‹‹የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ›› (ዮሐ.፪፥፲፮)
መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
በኢየሩሳሌም፤ ምኵራብ ተብሎ በተሰየመው የዐቢይ ጾም ሦስተኛው ሳምንት ዕለተ እሑድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ አይሁድ ንጉሥ ናቡከደነፆር ቤተ መቅደስን ካፈረሰባቸው በኋላ ሕገ ኦሪትን መማሪያ እና መጸለያ ስፍራ በማጣታቸው የሠሩት አዳራሽ ምኵራብ ነበርና፡፡ በዚያም ጌታችን በሬዎችንና በጎችን፥ ርግቦችንም የሚሸጡትን፥ ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው ባገኘ ጊዜ ያየውን ባለመውደዱ የገመድ ጅራፍ ካዘጋጀ በኋላ በጎችንና በሮዎችን እንዲሁም ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣቸው፤ የሻጮቹንም ገንዘብ በተነባቸው፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፤ ርግብ ይሸጡ የነበሩትን ደግሞ፤ ‹‹ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ አላቸው፡፡›› (ዮሐ.፪፥፲፬-፲፮)
ጌታችንም በአይሁድ ምኵራብ ገብቶ የተሰበሰቡትን ሰዎች እንዲህ ብሎ አስተማራችው፡፡ ‹‹ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን እወዳለሁ፤ የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው፡፡ ያባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል፡፡›› (ጾመ ድጓ)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራብ ያስተማረው ትምህርት የእግዚአብሔር ቤት በሆነቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጸሎት መጸለይ እና ምጽዋትን ማቅረብ እንጂ የተለያዩ የንግድ ሥራ የሚሠራበት ወይም ሸቀጣ ሸቀጦች የሚሸጡበት እንዳልሆነ የሚያስረዳ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ቅጥረ ግቢም ሆነ በአቅራቢያዋ ንዋያተ ቅዱሳት እና ምጽዋት ከሚመጸወቱባቸው መገልገያዎች ውጪ ምንም ዓይነት ቊሳዊ ነገር መሬት ላይ አስቀምጠን ልንነግድ አይገባም፡፡ ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያን የምንተገብራቸው ምግባራት ሁሉ ከነፍሳችን ጋር የተያያዙ እና ለነፍሳችን ብቻ የሚጠቀሙ መሆን አለባቸው፡፡ ‹‹የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ፡፡ ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛዋ ቀን ግን የእግዚአብሔር የአምላክህ ሰንበት ናት›› የተባለውም ኃይለ ቃል ስለዚህም እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቅጥረ ጊቢ ላይ መነገድ ይቅርና በሌሎች ሥፍራዎች ወይም በሥራ ቦታዎቻችን በተለይ በሰንበት ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት አይቻልም የተባለበት ምክንያትም የቤተ ክርስቲያንን ቅድስናንም ለመግለጽ ነው፤ ወደ ቤተ መቅደስም ስንገባ የምንይዛቸውም ሆነ የምንተገብራቸው ምግባሮች ሁሉ ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውሉ መሆን አለባቸው እንጂ ምንም ዓይነት ንግድ መፈጸም አይቻልም፤ ስለሆነም ይህን በመረዳት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተገቢውን ክብር መስጠት ይገባል፡፡ (ዘፀ. ፳፥፰)
በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ቅጥረ ጊቢ ግን በተለይ በአሁኑ ጊዜ ነጋዴዎች እና አንዳንድ ሸቀጣ ሸቀጥ አዟሪዎች ንግድ ያካሂዳሉ፡፡ ይህ ተግባር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጸሎት ቤት ያላትን የቤተ ክርስቲያን ክብር የሚያጎድል በመሆኑ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሁሉ ከዚህ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደሪዎችና አገልጋዮች ይህን የቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚያጎድል ድርጊት በመንቀፍ ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም የሚያችለውን ርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም በሰንበታት ብዙኃኑ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዳቸውን ሰበብ በማድረግ ንግድን የሚያካሂዱትን ግለሰቦች ማስቆም አለባቸው፡፡ በዚህ በጀመርነው በዐቢይ ጾምም ዕለታቱን በሙሉ በማክበር ጌታችን በምኵራብ ያስተማረውን ትምህርት ተረድተን መተግበር አለብን፡፡ ነጋዴዎችም ቢሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ከሆኑ የቤተ ክርስቲያንን ክብር ሥርዓት በመጠበቅ ዕለቱን ማክበር ይጠበቅባቸዋል እንጂ በዕለቱ ሥራ መሥራት አልተፈቀደላቸውም፡፡
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሦስተኛውን ሳምንት ወይም የምኵራብን በዓል የምናከብርበትን ሥርዓት በሠሩልን መሠረትም ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ ሊያከበረው ይገባል፡፡ በጸሎትም ሆነ ሥርዓተ ቅዳሴ እንዲሁም በስብከተ ወንጌል መሳተፍ፣ ከዚያም ቀጥሎ ምጽዋትንም ሆነ መባን ለቤተ ክርስቲያን ማስገባት አለብን፡፡
በርግጥ አንዳንድ ሰዎች የዕለት ጒርሻቸውን ለመሙላት የቀን ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለምግብ እንዲሁም ለቁሳዊ ነገሮች መግዣ ገንዘብ አስፈላጊ እንደሆነም የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ከሁሉም አስቀድመን እግዚአብሔርን መፍራትና ማክበር እንዳለብን መዘንጋት የለብንም፡፡ ምክንያቱም እስከዚች ዕለት በሕይወት የቆየነው እርሱ ስለፈቀደ ነውና፤ እንደ ቸርነቱ እና ምሕረቱ እንደሚያኖረን ልንረሳ አይገባም፡፡ ሰዎች ሲቸገሩ እግዚአብሔር የማያያቸው እና ጸሎታቸውን የማይሰማቸው ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ፍጥረቱን በሙሉ የሚመግብ አምላክ ነው፡፡ እንኳን ለእኛ ለሰው ልጆች ለእንስሳት በሙሉ ምግብን ያዘጋጃል፡፡ ከእኛ የሚፈለገው ግን ለሕጉ መገዛት እና ትእዛዛቱን መፈጸም በእርሱ ግዛት ለመኖር የሚያስችለንን ምግባር ማከናወን ነው፡፡
ነገር ግን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የሚያውክ ማንኛውም ተግባር መፈጸማችን በእርሱ ዘንድ የተጠላ በመሆኑ ተቸግረን የእርሱን ርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ መፍትሔ ማግኘት ይሳነናል፡፡ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚተላለፉ ሰዎች ሁሉ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትም ከመሻራቸው ባሻገር ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች ጥፋት መንሥኤ ይሆናሉና ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር