‹‹እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ጥቂትስ እንኳ የለም›› (፩ዮሐ. ፩፥፭)

ፀሐይ በቀን፣ ጨረቃም በጨለማ ለምድር ብርሃን እንደሆኑ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር በአማኞቹ ልብ ያበራል፤ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ‹‹እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ጥቂትስ እንኳ የለም›› ሲል እንደተናረው በእርሱ ዘንድ ጨለማ የለም፤ ሁሌም ብርሃን ነው፡፡ ‹‹ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤ የመብራት ብርሃን፥ ወይም የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ እግዚአብሔር ያበራላቸዋልና፤ ለዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣሉ›› እንደተባለው ያ ብርሃን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ነው፡፡ (ራእ. ፳፪፥፭)

ነቢዩ ዳዊትም ‹‹ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፤ እነርሱም ይምሩኝ ፥ አቤቱ ወደ መቅደስህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ›› እንዳለው ‹‹ብርሃን፣ ጽድቅ እና እውነት የሆነውን ቅዱስ ልጅህን  ልከህ ጨለማ ሆኖ የጋረደንና ካንተ የለየን ኃጢአታችን አስወግዶና ከአንተ አስታርቆ ወደ አንተ ይውሰደን›› ማለቱ ነው።  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በተዋሕዶ ፍጹም አምላክና ሰው ሆኖ በዓለም ሲያስተምር  «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ» በማለት ብርሃንነቱን አረጋግጧል፤ እርሱን የሚከተል ሁሉም ያንን ብርሃን እንደሚያገኝ እንዲህ በማለት ተናግሯል ‹‹የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ያገኛል እንጂ በጨለማም አይመላለስም።›› ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ሁሉ ሕይወት የሆነች ብርሃንን ገልጧል፤ ብርሃን መሆኑን ደቀ መዛሙሩ ቅዱስ ዮሐንስ ስለ  ብርሃንነቱ እንዲህ በማለት መስክሯል ‹‹ሕይወት በእርሱ ነበረ፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፤ ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም አላገኘውም።›› ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር የሚያበራ  እውነተኛ ብርሃን ነው። ሊቃውንትም ፀሐይ ዘዘልፈ ያበርህ፤ ሁሉ ጊዜ የሚያበራ ፀሐይዘእንተ ውስጥ አይነነ አብራህከ ወጽልመተ ሕሊናነ፣ ብርሃነ ፍጹማን ወልደ አምላክ ሕያው፤ የሕሊናችንን ጽልመት ያበራ፣ ዓይነ ልቡናችንን የገለጠው፣ የሕያው አምላክ ልጅ የፍጹማን ብርሃን ብለውታል። ቅዱስ ዮሐንስም ስለዚህ ብርሃን ሲመሰክር ‹‹ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛ ብርሃን ወደ ዓለም የመጣው ነው›› ብሏል፡፡ (ጸሎተ ኪዳን ፣መዝ. ፵፪፥፫፣ ዮሐ. ፰፥፲፪፣ ዮሐ. ፩፥፬-፭፣፩፥፱)

ቅዱሳን ነቢያት ሰው ሁሉ በጨለማ ውስጥ መኖሩን አውቀውና ተረድተው ጨለማውን ለማስወገድ አምላካችን ብርሃን እንዲልክላቸው የዘወትር ልመናቸውና ጸሎታቸው ነበረ፡፡ የነፍሳቸውን ብርሃን በተስፋ ይጠብቁ እንደነበርም  ቅዱሳት መጻሕፍት ይጠቅሳሉ፡፡ ጌታችን ከመምጣቱ በፊት በዘመነ ብሉይ÷ ደዌ-ሥጋ፣ ደዌ- ነፍስ የጸናበት፣ ለሰው ሁሉ አስጨናቂ ዘመን የሆነበት፣ ሁሉም  ሰው ብርሃን ከሆነው አምላኩ ርቆ በጭንቅ፣ በመከራና በጨለማ ውስጥ በመኖሩ ተስፋ ቢስ ሆኖ የኖረበት ዘመን በመሆኑ «ዘመነ-ፍዳ» ተብሏል፡፡ ይህንን ጨለማ  አስወግዶ ወደ ብርሃን የሚቀይር በጨለማ የሚያበራ ብርሃን እንዲልክላቸውና ከብርሃን የተገኘ እውነተኛ ብርሃን፣ አማናዊ ብርሃን ጌታችን ኢየሱስ እንዲመጣ ዘወትር ሲጸልዩም ነበር፡፡

በጨለማ የተጓዘ እንቅፋት ይመታዋል፤ ይህም በችግርና መከራ መውደቅ ነው፡፤ ጌታችን ኢየሱስ ግን ጨለማን በማስወገድ ብርሃን ሆኖ ከችግር ሁሉ ያወጣል። ስለዚህ ከእንቅፋትም ከውድቀትም ለመዳን በብርሃን መጓዝ ይገባል። በራሳችን ፈቃድ ከአምላካችን ካልራቅን እና ጨለማን ካልመረጥን እርሱ ብርሃን ይሆንልናል፤ ‹‹ብርሃን ዘበአማን ዘያበርህ ለኩሉ ሰብእ ለእለ ይነብሩ ውስተ ዓለም በእንተ ፍቅረ ሰብእ መጻእከ ውስተ ዓለም ወኩሉ ፍጥረት ተፈሥሐ በምጽአትከ፤ ሁሉም ፍጡር ሰው በመሆንህ የተደሰተብህ፣ ሰውን ወደህ ወደዚህ ዓለም የመጣህ፣ በዓለም ውስጥ ላለ ሁሉ ሰው የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን›› ተብሏል። ታድያ እኛስ ያለ እርሱ በጨለማ ውስጥ እንደምንኖር ተገንዝበናል? (የሰኞ ውዳሴ ማርያም)

በዕለተ ረቡዕ ለፍጡራን ሁሉ እርሱ ራሱ የፈጠራት ፀሐይ ከእነርሱ አልጠፋችም ነበር፤ አሁንም አለች፤ እርሷ ለሁሉም ብርሃን ናት፡፡ ነገር ግን በዘመነ ኦሪት የነበሩ ሰዎች ብርሃንህን ላክልን ሲሉ የነበረ አሁን በግዙፍ ዓይናችን የምንመለከታትን የፀሐይን ብርሃን አጥተው አልነበረም፡፡ የውስጥን ጨለማ ድንቁርናና ኃጢአትን አስወግዶ ውስጣዊ ሕሊናን በማብራት አምላካችንን የምንከተልበት መንፈሳዊ ዓይናችን ሊያበራ የሚችል አማናዊ ብርሃንን ፈልገው ነው እንጂ፤ አሁንም እኛ የዕውራንን ዓይንና አእምሮ የሚገልጠውን አማናዊ ብርሃንን ልንመኝ ይገባል፡፡

በዚህ ዓለም የምናገኘውን የፀሐይ ብርሃን ሁላችንም በጋራ እንጠቀመዋለን፤ ሆኖም ውስጣዊ ማንነታችንን አይገልጽም፤ የሚያስደንቀው ግን የእግዚአብሔር ቸርነት ነው፤ ምክንያቱም ይህ ብርሃን ለሚያምኑትም ሆነ ለማያምኑት፣ ለጠላቶቹም ሆነ ለወዳጆቹም በእኩል መድረሱ ነው፤ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ቀኑን በማፈራረቅ ለዓለም ስታበራ የቆየች ፀሐይ እንደ ሌሎቹ ፍጡራን አንድ ቀን ማለፍዋ ስለማይቀር የምትሰጠው ብርሃን የተፈራረቀና ውጫዊ ብርሃን  ቢሆንም እንኳ እርሱም ቀጣይነት እንደሌለው የተረጋገጠ ነው፡፡  ስለዚህ ብርሃንን ከሚጠሉና ጨለማን ከመረጡ ሰዎች መለየት አለብን፤ ከጨለማው ዓለምና አስተሳሰብ ወጥተን በፈጠራት ፀሐይ ዓለምን ያበራ እርሱ ራሱ ብርሃን በመሆን ደግሞ ውጫዊውንና ውሰጣዊውን የሚያበራ የሥጋና የነፍስ ብርሃን የሆነ የሕይወት ብርሃን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንከተል፡፡ ከዓለማዊ አስተሳሰብ ወጥተን ወደመንፈሳዊና ዘለዓለማዊ ሕይወት  እንግባ፡፡ ‹‹እናንተስ አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት፥ ጽድቁንም ፈልጉ›› ብሎ ጌታችን እንዳስተማረው በቃሉ እንመራ። ይህንን ማድረጋችን ከኃጢአትና ሥርዓት አልባ ከሆነ ዓለማዊ ምኞት እንጂ ከመብላት፣ ከመልበስ፣ ከመሥራትና ትዳር ከመያዝ አያግደንም፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም እንዲህ ብሏል ‹‹ከእንቅልፍ የምትነቁበት ጊዜ እንደ ደረሰ ዕወቁ፤ ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ደርሳለችና። ሌሊቱ አልፎአል፤ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማን ሥራ ከእኛ እናርቅ፤ የብርሃንንም ጋሻ ጦር እንልበስ። በቀን እንደሚሆን በጽድቅ ሥራ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር፥ በዝሙትና በመዳራትም አይሁን፥ በክርክርና በቅናትም አይሁን፡፡ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ የሥጋችሁንም ምኞት አታስቡ።›› (ሮሜ. ፲፫፥፲፩-፲፬)

በብርሃኑ ልቡናችን ያበራል ዘንድ የአምላካችን እግዚአብሔር ፍቃድ ይሁንልን፤አሜን!!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!