‹‹ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ›› (ማቴ. ፲፮፥፲፰)
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? የዓመቱ የትምህርት ወቅት እየተገባደደ የፈተና ጊዜ ደርሶ እየተፈተናችሁ ያላችሁ ተማሪዎች አላችሁና ፈተና እንዴት ነው? መቼም በደንብ እንዳጠናችሁ ተስፋችን እሙን ነው! ወደፊት መሆን የምትፈልጉትን ለመሆን በትምህርታችሁ ጎበዝ መሆን አለባችሁ!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በርትቶ የተማረና ያጠና በመጨረሻ በጥሩ ውጤት ከክፍል ወደ ክፍል ይዘዋወራል፤ አያችሁ ልጆች! በቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ የሚል ቃል አለ፤ ‹‹ጠቢብ ብትሆን ለራስህ ጠቢብ ትሆናለህ፤ ፌዘኛም ብትሆን ፌዘኝነትህን ለብቻህ ትሸከማለህ፡፡›› (ምሳ.፱፥፲፪) እንግዲህ በትምህርት ወቅት ጠቢብ ሆኖ መምህራን ሲዘሩት የነበረውን እውቀት በአግባቡ የቀሰመ ያጠና፣ ያልገባውን ጠይቆ በጥበብ የተረዳ ተማሪ የሥራውን ውጤት የሚያይበት ወቅት የዓመቱ መጨረሻ ነውና እናንተም በርትታችሁ አጥኑ! ፈተናውንም በማስተዋል ሥሩ!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አባቶች ምን ይላሉ መሰላችሁ፤ ‹‹ትምህርት በእርጅና ዘመን መጠለያ በመሆኑ በልጅነት ጊዜ መተከል ያለበት መሠረት ነው፡፡›› ታዲያ ይህን መሠረት በጥበብ በደንብ ልንገነባው ይገባል፡፡ መልካም !
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትርጉምና በመጀመሪያ ስለታነጸው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በጥቂቱ እንነግራችኋለን፤ መልካም ቆይታ! ቤተ ክርስቲያን ማለት ‹ቤት› ቤተ (አደረ) ካለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ማኅደርን፣ ወገንን፣ ማኅበርን ያመለክታል፤ ሌላው ልጆች ቤተ ክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች (የምእመናን) መሰብሰቢያ፣ የጸሎት ቤት፣ ሰውና እግዚአብሔር የሚገናኙበት ማለት ነው፤ ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ‹‹ቤተ ክርስቲያን›› የሚለው ቃል በሦስት ወገን ትርጉም አለው፡፡
፩.‹‹ቤተ ክርስቲያን›› ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ወንዶች፣ ሴቶች፣ ምእመናን በሙሉ አንድ ላይ ተሰባስበው ጸሎት የሚደርስበት፣ የጌታችን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም የሚፈተትበት ቅዱስ ቦታ /ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን/ ያመለክታል፡፡ ‹‹…በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን …›› እንዲል፤ (የሐዋ. ሥራ. ፳፥፳፰)
፪. ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ የዓለም መድኃኒት መሆኑን የሚያምኑ ሰዎች ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ይባላሉ፤ በክርስትና የክርስቶስ የሆኑ የክርስቲያን ወገኖችም ‹ቤተ ክርስቶስ› ይባላሉ፡፡ ‹‹..እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና…›› (፪ኛቆሮ. ፫፥፮) እንዲል፤ ‹‹የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ ወደ እርሱም እንመጣለን፤ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን፡፡›› (ዮሐ.፲፬፥፳፫)
፫. ሌላው ደግሞ ልጆች የክርስቲያኖች ማኅበር፣ የክርስቲያኖች ጉባኤ፣ የክርስቲያኖች ስብሰባ /አንድነት/ ቤተ ክርስቲያን ይባላል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ የምእመናንን ኅብረት (ስብስብ) ቤተ ክርስቲያን እያለ በመልእክቱ ጽፏል፤ ‹‹በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን ልጄ ማርቆስም ሰላምታ ያቀርብላችኋል..›› እንዲህ ማለቱ በባቢሎን ያሉ ምእመናንን (ክርስቲያኖች) ማለቱ ነው፡፡ (፩ኛጴጥ.፭፥፲፫)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ‹‹ቤተ ክርስቲያን›› የሚለውን ትርጉሙን በመጠኑ ተመለከትን፤ አሁን ደግሞ በመጀመሪያ ስለታነጸችው ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንመልከት! ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ቦታ በጌታችን፣ በእመቤታችን፣ በቅዱሳን መላእክት፣ በቅዱሳን ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ ስም ታንጸዋል፤ እነዚህ ሁሉ ግን በተለያየ ዘመንና ቦታ የታነጹ ሲሆኑ ከሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በፊት ግን የታነጸችው የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በፊልጵስዩስ ነው፤ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያትን ‹‹…ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማርችኋቸው፤ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው›› ብሎ እንዳዘዛቸው ቅዱሳን ሐዋርያት የምሥራቹን ወንጌል ለማስተማር በተለያየ የዓለማችን ክፍል ተጓዙ፡፡ (ማቴ. ፳፰፥፲፱)
ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ በርናባስም ፊልጵስዩስ በምትባል ከተማ ወንጌልን በሰበኩ ጊዜ ብዙ ሰዎች አመነው፤ ተጠመቁና ክርስቲያን ሆኑ፤ ከዚያም ለቅዱስ ጳውሎስ ምን አሉ መሰላችሁ? ‹‹በፊት የምንሄደው ወደ ጣዖት ቤት ነበር፤ አሁን እግዚአብሔርን አምነናል፤ ክርስቲያን ሆነናል፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን የምናመልክበት ቤተ ክርስቲያን ሥሩልን›› አሏቸው፤ ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን በተመለከተ መልእክት ለሐዋርያት አለቃ ለቅዱስ ጴጥሮስ ላከለት፤ ከዚያም ልጆች! ቅዱስ ጴጥሮስ ሁላቸው ጾም እንዲጾሙ ጸሎት እንዲጸልዩ አደረገ፤ ቅዱሳን ሐዋርያትም ጾሙ ጸለዩ፤ ከሱባኤው ፍጻሜ በኋላ ሰኔ ፳፩ ቀን ጌታችን ተገለጠላቸው፤ ሐዋርያትን ሁሉ ከያሉበት በፊልጵስዩስ ከተማ እንዲሰበሰቡ አደረገ፤ ከዚያም በተአምራት በሦስት ድንጋዮች በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ቤተ ክርስቲያን አነጸላቸው፤ በተሠራው ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ቅዳሴውን ቀድሶ ቅዱሳን ሐዋርያትን አቆረባቸው፤ ይህችንም ዕለት እንዲያከብሯት አዘዛቸው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሁሉን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር መልካም ነገር እንዲያደርግልን ስንለምነው ጸሎታችንን ይሰማል፤ ቅዱሳን ሐዋርያትን ምእመናን የጸሎት ቤት እንዲያዘጋጁላቸው ሲጠይቋቸው በጸሎትና በጾም ጠየቁ፤ ምላሽም ተሰጣቸው፡፡ ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን በተአምራት በእመቤታችንን ስም በመጀመሪያ ያነጻትን ቤተ ክርስቲያን መታሰቢያ በየዓመቱ ሰኔ ፳፩ ቀን ይከበራል:: እንግዲህ እኛም ወደ ቤተ ክርስቲያን በመምጣት አምላካችንን በጸሎት ልንማጸን ይገባል፤ ቤተ ክርስቲያን በጌታችን ደም የተቀደሰች ሥፍራ ናት፤ ወደ እርሷ ስንመጣ ንጽሕናችንን ጠብቀን፣ በፍርሃትና በትሕትና ሊሆን ይገባል፤ በውስጧ ስንመላለስ ሥርዓት አክብረን መሆንም አለበት!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጠኑ ይህን አልናችሁ፡፡ ‹‹በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡›› (፩ኛ ጢሞ. ፫፥፲፭) በቀጣይ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሦስት ክፍላት ማለትም ቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስት፣ መቅደስ አገልግሎት እንዲሁም ስለ ንዋያተ ቅዱሳት ምሥጢራዊ ትርጉም እንማማራለን፤ ይቆየን!!!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!