ እንዲሁም ከክፉ ሥራም መታቀብ (መከልከል) ነው፤ ጾም የጽድቅ በር ናት፤ ጾም ለመልካም ነገር የምታነሳሳን ናት፤ ጾም የቅዱሳን መላእክትን ኑሮ የምንለማመድባት ናት!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሰባት የዐዋጅ አጽዋማት አሉ፤ እነርሱም ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)፣ ጾመ ገሃድ (የጥምቀትና የልደት ዋዜማ የሚጾም)፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ነነዌ፣ ጾመ ድኅነት (ረቡዕና ዐርብ)፣ ጾመ ሐዋርያት (የሰኔ ጾም)፣ ጾመ ፍልሰታ ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህ አጽዋማት ዕድሜው ከሰባት ዓመት በላይ የሆነ ማንኛውም ክርስቲያን እንዳይጾም የሚከለክለው ሕመም ካልታመመ በስተቀር እነዚህን አጽዋማት ሊጾሟቸው ይገባል፤ እኛ ለመሆኑ ምን ያህሉን አጽዋማት እንጾም ይሆን?
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጾም የራሱ የሆነ ሥርዓት አለው፤ ስንጾም ጸሎትን መጸለይ አለብን፤ ስንጾም መከልከል ያለብን ከምግባና ከውኃ ብቻም አይደለም፤ ሰዎችን በማክበር፣ ከጓደኞቻችን ጋር ባለመጣላት፣ በአንደበታችን ክፉ ባለመናር መሆን አለበት፤ እነዚህን እና ሌሎችንም ምግባራት እየፈጸምን የምንጾም ከሆነ ሥርዓተ ጾሙን እየፈጸምን ነውና እግዚአብሔር የምንሻውን ነገር ያደርግልናል፤ ሌላው መገንዘብ ያለብን እስከ ስንት ሰዓት እንጹም የሚለው ነው፤ እንደ ሥርዓቱ ከሆነ ሥርዓተ ቅዳሴው እስኪፈጸም መጾም የሚገባ ሲሆን ትላልቅ አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድም እኅቶቻችን ከዚህም አትርፈው እስከ ምሽት የሚጾሙ አሉ፤ እኛ ግን ይህን ለማድረግ አቅማችን ስለማይፈቅድ እንዲሁም ሥርዓተ ጾሙን በደንብ መለማመድ ስላብን እንደ አቅማችን እንጾማለን፡፡
የመጾምን ሥርዓት እንዴት እንለማመድ?
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለመጾም እየፈለግን ስለሚደክመንና ቶሎ ስለሚርበን ለመጾም እንቸገራለን፤ ታዲያ ምን እናድርግ መሰላችሁ! በትንሽ እንጀምርና ቀስ በቀስ መጾምን መለማመድ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ምግብ ስንመገብ ብዙ ምግብ ቢኖርም በትንሹ በመብላት፣ ረቡዕና ዐርብ ደግሞ ቁርሳችንን ሳንመገብ እንደ የአቅማችን ለተወሰነ ሰዓት በመጾም የጾምን ሥርዓት መልመድ እንችላለን፤ ስንጾም የደከመን ቢመስልም እግዚአብሔር ግን ኃይልን ይሰጠናል፤ በሥጋችን ስንደክም መንፈሳችን ይጠነክራል፤ ምንም እንኳን ልጆች ብንሆንም ዕድሜያችን ግን ከሰባት ዓመት በላይ ከሆነ አቅማችን በፈቀደ ልንጾም ያስፈልጋል፤ በአጽዋማት ወቅት እንዳይበሉ የተከለከሉትን ባለመመገብ እንዴት እና ከምን መጾም እንዳለብን ልንለማመድ ይገባል፡፡
ለምን መሰላችሁ ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከልጅነታችን ጀምሮ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እየፈጸምን ካላደግን በኋላ ትልቅ ስንሆን ለመልመድ እንቸገራለን፤ መማር ያለብን፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም የሚገባን በልጅነት ዕድሜያችን መሆን አለበት፤ እስከ ዛሬ ሳናስተውል ቀርተን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰባት የዐዋጅ አጽዋማት የሻርን ከሆነ ከአሁን በኋላ ግን በአቅማችን ልክ በመጾም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንፈጽም፡፡
በልጅነታቸው በሥርዓት የኖሩ እግዚአብሔር የመረጣቸው በርካታ ቅዱሳን አሉ፤ እንደ ምሳሌ ብንወስድ ነቢዩ ሳሙኤል ገና ሕፃን ሳለ ነበር በቤተ መቅደስ በሥርዓት ያገለግል የነበረው፣ እምነቱን መስክሮ ከተጣለበት የፈላ ውኃ ቅዱስ ገብርኤል ከእናቱ ጋር ያዳናቸው የቅድስት ኢየሉጣ ልጅ ቅዱስ ቂርቆስ ሕፃን ነበር፡፡ አያችሁ! በልጅነትም መልካም ሠርቶ ለቅድስና ሕይወት መድረስም ይቻላል፤ ስለዚህ “እኔ ገና ልጅ ነኝ” እያልን ጸሎት ከመጸለይ፣ ጾም ከመጾም መስነፍ የለብንም፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ ለዛሬ በዚህ አበቃን፤ በቀጣይ ጊዜ እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ስለ ሥርዓተ ጸሎት እንማማራለን፤ አምላካችን ጾምን ጾመን በረከት የምናገኘኝበት ያድርግልን፤ በቸርነቱ ይጠብቀን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!