‹‹አሁንስ ተስፋዬ ማነው? እግዚአብሔር አይደለምን?›› (መዝ.፴፰፥፯)
የካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
በእግዚአብሔር ተስፋ መኖር በእርሱ ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ እግዚአብሔር ከጎናችን ሲሆንም እያንዳንዳችን ከምናስበው ዳርቻ መድረስ እንችላለን፡፡ ስለዚህ ተስፋችን የሚወሰነው በአምላካችን ላይ ባለን የእምነት ጥንካሬ ነው፡፡ ተስፋ በሕይወታችን ውስጥ ወደፊታችን የምንራመድበት መወጣጫ ድልድይ፣ የኑሮአችን መሠረት እንዲሁም የደስታችን መጀመሪያ ነው፤ በተስፋ ኖረን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንሸጋገራለንና፡፡
ነቢዩ ዳዊት ‹‹አሁንስ ተስፋዬ ማነው? እግዚአብሔር አይደለምን?›› ብሎ እንደተናገረው ሰዎች በመከራ ውስጥ ብንሆንም እግዚአብሔር እኛን ከችግር እንደሚያወጣን ልናምን ይገባል፡፡ ነቢዩ ጠላቶቹ በበዙበት ጊዜ እግዚአብሔር አምላኩን ተስፋ አድርጎና ተመክቶ ይኖር እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል፤ እግዚአብሔርም ለጠላቶቹ አሳልፎ አልሰጠውም፡፡ (፩ ሳሙ. ፲፮-፴፩)
አንዳንድ ሰዎች ግን ማንኛውንም ፈታኝ ሁኔታ በራሳቸው ሊቋቋሙ እንደሚችሉ ያምናሉ፤ ነገር ግን በራስ መተማመን ከመከራ ነፃ አያደርግም፤ ከሁሉም የሚሻለው በእግዚአብሔር ማመንና ተስፋም ማድረግ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ተስፋ ካደረግን ማንኛውንም ችግር እንወጣዋለን፤ ተስፋ ከእምነት ኃይል ጋር የቆራኘ ነውና፡፡ አባታችን አብርሃም ‹‹ዘርህ እንዲሁ ይሆናል ብሎ እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጠው ተስፋ ባልነበረ ጊዜ የብዙዎች አሕዛብ አባት እንደሚሆን አመነ፡፡›› (መዝ.፴፰፥፯፣ሮሜ ፬፥፲፰)
ተስፋም ልክ እንደ እምነት በማይታየው ነገር ውስጥ ነው፡፡ ‹‹የነፍሳችን ድኅነት እናገኝ ዘንድ የልጅነትን ክብር ተስፋ እናደርጋለንና፤ በእምነት ድነናልና፡፡ የሚታየውን ተስፋ ማድረግ ተስፋ አይደለም፡፡ የሚያየውንማ እንዴት ተስፋ ያደርጋል? እንዴትስ ይጠብቃል? የማይታየውን ተስፋ ብናደርግ ግን እርሱን ተስፋ አድርገን በእርሱ እንደ ጸናን መጠን ትዕግሥታችን ይታወቃል›› እንዲል፡፤ (ሮሜ ፰፥፳፬-፳፭)
ተስፋ በእግዚአብሔር በማመን የምንኖረው የሕይወታችን መልካም ውጤት ማረጋገጫ ነው። በእምነት ላይ የተገነባውን የሕይወት ፍሬን እንደሚያፈራ ተክል እያደር ያብባል። ምንም እንኳን በዚህ ጨለማ በሆነው እና ኃጢአት በበዛበት ዓለም ብንኖርም የእግዚአብሔር ቸርነቱ በእኛ ላይ የበዛ በመሆኑ በእርሱ ተስፋ ማድረግ በእምነት መኖር ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርገዋለች፥ ረዳታችን እና መጠጊያችን እርሱ ነውና፡፡ ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋልና፥ በቅዱስ ስሙም ታምነናልና። አቤቱ፥ በአንተ ተስፋ እንደ ታመንን ፥ ምሕረትህ በላያችን ትሁን›› እንዲል። (መዝ. ፴፫፥፳-፳፪)
የተስፋ ተቃራኒ ተስፋ መቁረጥ ነው፤ ተስፋ ማጣት ከሁሉ የከፋ ነው፡፡ ምክንያቱም ያለ ተስፋ መኖር አይቻልም፡፡ አንድ ሰው እምነት ከሌለው ሊያምን ይችላል፡፡ አንድ ሰው የሚኮራ ከሆነ ሊዋረድ ይችላል፤ ርኩስ፣ ሊነፃ ይችላል፤ ደካማ፣ እርሱ ሊጠነክር ይችላል፤ ክፉ ጻድቅ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንድ ሰው ተስፋ ቢቆርጥ የመኖር ትርጉሙን መረዳት ይሳነውና የሚያደርገው ነገር ሁሉ በደመ ነፍስ ይሆናል፤ በሕይወቱ ውስጥም የሚወስናቸው ውሳኔዎች በተሳሳተ አመለካከት እንዲሁም እርምጃው ሁሉ የተዛባ ይሆናል፡፡ ያመነበትንም ሆነ ያላመነበትን ነገር በዘፈቀደ ይተገብራል፡፡ ስለዚህም ለኃጢአት ይጋለጣል፤ ወደ ትክክለኛው መንገዱ መመለሻውም ይጠፋበታል፤ ወደ እግዚአብሔርም መቅረብ ይሳነዋል፡፡
ሰዎች በዚህ ዓለም ስንኖር ብዙ መከራ እና ሥቃይ ሊደርስብን ይችላል፤ ሕይወታችንም በፈተና የተሞላ ይሆናል፡፡ በማኅበረሰባዊ፣ በሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ችግር ምክንያት ሰዎች ብዙ መከራ ሊደርስብን ይችላል፡፡ የኢዮብን ታሪክ ብንመለከት ሀብቱ÷ ንብረቱ ሲጠፋ ልጆቹ በሙሉ ሲሞቱና መላ አካሉ በበሽታ ሲመታ አምላኩን ተስፋ አድርጎ ታግሦ ኖረ እንጂ ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ‹‹ወተፈትነ ወተነጥፈ ከመ ወርቅ በእሳት፤ ወርቅ በእሳት እንዲፈተን ፈጽሞ ተፈተነ›› ተብሏል:: እግዚአብሔርም በደመና ውስጥ ኢዮብን ተናገረው:: ከዚያ በኋላ ከደዌ ሁሉ ፈወሰው፤ ሀብቱንም ሁሉ ባርኮ ከቀድሞ እጥፍ አደረገለት የተባረኩ ልጆችም ሌሎች ወንዶችና ሴቶችን ሰጠው:: (ኢዮብ ፩፥፳፩)
ዓለም በዚህ ጊዜ በጦርነት በበሽታና በተለያዩ መቅሠፍቶች ተይዛ እየተጨነቀች መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በተማራችሁት ሃይማኖት ጽኑ›› ብሎ እንደተናገረው እግዚአብሔር አምላካችንን ተስፋ አድርገን በእምነት ጸንተን መኖር ይጠበቅብናል፡፡ እኛ ያዳነን እግዚአብሔር አንድ ልጁን ሠውቶ በመስቀሉ ላይ በከፈልንን ዋጋ መዳን እንደምንችል አምነን በተስፋ መኖር አለብን፡፡ (ቆላ.፪፥፯)
የእግዚአብሔር ቃል ተስፋ ነው፤ ዘወትርም ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ቃሉን በመስማት እና ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ወንጌልን በማወቅ አዳኝነቱን ተረድቶ እርሱን ተስፋ አድርጎ መኖር ተገቢ ነው፡፡ ቃሉን የተረዱ፣ ለሕጉ የተገዙና ትእዛዛቱን የፈጸሙ ጻድቃን እርሱን ተስፋ ከማድረጋቸውም በላይ ለሌሎች የድኅነት ተስፋ እንደሆኑም ገድላቸው ይዘክራል፡፡ የእነርሱ እምነትም ኃይልን ታደርጋለችና በጸሎታቸው እንዲያስቡን እንዲሁም በአማላጅነታቸው ተራዳኢነታቸው ከእግዚአብሔር ቸርነትን ምሕረትን እንዲለምኑልን ተስፋ በማድረግም እንማጸናለን፡፡
በተለይም በዚህ ጊዜ የእነርሱም አማላጅ ተራዳኢነት ያስፈልገናልና ቅዱሳን አባቶችንና ጻድቃን ሰማዕታትን ሁሉ ተስፋ በማድረግ ወደ እግዚአብሔር ልንጸልይ ይገባል፤ ችግራችንን መከራችንን በጽናት እንድንወጣውና ፈተናችንን እናልፍ ዘንድም የእነርሱን አማላጅነትና ተረዳኢነት ተስፋ አድርጎ መኖር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላካችን የእኛን ድኅነት እንጂ ጥፋት ስለማይፈለግና ለብዙ ቅዱሳን እና ጻድቃን ቃል ኪዳን በመስጠት ለልጆቹ ድኅነት እንዲሆኑ ፈቅዶላቸዋል፡፡ እኛም ይህን ተስፋ በማድረግ ቀናቸውን በማሰብና በመዘከር በእነርሱ አማላጅነት እንድን ዘንድ ተስፋ እንኑር፡፡
የእግዚአብሔር አምላካችን ቸርነትና ምሕረት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ቅዱሳን፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት አማላጅነት ተረዳኢነት አይለየን፤ አሜን፡፡