‹‹እግዚአብሔርም የፈጠረው ሁሉ እጅግ ያማረ እንደሆነ ተመለከተ›› (ዘፍ.፩፥፴፩)
መምህር ዐቢይ ሙሉቀን
መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
በባሕርዩ ክቡር የሆነው እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ ክቡር ነው። ይሁን እንጂ አበው በብሂላቸው ‹‹ከጣትም ጣት ይበልጣል›› እንዲሉ እጅግ የከበሩ ፍጥረታትም አሉ። ከእነዚህ እጅግ የከበሩ ፍጥረታት ከሚባሉት መካከል በቀዳሚነት የሚገኘው የሰው ልጅ ነው። ስለዚህ የሥነ ፍጥረትን ታሪክ የጻፈልን ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሁሉንም ፍጥረታት ከፈጠረ በኋላ ‹‹መልካም እንደሆነ አየ›› እያለን ይመጣና ሰው ላይ ሲደርስ ግን ‹‹እጅግ መልካም እንደሆነ አየ›› በማለት ይደመድማል። ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ‹‹ሰንበት ተዐቢ እምኵሉ ዕለት ወሰብእ ይከብር እምኵሉ ፍጥረት፤ ከዕለታት ሰንበት ትበልጣለች፤ ከፍጥረታትም ሁሉ ሰው ይበልጣል›› በማለት እንደነገረን የሰውን ልጅ እጅግ ክቡር ፍጥረት መሆኑን ያስረዳናል። የሰው ልጅ ክቡርነት በተመለከተ መጻሕፍት አምልተውና አስፍተው ይናገራሉ። (ዘፍ.፩፥፴፩)
ቀሌምንጦስ የተባለው የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ደቀ መዝሙር እንደሚከተለው ገልጾታል።
እግዚአብሔር አብ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ በአርአያችንና በአምሳላችን ሰውን እንፍጠር አላቸው። መላእክት ይህን ከልዑል እግዚአብሔር በሰሙ ጊዜ በላያቸው ላይ ከባድ ፍርሃትና ድንጋጤ አደረባቸው። በየራሳቸውም ‹ይህ ትልቅ አስደናቂ ተአምር የምንሰማው ምንድር ነው? የፈጣሪያችንና የአምላካችንን አርአያና አምሳልንስ ማየት እንዴት ይቻለናል?› ተባባሉ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር ቀኝ በምድር ላይ ተዘረጋች። ዓለም በመላ በእግዚአብሔር መዳፍ ላይ ሁና ለመላእክት ሁሉ ታየቻቸው። እግዚአብሔር አባታችን አዳምን ከእነዚያ አራቱ ደካማዎች ፈጠረው። አራቱ ኀይል የሌላቸው ናቸው። ይህን ያደረገው ፍጥረት ሁሉ እንዲታዘዙለት ነው። መሬት፡- ሰው ሁሉ እንዲታዘዝለት፤ ውኃ፡- በውኃ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሁሉ እንዲታዘዙለት፤ ነፋስ፡- የሚነፍሰውን ሁሉ ለማሽተት ይቻል ዘንድ፤ እሳት፡- በዋዕይ እንዲጠነክርና የሚረዳውን ኃይል እንዲያገኝ። ስለዚህ እግዚአብሔር ልዑል አባታችን አዳምን በተቀደሰች እጁ በአርአያውና በምሳሌው አድርጎ ፈጠረው። ይህንም ያደረገበት ምክንያት አዳም ጥበብን፣ ነባቢነትንና ዕውቀትን እንዲቀበል ነው። (ቀሌ. ፩፥፴፫-፴፯)
የሰው ልጅ እጅግ የከበረ መሆኑን ሌላ ምንም ማብራሪያ ሳያስፈልግ ከላይ የተጠቀሰውን ምንባብ ብቻ በማንበብ መረዳት ይቻላል። ሊቀ ነቢያት ሙሴም የሥነ ፍጥረትን ታሪክ በጻፈበት ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔርም አለ ሰውን በአርአያችንና በአምሳላችን እንፍጠር የባሕር ዓሣዎችንና የምድር አራዊትን የሰማይ ወፎችን እንስሳትንና ምድርን ሁሉ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ይግዛ። እግዚአብሔርም ሰውን በእግዚአብሔር አምሳል ፈጠረው›› በማለት ሰው በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረና ክቡር ፍጥረት መሆኑን አስረድቶናል። (ዘፍ.፩፥፳፮-፳፯)
የሰው ልጅ ክቡር ሆኖ መፈጠር ብቻ ሳይሆን የፍጥረታት ሁሉ ገዥ ሆኖ የተፈጠረ ነው። በመሆኑም የእግዚአብሔርን ሕግ ከማፍረሱ በፊት እንስሳት አራዊት ሁሉ ይገዙለት የነበረ፣ ከመላእክቱ ጋር እግዚአብሔርን እያመሰገነ የሚኖር በልጅነት ላይ ሀብተ ክህነቱን፣ ሀብተ ምስፍናውን፣ ሀብተ ትንቢቱን ወዘተ ያደለው ታላቅ ፍጥረት ነበር። ብዙ ነገር ተፈቅዶለት ሳለ አንድ ነገር ላይ ባለመታመኑ የተሰጠውን ሁሉ አጣ፤ ጠላት በዛበት፤ ቀድሞ በእባብ ላይ አድሮ ከእግዚአብሔር ያጣላው ጠላት ዲያብሎስ በብዙ መንገድ መከራውን አበዛበት።
ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ በቃየል ገዳይነት በአቤል ሟችነት ያስጀመረውን ክፉ ምግባር አጠናክሮ የሰውን ልጅ በራሱ በሰው ልጅ እያገዳደለ እስከ ዛሬ ቀጥሏል። እግዚአብሔር አምላካችን በነቢዩ በሆሴዕ ላይ አድሮ ‹‹ሕዝቤ ዕውቀትን በማጣት ጠፍቷል›› በማለት እንደተናገረው የሰውን ልጅ ተፈጥሮ ባለመረዳት አንዱን አንዱ ሲገድለው እናስተውላለን። ምንም እንኳን የአገዳደል ጥሩ ባይኖረውም ለአእምሮ በሚዘገንን ሁኔታ ሲገደሉ እያስተዋልን ነው። በሻሸመኔ፣ በጅግጅጋ፣ በጉራ ፈርዳ በትግራይ፣ በማይካድራ፣ በቤንሻጉል ጉምዝ ወዘተ የሚስተዋለው ግፍ የተሞላበት የሰዎች ግድያ የገዳዩን አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን የሰይጣን ማደሪያ መሆኑን የምናስተውልበት ነው። (ሆሴ. ፬፥፮)
እንደዚህ ያለውን የግፍ ግፍ በተመለከተ እግዚአብሔር አምላካችን በነቢዩ በሕዝቅኤል ላይ አድሮ ‹‹የሕዝቤን ነፍስ ታጠምዳላችሁ፤ በእውኑ እናንተ ነፍሳችሁን ታድናላችሁን? ከንቱ ነገርን ለሚሰሙት ሕዝቤ እየዋሻችሁ ሞት የማይገባቸውን ነፍሳት ትገድሉ ዘንድ በሕይወትም መኖር የማይገባቸውን በሕይወት ታኖሩ ዘንድ ስለ ጭብጥ ገብስና ስለ ቍራሽ እንጀራ ሕዝቤን አርክሳችኋል›› በማለት እንደተናገረ ለሕዝቡ የተቆረቆሩ እየመሰላቸው በሐሰት ወሬ ታሪክ እየጻፉ፣ እርስ በእርሱ እንዲጋደል ያደረጉትንም በዚህ መልኩ ይወቅሳቸዋል። (ሕዝ.፲፫፥፲፰-፲፱)
እንደዚህ ያለውን ክፉ ምግባር መንግሥትም እንደ መንግሥት ድርሻውን በመውሰድ፣ ቤተ ክርስቲያንም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በስፋት በማስተማር፣ ራሱ ሕዝቡም እርስ በእርስ በመገዳደል የሚያገኘው ትርፍ እንደሌለ በመረዳት ከምንም በላይ ሰላም ይበልጣልና በሰላም መኖርን መምረጥና ሰላም የሚሰፍንበትን መንገድ መከተል ይኖርበታል።
ማንም ሰው ሰው ሲገድል እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ በጥንተ ተፈጥሮ በአርአያው ፈጥሮ በልጅነት ያከበረው በኋላም ደሙን ያፈሰሰለት ሥጋውን የቆረሰለት ክቡር ፍጥረት ነውና የሚያደርገውን ሁሉ ክፉ ምግባር በእግዚአብሔር ላይ እንዳደረገ መረዳት ይኖርበታል። እንዲህ የሚያደርጉትን ደግሞ ብርሃነ ዓለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚያፈርሰውን ግን እርሱን ደግሞ እግዚአብሔር ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነውና›› በማለት የማይገባ ተግባር እንደሆነ ይናገራል። ስለዚህ እንደዚህ ያሉት ሰዎች ከክፉ ምግባራቸው ሊመለሱ ይገባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ከላይም እንደተገለጸው የሐሳብ ልዩነትንም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ በመወያየት መፍታት እንጂ ወደ ግድያ መሄድ እንደሌለበት መገንዘብ ያስፈልጋል። ለዚህ ሁሉ ግን ሁሉም ማለትም ከመንግሥት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንም ምእመናንም የየድርሻችንን በመወጣት ለሰው ልጅ የሚገባው ሰላምና መልካም የሆነው ነገር እንዲሰፍን ማድረግ ይኖርብናል። (፩ቆሮ ፫፥፲፯)
የሰላም አምላክ በሰላም ኖረን፣ በተረጋጋ መንፈስ እግዚአብሔርን አገልግለን፣ በጎ ምግባር ሠርተን በሚያልፈው ዓለም ብቻ ሳይሆን በማያልፈው ዓለም ከቅዱሳኑ ጋር ሕያዋንና ዘለዓለማውያን ሆነን እንድንኖር ይፍቀድልን፤ አሜን።