በዓሉ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል
ኅዳር ፲ ቀን፤ ፳፻፲፬ ዓ.ም
በኅዳር ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ቤተ ክርስቲያናችን የታላቁ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡አምላካችን እግዚአብሔር ሳጥናኤልን በትዕቢቱ ምክንያት ከሥልጣኑ አውርዶ ወደ ምድር ሲጥለው ቅዱስ ሚካኤል በእርሱ ቦታ በዐሥሩ ከተማ በመቶውም ነገደ መላእክት ላይ ተሹሟል፡፡
የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ ግን አይደለም ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይም ጭምር ነው፡፡ ይህም እንደሆነ እንድንረዳ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባለውን እስራኤል ዘሥጋን ሲራዳና ሲጠብቅ እንደነበረ ተጽፎልን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለኢያሱ በኢያሪኮ ምድረ በዳ እንደተገለጠለት ‹‹… ዐይኑን አንሥቶ ተመለከተ፤ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ ሰው በፊቱ ቆመ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ፤ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ? አለው፡፡ እርሱም “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁንም ወደ አንተ መጥቼአለሁ›› ይለናል፡፡ (ኢያ.፭፥፲፫)
እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ነፃ ሲያወጣቸው ይመራቸው የነበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነበር፡፡ ሹመቱ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይም በመሆኑ ስለ እነርሱ ዲያብሎስ ይዋጋው፣ በጸሎትም ረድቷቸዋል፡፡ ነገር ግን ኃጢአት ሠርተው ሲያገኛቸው ለእግዚአብሔር አድልቶ ኃጢአተኞችን ስለሚቀጣ እግዚአብሔር ሕዝቡን “በፊቱ ተጠንቀቁ! ቃሉንም አድምጡ፤ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት” ብሎ አስጠንቅቋቸው ነበር፡፡ ይህም ቅዱስ ሚካኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሾሙን ያስረዳናል፡፡ ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ሕዝበ እስራኤልን ይራዳቸው የነበረው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ አያረጋግጥም የሚል ካለ ‹መልአክ› የተባለው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ነቢዩ ዳንኤል በተላከ ጊዜ ገልጦልን እናገኛለን፡- ቅዱስ ገብርኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ቅዱስ ሚካኤል ስለመሾሙ ሲመሰክር ‹‹በእውነት በመጽሐፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር የሚረዳኝ ማንም የለም›› ብሏል፡፡ ስለዚህም ለኢያሱ የተገለጠውና እስራኤላውያንንም የመራው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን እንረዳለን፡፡ (ዘፀ.፳፫፥፳፩፣ዳን.፲፥፳፩)
የቅዱስ ሚካኤል አለቅነት በሐዲስ ኪዳንም አንደሚቀጥል ይህ ነቢይ በትንቢቱ ‹‹በዚያ ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ ሚካኤል ይነሣል..›› በማለት ተናግሮለታል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ሚካኤል እኛን ከሰይጣን አሽክላና ወጥመድ ይጠብቀንና በጸሎቱ በእግዚአብሔር ፊት ይቆምልን ዘንድ በእኛም ላይ ሹም ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ የእግዚአብሔር ሕዝቦችና የርስቱ ወራሾች ነንና፡፡ (ዳን.፲፪፥፩)
እግዚአብሔር ነቢዩ ሙሴን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መሾሙ እጅግ ትሑትና ስለመንጎቹን ነፍሱን እንኳ አሳልፎ እስከመስጠት ደርሶ ስለሚወዳቸው ነበር፡፡ (ዘኁ.፲፪፥፫፣ዘፀ.፴፪፥፴፪) በሕዝቡም ላይ እርሱን መሾሙ እንዲሠለጥንባቸው ወይም እንዲገዛቸው ሳይሆን በትምህርቱና በጸሎቱ እነርሱን እንዲቤዣቸው ነው፡፡ እንዲህም ስለሆነ ቅዱስ እስጢፋኖስ ስለሙሴ ሲመሰክር ‹‹እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው›› አለ፡፡ (የሐዋ.፯፥፴፭) እንዲሁ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል እጅግ ትሑትና ለሠራዊቱ ተቆርቋሪ የሆነ መልአክ በመሆኑ በመላእክትና በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ተሾመ፡፡ በመላእክትና በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሾሙ ልክ እንደ ሙሴ በእነርሱ ላይ ሊሠለጥንባቸው ወይም ሊገዛቸው ሳይሆን መላእክትን ሊመራ፣ እኛን ደግሞ ከሰይጣን ጥቃት ሊጠብቀንና በጸሎቱ ሊራዳን ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱሳን መላእክት እኛን እንደሚጠብቁና እንደሚራዱ እንዲሁም ስለእኛ በፊቱ አንደሚቆሙ ሲያስተምረን ‹‹ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ስንኳ እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ሁል ጊዜ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁ›› ብሎናል፡፡ (ማቴ.፲፰፥፲) እኛን ይጠብቁ ዘንድ የተሰጡን ቅዱሳን መላእክት ስለእኛ እንዲህ የሚቆረቆሩና ስለመዳናችን የሚተጉ ከሆነ በቅድስናው ልቆ የመላእክት አለቃ ሆኖ የተሾመው ቅዱስ ሚካኤል እንዴት ስለእኛ በእግዚአብሔር ፊት ይበልጥ አይቆም? (ሉቃ.፲፫፥፮-፱) እንዴትስ በተሰጠው ሥልጣንና ኃይል አይረዳን? (መዝ.፴፫፥፪) እርሱ ‹‹ስለሕዝብህ ልጆች የሚቆመው›› መባሉም እኛን በጸሎቱና በተራዳኢነቱ የጽድቅ ሕይወታችንን በሚገባ እንድናከናውን እንደሚራዳን የሚያሳይ ኃይለ ቃል ነው፡፡
የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤል ጸሎቱና በረከቱ በእኛ ላይ ለዘለዓለሙ ይደርብን፤ አሜን፡፡