የቅዱሳንን ገድል የመማር አስፈላጊነት
መምህር ፈቃዱ ሣህሌ
ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
የቅዱሳንን ገድል ለምን እንደምንማር ለማወቅ ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተጠቀሱትን ታሪኮች ምሳሌ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በቃሉ የተናገረላቸው ቅዱሳን ስለመኖራቸው በቀዳሚነት መጽሐፍ ቅዱስ ተጠቃሽ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የሃይማኖታችን መመሪያ እንደመሆኑ መጠን በእርሱ የምንመራ ሰዎች ከቅዱሳን የቅድስና ሕይወት ትጋትና ታሪክ ልንማር እንደሚገባ የእግዚአብሔር ቃል ያስረዳናል፡፡ በቅዱሱ መጽሐፍ የተጻፉትን ታሪኮች የጻፉትም ሆነ የተጻፈላቸው ሰዎች ቅዱሳን ናቸው፡፡ ለምሳሌ በቅዱስ ጳውሎስ የዕብራውያን መልእክቱ ላይ ስናነብ እምነት ምን ማለት እንደሆነ ካስረዳን በኋላ ስለ ቅዱሳን ሕይወት ይነግረናል። መጽሐፍ ቅዱስም እነዚህ ቅዱሳን እምነትን በሕይወታቸው እንዴት እንደተረጎሙት ተጋድሏቸውን እና ድል መንሣታቸውን እንድንመለከት አድርጎናል፡፡ ከአቤል ታሪክ ጀምሮ እነ ሔኖክን፣ ኖኅን፣ አብርሃምን፣ እነ ሣራን እና ሌሎችንም ቅዱሳን እያነሣ ስለ ቅድስና ሕይወት ያስተምረናል፡፡
እግዚአብሔር እምላካችን ‹‹እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ›› በማለት እንደተናገረው ቅዱስ የመሆን ጸጋን የታደሉ እና የቅድስና ሕይወት ጥሪን በተግባር የተረጎሙ ቅዱሳን ለመሆን የተጋደሉና በእግዚአብሔር ኃይልና ረድኤት ለቅድስና የበቁ ለእኛ አርአያ ስለሆኑ ስለ ቅዱሳን እንማራለን፡፡ (ዘሌ.፲፩፥፵፬-፵፭)
የሃይማኖት ትርጉምም ከቅዱሳን የተሰጠንና የተቀበልነው ነው፡፡ ስለ ቅዱሳን ሳንማር ሃይማኖታችንን ገንዘብ ልናደርግ አንችልም፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት፣ ትውፊትና ምግባር የተማርነው ሁሉ በእነርሱ ሕይወት አማካኝነት ነው፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የመጀመሪያውን ክፍል ስንመለከለት የጻፈው ሊቀ ነቢያት ሙሴ ነው፡፡ አባቶቻችን እንደተናገሩት አንድን መጽሐፍ ከማንበባችን አስቀድሞ የጸሓፊውን የዕውቀት ደረጃ፣ ማዕረግና ቅድስና ማወቅ አለብን፡፡ ስለዚህም ኦሪት ዘፍጥረትን ለመረዳት ስለ ነቢዩ ሙሴ ማወቅ ይገባል፡፡ የሐዋርያትን ሥራ ከማንበባችን በፊት ጸሓፊው ቅዱስ ሉቃስ እንደሆነና ስለ እርሱ ታሪክ ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ መረዳትና ስለ ሃይማኖታችንም ማወቅ እንችላለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ልጆቹን ስለሚወድ በቅዱሳን አማካኝነት ሃይማኖት ወደ እኛ እንዲደርስ አድርጓል፡፡ በዚህም ስለ ቅዱሳን ማወቅና መማር የግድ እንደሆነ ልናውቅ ይገባል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ እንደተናገረው ‹‹ይህን በመጀመሪያ ዕወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፡፡›› ቅዱሳን በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተመርተውና ተቃኝተው የጻፉት እንደሆነ በዚህ እንረዳለን፡፡ (፪ኛጴጥ.፩፥፳)
እግዚአብሔር ሥራውን የሠራውና የሚሠራው አድሮ በቅዱሳን ነው፡፡ ዓለምን ለማዳን አስቀድሞ ትንቢትን በነቢያት አናግሯቸዋል፤ ከዚያም ብሥራትን በቅዱስ ገብርኤል አድርጓል፡፡ ከዚያም የሁሉም መድኃኒት በተገኘባት በንጽሕተ ንጹሓን ቅድስተ ቅዱሳን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የእርሱ ዕፁብ ድንቅ ሥራ ተገልጧል፡፡ ይህንም ቀጥሎም በቅዱሳን ሐዋርያት፣ በአርድእት፣ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ ይህ ከሆነ ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌን የአስተማሩን፣ ያስረዱንና ምሥጢሩን ያመሠጠሩልን ቅዱሳን ሊቃውንት መሆናቸውን አምነን ልንቀበል ይገባል፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር ላይ እንደተናገረው ‹‹እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው፡፡››(መዝ.፷፯፥፴፭)
እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ለማውጣት ነቢዩ ሙሴንና ሊቀ ካህናቱ አሮንን ተጠቅሟል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ለዕብራውያን በላከው መልእክቱ የተናገረው ይህንን ነው፡፡ ‹‹ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ›› እንዲል፤ (ዕብ.፩፥፩) በብዙ ኅብረ አምሳልና ኅብረ ትንቢት እግዚአብሔር ተናግሮ ድንቅ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡
ከቅዱሳን ጋር ቀጥተኛ ኅብረት እንዳለንም ልንረዳ ይገባል፡፡ ከእነርሱ ጋር ቤተሰብ ስለሆንና ማኅበር ስላለን ስለ እነርሱ ማወቅ ግዴታ አለብን፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ማኅበር ወይም ጉባኤ እንደምትባለው ማለት ነው፡፡ እርሷም በሰማይና በምድር አባሎች አሏት፡፡ በሰማይ በዐጸደ ነፍስ በገነት ቅዱሳን የሚኖሩ አሉ፤ ለምሳሌ እነ ኤልያስ እና ሔኖክ በብሔረ ሕያዋን ይኖራሉ፡፡ ከባቢሎን ሲመለሱ የገቡባት መካነ ዕረፍት ብሔረ ብጹዓን ነው፡፡ በዓለመ መላእክት ደግሞ ቅዱሳን መላእክት ይኖራሉ፡፡ (የዮሐንስ ምዕራፍ አንድምታ ትርጓሜ)
በምድር ላይ ያለነው በአጠቃላይ ገዳማውያኑ፣ ባሕታውያኑ፣ መነኰሳትም ሁላችን ሥጋ የለበስነው ሁሉ አንድ ሃይማኖት እስካለን ድረስ አንድ ማኅበር ነን፡፡ ስለዚህ ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ከአቡነ አረጋዊ፣ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ከቅዱሳን መላእክት ጋር አንድ ማኅበርተኞች ነን፡፡ በመሆኑም ማኅበርተኞቻችን ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ ‹‹እንግዲህስ ወዲህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም›› እንዲል፤ (ኤፌ.፪፥፲፱) ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን፣ ማኅበረ ጻድቃን፣ ማኅበረ ነቢያት፣ ማኅበረ ካህናት እንዲሁም ማኅበረ ሐዋርያት ዘርዝሮ ይነግረናል፡፡ (ዕብ.፲፪፥፳፪-፳፭)
በዚህም መሠረት ቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱሳን ስታስተምር ኖራለች፤ እያስተማረችም ነው፤ ወደፊትም ታስተምራለች፡፡ ይህም እግዚአብሔር መርጦ ያከበራቸውን ቅዱሳኑንና ቅዱሳቱን ልናውቃቸው፣ አርአያና ምሳሌ ልናደርጋቸው፣ ልንባረክባቸው፣ በቃል ኪዳናቸውም ልንማፀን ይገባል፡፡
የቅዱሳን አርአያነት በብዙ መልኩ ነው፤ በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ፈተናም ሆነ ጠላቶቻቸውን ድል የሚያደርጉት በእግዚአብሔር ኃይል ነው፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ዳዊት ጎልያድን ያሸነፈው አምላኩ በሰጠው ኃይል ነው፡፡ በቅዱስ ጴጥሮስ አድሮ እነ ሳኦልን እንዲሁም በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ አድሮ ናኦስን ድል አድርጓል፡፡ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ለማሳት ሰዎችን እንደሚጠቀመው ሁሉ ከዚያ የበለጠ ደግሞ እግዚአብሔር ሰዎችን ለማዳን ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን በቅዱሳኑ ምክንያት ሌሎች እንዲድኑ ያደርጋል፡፡
ስለሆነም እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቅዱሳን እንድንማር እና ወደ እነርሱ እንድንመለከት አዞናል፡፡ ለምሳሌ ለአቤሜሌክ በራእይ ተገልጾ ወደ አብርሃም ልኮታል፡፡ ለራሱ መዳኑን ማብሠር እየቻለ ወደ ሌሎች የላከበት ምክንያት አለው፡፡ ይህም ወደ ቅዱሳን ማየት እንዳለብን እንድረዳ፣ ቅዱሳንን እንድንማፀንና በቅዱሳን እንድባረክ ስለሚፈልግ ነው፡፡ ሊያስተምረን ሲፈልግ አቤሜሌክን ‹‹ነቢይ ነውና ይጸልይልሃል፤ አንተም ትድናለህ›› ብሎታል፡፡ (ዘፍ.፳፥፯) በጊዜው ለአቤሜሌክ የተነገረ ቢሆንም ትእዛዙ ለሁላችንም ነው፡፡ ወደ ቅዱሳን እንድንመለከት የነገረን በእነርሱ ጸሎት እንደሚሰማን ሲያስተምረን ነው፡፡ በቅዱሳን ጸሎት እንደሚሰማን በማመን ሀገራችንና ቤተ ክርስቲያናችን በተቸገረችበት በዚህ ከባድ ጊዜም ጭምር እነርሱን መማጸን ያስፈልጋል፡፡ በትንቢተ ኢሳይያስ ላይ ‹‹ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሳራ ተመልከቱ›› ብሏል፡፡ (ኢሳ.፶፩፥፪) ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ›› በማለት ተናግሯል፡፡ (፩ኛ ቆሮ.፲፩፥፩) ሐዋርያው ‹እኔን› ሲል ቅዱሳንን ወክሎ፣ እነርሱን እንድንመለከት እንዲሁም እንድከተላቸው ሲያስተምረን ነው፡፡ ‹‹እኔን ስትመስሉም ክርስቶስን ምሰሉ›› ማለቱ ደግሞ ቅዱሳንን መምሰል አምላካችንን መምሰል እንደሆነ ሲያስረዳን ነው፡፡ ስለዚህ ስለ ቅዱሳን የምንማረው ክርስቶስን ለመምሰል ነው፡፡ ቅዱሳንን አልፎ በአቋራጭ መንገድ ጌታችንን መምሰል ግን አይቻልም፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስም በመንገድ ተቀምጦ የነበረውን ሽባ ‹‹ወደ እኛ ተመልከት›› በማለት የተነናገረው በዓይነ ሥጋ ሳይሆን በዓይነ ልብ ሐዋርያቱን እንዲመለከት ነው፡፡ (ሐዋ.፫፥፬) እነርሱ በተሠጣቸው ሥልጣንና ጸጋ እንዲያምንም እየተናገረ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በጊዜው ለእርሱ ብቻ የነገረው ቢመስልም መልእክቱ ግን ለሁላችን ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ዋኖቻችሁን ተመልከቱ›› በማለት ተናግሯል፡፡ (ዕብ.፲፫፥፯) ዋኖቻችሁ የተባሉትም ቅዱሳን ናቸው፡፡ የእነርሱን ተጋድሎና የሃይማኖታቸውን ፍሬ ተመልክተን እንድመስላቸው ነግሮናል፡፡ ስለዚህ የጾምና የጸሎታቸውን ፍሬ ማወቅም ያስፈልጋል፡፡ ያንን ፍሬ ለመቋደስ የምንችለው ደግሞ እነርሱን ስንመስል ነው፡፡ በሃይማኖት፣ በምግባርና በትሩፋት ልንመስላቸው ይገባል፡፡ ይህንንም የምናደርገው አቅማችን እንደፈቀደ ነው፡፡ ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ›› ተብሎ እንደተነገረ በቅድስና ሕይወት መኖር ይቻላል፡፡ (ዘሌ.፲፱፥፪) ይህ በር ሁል ጊዜም ክፍት እንጂ ዝግ አይደለም፡፡ የቀደምት አባቶቻችንን ተጋድሎና ታሪክ እያደነቅን እኛም በዚያ ሕይወት የመኖር ፈቃድ ሊኖረን ይገባል፡፡ ሆኖም ግን በስንፍችን የተነሣ ልንወድቅ እንችላለን መጠንቀቅና መበርታት ያስፈልጋል፡፡ ምንም ፈተናና ችግር እንዲሁም ሥቃይ ቢበዛብን በቅድስና ሕይወት መኖር ተገቢ ነው፡፡
የክርስትና ሕይወት ዓላማው ደግሞ ወደ ቅድስና ሕይወት ማድረስ ነው፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ እንዴት መኖር እንደሚቻልና ወደ ቅድስና ደረጃ እንዴት እንደሚደረስ ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም አርአያ የሆኑንን ቅዱሳንን እንመለከታለን፡፡ በእንዴት ዓይነት ተጋድሎ ለቅድስና ሕይወት መብቃት እንደሚቻል እነርሱን አብነት ማድረግ አለብን፡፡ ብዙዎች ግን ወደ ቅድስና ሕይወት እንዴት እንደሚደረስ አያውቁም፡፡ ይህን ለማወቅ የቅዱሳንን ታሪክ ማንበብ አስፈላጊ ነው፡፡ ‹‹ቅድስናችሁን አትተው!›› እንደተባለው ስለዚህም ክርስትና ለራሱ ቅድስና ሕይወት በመሆኑ በሕይወት ውስጥ እስከ ፍጻሜ ልንኖር ይገባል፡፡ (ዕብ.፲፪፥፲፬) ክርስትናችንም ሆነ ሃይማኖታችንንን መጠበቅ ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ሃይማኖታችን ቅዱስ ነው፤ ቤተ ክርስቲያናችንም የተቀደሰች በመሆኗ ‹ቅድስት› ትባላላች፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም በአንደኛው መልእክቱ ‹‹እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ እንደተጻፈ እናንተም በአካሄዳችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ›› ብሏል፡፡ (፩ኛጴጥ.፩፥፲፭) ስለዚህ ቅዱስ ለመሆን ስለ ቅዱሳን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ስለ እነርሱም መማር የግድ ነው፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር ለእኛ ተጽፎ የሚነበብልን ለዚህ ነው፡፡
ከማንም በላይ ቅዱሳን ለእግዚአብሔር ቅርቦች በመሆናቸው የምሥጢሩ ተካፋይ ስለሆኑ ስለ እነርሱ ብንማር ስለ አማላጅነታቸውና ተራዳኢነታቸው አውቀንና ተረድተን እነርሱን ከመሰልን መዳን እንችላለን፡፡ በዚህ ምድር ላይ አንድን ንጉሥ ወይም መሪ ወይም ባለሥልጣን ለማነጋገር እርሱን የሚቀርበውን ባለሟሉን እንዲያናግርልን እንደምንጠይቅ ሁሉ ንጉሡም ወይም ባለሥልጣኑም ባለሟሉን አምኖ ከእኛ ይልቅ እንደሚቀበል እግዚአብሔርም ከእኛ ይልቅ ለእርሱ ቅርብ የሆኑትን ቅዱሳንን ይሰማል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም እንደሚመሠክሩት ለእርሱ ቅርብ የሆኑ ወዳጆቹን ቅዱሳንን እና ቅዱሳትን የበለጠ እንድናውቃቸውና እንዲረዱን ስለ እነርሱ እንማራለን፡፡ እነርሱም የእግዚአብሔር የምሥጢር መዝገቦች በመሆናቸው ሐሳቡንና ፈቃዱን ለዓለም የገለጠው በእነርሱ በኩል ነው፡፡
ለምሳሌ ኦሪት ዘፀአት ላይ ‹‹እግዚአብሔርም ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር›› ተብሎ ተጽፏል፡፡ (ዘፀ.፴፫፥፲፩) ይህ ነቢዩ ሙሴ ምን ያህል ከፈጣሪው ጋር ቅርበት እንዳለው ያሳያል፡፡ ‹‹ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ። ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው።…የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል›› ብሎ አምላካችን ተናግሯል፡፡ (ዘኁ.፲፪፥፮-፰) የእግዚአብሔር ፊት (መልኩን) እንዳየ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቧል፡፡ በዚያን ጊዜም እስራኤላውያን ኢትዮጵያዊቷን በማግባቱ ነቢዩ ሙሴን አምተውት ስለነበር (በአሁኑ ጊዜ ዘረኝነት እንድምንለው ማለት ነው) እግዚአብሔር ‹‹በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለ ምን አልፈራችሁም?›› በማለት ገሥጿቸዋል፡፡ (ዘኅ.፲፪፥፰)
ቅዱሳን በእግዚአብሔር ፊት የታመኑ እንደሆኑም በጻድቁ አባት በአብርሃም ታሪክ ውስጥ ታውቋል፤ ‹‹እግዚአብሔርም አለ እኔ የማደርገውን ከወዳጄ አብርሃም እሠውራለሁን?›› ብሎም በሰዶምና በገሞራ ላይ ሊያደርግ ያሰበውን ነገረው፡፡ የሕዝቡ ኃጢአት ስለበዛ ቢታገሣቸውም ስላልተመለሱ ሊፈርድባቸው እንደሆነም አሳወቀው፡፡ አምላክ ግን የነገረው እርሱ እንዲማጸንላቸው ነበር፡፡ ‹‹አብርሃምም ቀረበ አለም፥ አቤቱ ጻድቃንን ከኃጥአን ጋር አታጥፋ፤ ጻድቁ እንደ ኃጥኡ አይሁን፡፡ አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በውኑ ሁሉን ታጠፋለህን? ከተማዪቱንስ በእርስዋ ስለሚገኙ አምሳ ጻድቃን አትምርምን? አቤቱ ይህ ለአንተ አግባብ አይደለም፤ ይህን ነገር አታድርግ፤ ጻድቃንን ከኃጥአን ጋር አታጥፋ፤ ምድርን ሁሉ የምትገዛ ይህን ፍርድ ታደርግ ዘንድ ለአንተ አግባብ አይደለም፡፡ እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፤ በሰዶም ከተማ ውስጥ አምሳ ጻድቃን ባገኝ ከተማውን ሁሉ ስለ እነርሱ አድናለሁ።›› አብርሃምም መለሰ፤ አለም፤…ከእነዚያ አምሳ ጻድቃን አምስት ቢጐድሉ ከተማዪቱን ሁሉ በጐደሉት በአምስቱ ምክንያት ታጠፋለህን? እግዚአብሔርም፤ ከዚያ አርባ አምስት ባገኝ ስለ እነርሱ አላጠፋትም አለው። አብርሃምም አለው፤ ከዚያ አርባ ቢገኙሳ? እግዚአብሔርም ለአርባው ስል አላጠፋም አለው። ከዚያ ሠላሳ ቢገኙሳ? አለው። ደግሞም እነሆ፥ ከጌታዬ ከእግዚአብሔር ጋር እናገር ዘንድ ባለሟልነትን ካገኘሁ ከዚያ ሃያ ቢገኙሳ? አለው። እርሱም ከዚያ ሃያ ቢገኙ ስለ ሃያው አላጠፋም አለው። አብርሃምም አለው፤ አቤቱ እንደገና እናገር ዘንድ ጌታዬ ፍቀድልኝ፤ ከዚያ ዐሥር ቢገኙሳ? አለው። እርሱም ስለ ዐሥሩ አላጠፋትም አለው።›› (ዘፍ.፲፰፥፳፫-፴፪) አስቀድሞ ነቢዩ ሙሴም ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር እንዳያጠፋና ለሕዝቡ እንደለመነ እናነባለን፤ እግዚአብሔርም ልመናውን ተቀብሎታል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለሰው የምናደርገውን መልካም ሥራ ሁሉ ለራሱ እንዳደረግነው እንደሚቆጥረው ልናውቅ ይገባል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እውነት እላችኋለሁ ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት፣ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው’ ይላቸዋል›› በማለት ተናግራል፡፡ (ማቴ.፳፭፥፵) በዳግም ምጽአቱ ለፍርድ በግራ የሚያቆማቸውን ኃጥኣንን ‹‹ጌታ ሆይ፤ ተርበህ ወይም ተጠምተህ፣ እንግዳ ሆነህ ወይም ታርዘህ፣ ታመህ ወይም ታስረህ ዐይተን መቼ አልደረስንልህም’?›› ብለው ሲጠይቁት አንድ የተራበውን ሰው ያለማብላት እርሱን አለማብላት፣ የታረዘውን አለማልበስ እርሱን አለማልበስ፣ የታመመውን አለመጎብኘት እርሱን አለመጎብኘት እንደሆነ ይነግራቸዋል፡፡ በቀኙ የቆሙትም ‹‹ጻድቃንም መልሰው እንዲህ ይሉታል፤ ‘ጌታ ሆይ፤ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ወይም ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ?›› ብለው በሚጠይቁት ጊዜ ለአንዱ ያደረጉት ለእርሱ ማድረግ እንደሆነ ይነግራቸዋል፡፡ (ማቴ.፳፭፥፵-፵፭) ስለዚህ ለምስኪኖች የሚደረገው ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር እንደሚደረግ በማመን ለቅዱሳን የሚገባውን የጸጋ ክብር፣ ስግደትና ምስጋና እናቀርባለን፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ በስሙም ያሳያችሁን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዐመፀኛ አይደለም›› እንዲል (ዕብ.፮፥፲) በምድር ላይ ያሉትን ቅዱሳንንና በዐጸደ በነፍስም ያሉትን ስማቸውን መጥራት፣ መታሰቢያቸውን ማድረግ፣ መማጸን፣ ማገልገል፣ ቤታቸውን መሥራት ይገባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ያደረግን እንደሆነ እግዚአብሔር እንደማይረሳና ለእነርሱ ባደረግነው ነገር አምላካችን ዋጋ እንደሚከፍለን ነግሮናል፡፡
የምንማረውን በመተግበር ለመባረክ የቅዱሳንን ታሪክን ምሳሌ እንዳርጋለን፡፡ እነርሱን ባወቅን በተረዳን ባከበርን ቁጥር ስለ ድኅነትና ስለ በረከት እናውቃለን፡፡ ለምሳሌ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ አባት ቆመው ሲያስተምሩ እርሱ ሊባርክ በመካከል ይገኛል፡፡ ስሙን ከፍ ከፍ የሚያደርጉትንና ስለ እርሱ የሚዘምሩትን ሊባርክ ይመጣል፡፡ ሌላውም ቅዱስ እንደዚያ ነው፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ሲነሣ እና ተአምሯ ሲነበብ እርሷ ልትባርክ ትመጣለች፡፡ የቅዱሳን ስም ሲጠራም ሆነ መታሰቢቸወ ሲደረግ እኛ እንባረካለን ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ‹‹ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ እባርክሃለሁ፤ ስምህንም ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፤ ቡሩክም ትሆናለህ፤ የሚባርኩህን እባርካለሁ፤ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ›› ብሎ የተናገረው ለጻድቁ አብርሃም ብቻ አይደለም፡፡ ለቅዱሳኑ ሁሉ የተሰጠ ቃል ኪዳን ነው እንጂ፡፡ (ዘፍ.፲፪፥፪-፬)
በመጽሐፈ ምሳሌም ላይ ‹‹የእግዚአብሔር በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ነው›› ተብሏል፡፡ በረከቱን በእነርሱ ራስ ላይ እንዳኖረው በዚህ እንረዳለን፡፡ እነርሱን በመማጸንና በማክበር በረከት እናገኛለን፡፡ ‹‹በጻድቃን ደግነት ከተማ ትቀናለች፤….. በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች›› እንዲል፤ (ምሳ.፲፥፮፣፲፩፥፲-፲፪)
በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ያዕቆብ እንዲህ ተብሎለታል፤ ‹‹በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፤ እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ አትፍራ፤ እኔ ካንተ ጋር ነኝና እባርክሃለሁ፤ስለ አባትህ ስለ አብርሃም ዘርህን አበዛዋለሁ፡፡›› (ዘፍ.፳፮፥፳፬)
ለቅዱሳን የተገባላቸው ቃል ኪዳን መታሰቢያቸው ለሚያደርጉ ሰዎች ይፈጸምላቸዋል፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የተገባላቸው ቃል ኪዳን ክብረ በዓላቸው በሚከበርበትና ዝክራቸው እንዲሁም መታሰቢያቸው በሚደረግበት ዕለት በረከታቸው ለሰዎች ይደርሳል፤ ቃል ኪደናቸው ይፈጸማል ማለት ነው፡፡ ሰው ይደረግልኛል ብሎ አምኖ በቅዱሳን ስም ሲዘክር በቅዱሳን ምልጃና በረከት ክብርን ያገኛል፡፡ እስራኤላውን የተስፋይቱን ምድር የወረሱት በአባታቸው በአብርሃም፣ በይስሐቅና በያዕቆብ በተገባላቸው ቃል ኪዳን ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ ‹‹አምላካቸወ ተብሎ ይጠራ ዘንድ አያፍርም›› በማለት ተናግሯል፤ (ዕብ.፲፩፥፲፮)ስለዚህም ከእነዚህ ቅዱሳን ታሪክ ተምረንና እነርሱን ተከትለን ወደ ተስፋይቱ ምድር መንግሥት ሰማያት ለመግባት መትጋት አለብን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!