በዓለ ቅዱስ ሩፋኤል
ጳጉሜን ፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ጳጉሜን ሦስት ቀን የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል በዓል በየዓመቱ ይታሰባል፤ ይከበራልም፡፡ መልአኩ የጦቢትን ዓይን ያበራና ወለተ ራጉኤልን ተቆራኝቷት ከነበረው ጋኔን ያላቀቀ ነውና፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ከመላእክት አለቆች ሦስተኛ የሆነ ነው፡፡ ደግሞም ከእስክንድርያ ውጭ በደሴት የታነጸች ቤተ ክርስቲያን በከበሩ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን በውስጧ ተአምር የተገለጸበትና የከበረችበት ዕለት ነው፡፡ ይህም እንዲህ ነው፤ ሀብታም ሴት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ መጥታ ሳለ ከእርሷ ጋርም ብዙ ሰው ነበር፡፡ ከባሏም የወረሰችው ብዙ ገንዘብ አላት፡፡ በሊቀ ጳጳሳቱ ቤት አንጻር ያለውን ኮረብታ አስቆፈረችው። በጥምቅት ወር ዐሥራ ስምንት ቀን እንደጻፍን የወርቅ መዝገብ ተገለጠ፡፡
በዚያም ወርቅ ብዙዎች አብያተ ቤተ ክርስቲያናትን አነጸ፡፡ ከእርሳቸውም አንዲቱ የመላእክት አለቃ በሆነ በከበረ መልአክ ሩፋኤል በስሙ የታነጸች ይህች ናት፡፡ ሥራዋንም በፈጸመ ጊዜ እንደዛሬው በዚህች ቀን አከበራት፡፡ ብዙ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጸች፡፡ ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና፡፡ የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው፡፡ ወደ ክብር ባለቤት እግዚአብሔርም በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮሁ፡፡ ያን ጊዜም ያንን አንበሪ በጦሩ ወግቶ እንዲህ አለው፡፡ “እግዚአብሔር አዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጽ ጸጥ ብለህ ቁም፡፡” አንበሪውም ጸጥ ብሎ ቆመ፤ አልታወከም፤ በውስጧም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፤ ለሕሙማንም ፈውስ ሆነ፡፡ ይህችም ቤተ ክርስቲያን እስላሞች እስከተነሡበት ዘመን ኖረች፡፡ ከዚህም በኋላ ሁለተኛ ያ አንበሪ ተናወጸ፤ ደሴቲቱም በላይዋ ከሚኖሩ ብዙ ሕዝብ ጋር ሠጠመች፡፡
ዳግመኛም ቅዱስ ሩፋኤል ያደረገው ድንቅ ተአምር ይህ ነው፡፡ በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን መንግሥት የተማረከ ከነገደ ንፍታሌም የተወለደ አንድ እስራኤላዊ ነበር፤ ስሙም ጦቢት ነው፡፡ እግዚአብሔር በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ ሰጠው አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ለወገኖቹ ምጽዋት በመስጠት ሕገ ርትዕን በመሥራት የተጋ ሰው ነበር፡፡ ሐና ከምትባል ሚስቱም አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ ስልምናሶር ሞቶ ሰናክሬም በነገሠ ጊዜ ከሹመቱ ስለሻረው ደግሞ ወደ ምድያም መሄድ አልቻለም፡፡
አንዲት ሣራ የምትባል የራጉኤል ልጅ ሴትም በዚያን ጊዜ ከፍተኛ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ እርሷም ልጆች በመውለድ ቤት ንብረት ይዛ ለመኖር አስባ ባል አገባች፤ ነገር ግን በዚህች ሴት አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን አድሮ ያገባችውን ሰው ገደለባት፤ ሌላም ባል ብታገባ ሞተባት፤ እንደዚህ እየሆነ በጠቅላላ ሰባት ድረስ ያሉትን ባሎችን ገደለባት፡፡ የራጉኤል ልጅ ሣራ በዚህ ሁኔታ በኀዘን ተውጣ ስትኖር በነበረበት ጊዜ ጦቢት ሸምግሎ ነበር፤ ልጁ ጦብያንም ጠርቶ በዚህ ዓለም እስካለ ድረስ ሊሠራው የሚገባውን በጎና የጽድቅ ሥራ እንዲሠራ በጥብቅ ከመከረው በኋላ በመጨረሻ “ልጄ በሞትሁ ጊዜ በመልካሙ ቅበረኝ፤…ከአባቶችህ ዘር ሁሉ አስቀድመህ ሚስት አግባ፤ ከዘመዶችህ ካልሆነች ከባዕድ ወገን ግን አታግባ፤እኛ ከጥንት ጀምሮ ከነበሩ ከነቢያት፣ ከኖኅና ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ልጆች ወገን ነንና፤… በገባኤል ዘንድ አደራ ስላስጠበኩት ስለ ዐሥሩ የብር መክሊትም” ነገረው፡፡ (ጦቢ.፬፥፫-፲፪)
ጦብያም አባቱን መልሶ እንዲህ አለው፤ “አባቴ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤ ነገር ከማላውቀው ሰው ያን ብር መቀበል እንዴት ለማምጣት እችላለሁ?” አለው፡፡ በዚህም ጊዜ ጦቢት ልጁ ጦብያን “ከአንተ ጋር የሚሄድ ሰው እስኪ ፈልግ፤ እኔም በሕይወት ሳለሁ ደመወዙን እሰጠዋለሁ፤ ሄደህም ያን ብር ተቀበል” አለው፡፡ (ጦቢ.፭፥፩-፫)
ጦብያም አብሮት የሚሄደው ሰው ለመፈለግም ጀመረ፤ በመንገድም ሲጓዝ አንድ መልካምና ጐበዝ ሰው አገኘ፤ ይኸውም በሰው የተመሰለው መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ጦብያ ግን መልአኩ መሆኑን ፈጽሞ አላወቀም ነበር፡፡ ጦብያም መልአኩን “ሀገሩን ታውቅ ዘንድ ወደ ሜዶን ክፍል ወደ ራጌስ ከእኔ ጋር ለመሄድ ትችላለህን?” ሲል ጠየቀው፤ ቅዱስ ሩፋኤልም “ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ መንገዱንም ዐውቀዋለሁ፤ በገባኤልም ዘንድ ነበርሁ” ብሎ መለሰለት፡፡ (ጦቢ.፭፥፭-፮) ጦብያም “ለአባቴ እስክነግረው ድረስ ቆዩኝ” ካለው በኋላ ወደ አባቱ ጦቢት ሄዶ “ከእኔ ጋር የሚሄደው ሰው ይህ ነው” በማለት አስተዋወቀው፤ በኋላም ጦቢት ከወዴት እንደ መጣ፤ ማን ተብሎ እንደሚጠራ ጠየቀው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልም መልስ “እኔስ የወንድምህ የታላቁ አናንያ ዘመድ አዛርያ ነኝ” አለው፡፡ (ጦቢ.፭፥፲፪-፲፭) ጦቢትም የወንድሙ ዘመድ መሆኑን ከሰማ በኋላ ወንድሙ እንደሆነ አምኖ የልጁን የጦብያን ነገር አደራ በማለት ዋጋውንም እንደሚከፍለው ነግሮ ከስንቃቸውን አስይዞ ሸኛቸው፡፡
ቅዱስ ሩፋኤልም ጦብያን በመንገድ እየመራ ወሰደው፡፡ በዚህም ቅዱስ ሩፋኤል “መራኄ ፍኖት” (መንገድ መሪ) ይባላል፡፡ እነርሱ ሲጓዱ ውለው ማታ ጤግሮስ ከተባለው ታላቅ ወንዝ ደረሱና ከዚያም ለማደር ወሰኑ፡፡ ጦብያም ደክሞት ስለነበር ሊታጠብ ወደ ወንዙ ወረደና ልብሱን አውልቆ መታጠብ ሲጀምር አንድ ዓሣ ሊውጠው ከባሕር ወጣ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን “ያን ዓሣ ያዘው” በማለትም ነገረው፤ ጦቢያም ከዓሣው ጋር ግብ ግብ ገጥሞ እየጐተተ ወደ የብስ አወጣው፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን እንዲህ ሲል አዘዘው፡፡ “ዓሣውን እረደው፤ ልቡንና ጉበቱን፣ ሐሞቱንም ያዝ፤ አጥብቀህም ጠብቅ” አለው፡፡ (ጦቢ.፮፥፩-፬) ጦብያም መልአኩ እንዳዘዘው ዓሣውን አርዶ ሐሞቱንና ጉበቱን ያዘ፤ ሌላውን ሥጋውን ግን ጠብሰው ራታቸው በሉት፡፡ ጦብያም የዚያ ዓሣ ጉበትና ሐሞት ለምን እንደሚጠቅም ለማወቅ “አንተ ወንድሜ አዛሪያ! የዚህ ዓሣ ልቡ፣ጉበቱና ሐሞቱ ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው፤ ቅዱስ ሩፋኤልም “ልቡና ጉበቱ የሚያሳምም ክፉ ጋኔን ያደረበት ቢኖር ያን ለዚያ ሰው በፊቱ ያጤሱለታል፤ ሴትም ብትሆን ያጤሱላታል፤ ከዚያም በሃላ አይታመሙም፤ ሐሞቱን ግን በዐይኑ ላይ ብልዝ ያለበትን ሰው ይኩለታል፤ እርሱም ይድናል” በማለት መለሰለት፡፡ (ጦቢ.፮፥፭-፰)
ከዚህም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን “አንተ ወንድሜ! ዛሬ ከራጉኤል ቤት እናድራለን፡፡ እርሱም ዘመድህ ነው፡፡ አንዲት ልጅም አለችው፡፡ ስሟም ልጅ ሣራ ይባላል፡፡ ሚስት ትሆንህ ዘንድ እንዲሰጥህ ስለ እርስዋ እነግርልሃለሁ” አለው፡፡ ጦብያም “አንተ ወንድሜ አዛሪያ! ያቺን ልጅ ለሰባት ወንዶች እንዳገቧት እኔ ሰምቻለሁ፤ ሁሉም በሠርጉ ሞቱ፡፡ አሁንም እኔ ላባቴና ለእናቴ ብቸኛ ልጅ ነኝ፤ ወደ እርሷ በገባሁ ጊዜ እንዳልሞት የአባቴንና የእናቴን ሕይወት በእኔ ምክንያት በጭንቅ ወደ መቃብር እንዳላወርድ እፈራለሁ፤ የሚቀብራቸውም ሌላ ልጅ የላቸውምና” አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ግን “ከዘመዶችህ ሚስት ታገባ ዘንድ አባትህ ያዘዘህን ቃል አታስብምን? አሁንም አንተ ወንድሜ ስማኝ! የጋኔኑ ነገርስ አያሳዝንህ፤ በዚህች ሌሊት ከዘመዶችህ ወገን እርሷ ሚስት ሆና ትሰጥሃለችና፤ ወደ ጫጒላ ቤትም በገባህ ጊዜ የዕጣን ዕራሪ ውሰድ፤ ከዚህም በኋላ ከጉበቱና ከልቡ ጨምረህ አጢስበት፤ ጋኔኑም በሸተተው ጊዜ ይሸሻል፤ ለዘለዓለም አይመለስም፡፡ ወደ እርሷም በገባህ ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ጸልዩ! እርሱም ያድናችኋል፤ ይቅርም ይላችኋል፡፡ እንግዲህ አትፍራ፤ ከጥንት ጀምሮ እርሳን አዘጋጅተልሃልና፤ አንተም ታድናታለህ፤ እርሷም ከአንተ ጋር ትሄዳለች፤ ከእርሷም ልጆችን እንደምትወልድ እነግርሃለሁ” አለው፡፡ ጦብያም በዚህ ጊዜ በሰማ ደስ አለው፡፡ (ጦቢ.፮፥፲፫-፲፯)
ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱም ሣራ በደስታ ተቀበለቻቸው፤ የሣራ አባትም ጦብያን ገና እንዳየው ሚስቱ አድናን “ይህ ልጅ ድንቅ ነው፤ ከዘመዶች ወገን የሆነ ጦቢትን ይመስለዋል” አላት፤ ከዚያም ጋር አያይዞ “ወንድሞቻችን! እናንተ ከወዴት ናችሁ?› አላቸው፡፡ እነርሱም “ ወደ ነነዌ ከተማረኩት ከንፍታሌም ልጆች ነን” አሉት፡፡ ራጉኤልም “ ወንድሜ ጦቢትን ታውቁታላችሁን?› ሲል ጠየቃቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጦቢያ አባቱን ሲጠራለት “እናውቀዋለን” አሉት ጦቢያም “አባቴ ነው” አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ራጉኤል እቅፍ አድርጐ ሳመው፡፡ አድናም ሳመችውና ሁሉም ተያይዘው የናፍቆት ልቅሶ ተላቀሱ፤ ከወንድሙ እንደ መጡም ሲገነዘብ በግ አርዶ በጥሩ ሁኔታ ጋበዛቸው፡፡ (ጦቢ.፯፥፩-፰)
ራታቸውን ከተመገቡ በኋላ ጦብያ ቅዱስ ሩፋኤል በመንገድ የነገረውን እንዲያደርግለት ቅዱስ ሩፋኤልንም “ አንተ ወንድሜ አዛሪያ በጎዳና ያልከኝን ነገር ተናገር፤ ነገሩም ይለቅ” ሲለው ሰምቶ ስለ ልጅቷ መሆኑን ስለ ገባው ራጉኤል ጦብያን “አንድ ጊዜ ብላ፤ ጠጣ፤ ደስም ይበልህ፤ ልጄ ለአንተ ትገባለችና፤ አንተም ታገባሃታለህና” አለውና ሣራ ካለችበት የጫጉላ ቤት አግብተው ዘጉት፡፡ ጦብያም ሣራን “እኅቴ ተነሽ! እግዚአብሔር ይቅር ይለን ዘንድ እንጸልይ” አላትና አብረው ጸሎት ካደረጉ በኋላ ያንን የያዘውን የዓሣ ጉበትና ሐሞት ከዕጣን ጋር ጨምሮ ቢያጤስበት በሣራ አድሮ ባሎችዋን ይገድልባት የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ከሣራ ለቆ ወጥቶ ሄደ፤ ሁለተኛም ሊመለስ አልቻለም፡፡ እነርሱም በሰላምና በጤና አደሩ፡፡ የጦብያንና የሣራን ጋብቻ የባረከ ቅዱስ ሩፋኤል ስለሆነ “መልአከ ከብካብ” ይባላል፡፡ ከዚያ በኋላ የጤንነታቸውን ነገር ሲረዱ የሠርጉ ቀን የሚሆን የ፲፬ ቀን በዓል እስኪፈጸም ድረስ ጦብያ ወደ ሀገሬ እሄዳለሁ ብሎ እንዳያውከው በማለት አማለው፡፡ (ጦቢ.፰፥፬-፳) በዓሉም በተፈጸመ ጊዜ ጦብያ ከመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጋር ሚስቱን ይዞ ወደ አባቱና እናቱ ቤት ተመለሰ፡፡ እናቱ ሐናም በደስታ ሮጣ የልጅዋን አንገት ሳመችው፡፡ ጦቢትም ልጁ በሰለም መመለሱን ዐይቶ በደስታ ሊቀበለው ወጣ። ነገር ግን ዐይኖቹ ጠፍተው ነበርና ተሰነካከሎ ወደቀ። ጦቢትም አባቱን አንሥቶ የአባቱን ዐይኖች በዚያ ሐሞት መልአኩ እንደነገረው ኳለው፡፡ በካለውም ላይ ዐይኖቹን ባሸው ጊዜ ብልዙ ከዐይኑ ብሌን ተገፈፈለት፤ ልጁንም አየው፤ አንገቱን አቅፉ ሳመው፡፡ (ጦቢ.፲፥፮-፲፪)
ጦቢያም የድካሙን ዋጋ ገንዘብ ለመስጠት አዛሪያን አስጠራው፤ እርሱ ግን ጦቢትንና ጦብያን ለብቻቸው ወስዶ እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔርን አመስግኑት! ለእርሱም ተገዙ፤ ለስሙም ምስጋና አቅርቡ፤ ስላደረገላችሁም በጎ ነገር ሁሉ በሰው ፊት እመኑበት፤…እነሆ ነገሩን ሁሉ ከእናንተ አልሰውርም፡፡ የመንግሥትን ምሥጢር ሊሰውሩት የእግዚአብሔርን ሥራ ግን በክብር ሊገልጡት መልካም እንደሆነ እነግራችኋለሁ፡፡… የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ፣ በገናናው በቅዱሴ ጌትነት ፊት ከሚያቀርቡ ሰባቱ ቅዱሳን ሊቃነ መላእክት አንዱ መልአክ እኔ ሩፋኤል ነኝ” ሲል ገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ወድቀው የአክብሮት ስግደት ሰገዱለት፡፡ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፡፡ (ጦቢ.፲፪፥፩-፲፭)
የቅዱስ ሩፋኤል ምልጃው አይለየን፤ በረከቱም ይደርብን፤ አሜን!
ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ጳጉሜን እና መጽሐፈ ጦቢት