“እነሆ÷ ድነሃል ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ (ዮሐ.፭፤፲፬)

በእንዳለ ደምስስ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን ይሰብክ በነበረበት ዘመን አምስት ገበያ ሕዝብ ይከተለው እንደ ነበር በቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ተገልጾ እናገኛለን፡፡ አምስት ሺህ ሰዎች ያህሉ ነበርና ለደቀ መዛሙርቱ በየክፍሉ አምሳ አምሳውን አስቀምጡአቸው አላቸው፤ (ሉቃ.፱፤፲፬) እንዲል፡፡ ሕዝቡም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የተከተሉበት የተለያየ ምክንያት ነበራቸው፡፡ትምህርቱን ሰምተው፣ በተአምራቱ ተደንቀው፣ ከተያዙበት የአጋንንት ቁራኝነት ለመፈወስ፣ ረሐባቸውንና ጥማቸውን ለማስታገስ፣ መልኩን ለማየት፣ ጎዶሏቸውን ይሞላላቸው ዘንድም ይከተሉት ስለነበር እንደ መሻታቸውም ይፈጽምላቸው ነበር፡፡

በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዘው ይማቅቁ የነበሩትንም ካዳናቸው በኋላ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ ይመልሳቸው ዘንድ ዳግመኛ እንዳይበድሉ ያስጠነቅቃቸውም ነበር፡፡ የእምነት ጽናት የነበራቸውንና በተግባርም የገለጡትን ጌታችን ኢየሱስ፦ “ሂድ፤ እምነትህ አዳነችህ” (ማር. ፲፥፶፪) እያለም መስክሮላቸዋል፡፡

እነሆ÷ ድነሃል ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ የተባለው ሰው ደግሞ ለ፴፰ ዓመት ደዌ ሥጋ ሰልጥኖበት፣ አጥንቱ ከመኝታው የተጣበቀበት፣ ረዳት አጥቶ በቤተ ሳይዳ በበጎች በር በመጠመቂያው አጠገብ የወደቀው መጻጉዕ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃውን በሚያናውጠው ጊዜ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በደዌ ብዙ ዘመን እንደቆየ አውቆ ልትድን ትወዳለህን?ነበር ያለው፡፡ በመጀመሪያ ለመዳን ፈቃዱን ነበር የጠየቀው፡፡ መጻጉዕም አዎን ጌታዬ፤ ነገር ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያው የሚወስደኝ ሰው የለኝም የሚል ነበር መልሱ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መጥፋታችንን ሳይሆን መዳናችንን የሚወድ ቸር አምላክ ነውና ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ (ዮሐ.፭፥፰-፱) በማለት ድኅነቱን አበሠረው፡፡ከታሠረበት ተፈታ፣ ከወደቀበት ተነሣ፣ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ፡፡(ዮሐ.፭፥፰-፱)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጻጉዕን የፈወሰው በቀዳሚት ሰንበት ቀን ነው፤ ሆኖም አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ብቻ አልነበረም ያለው፡፡እነሆ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ በማለት አስጠንቅቆታል፡፡ ይህም መጻጉዕ ኃጢአተኛ እንደነበርና ፈውሰ ሥጋን ካገኘ በኋላ አምላኩን በማገልገል እንዲኖር ጌታችን አስጠንቅቆታል፡፡ ያ ካልሆነ ግን ድኀነተ ነፍስን ከምድራዊ ስቃይ የባሰ ዘለዓለማዊ እሳት ውስጥ  መጣል እንዳለ ሲያመለክተው ነው፡፡

ከዚህ በኋላ አይሁድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በምቀኝነት ሊገድሉት ይፈልጉ ነበርና ከሰሱት፡፡ አንዱ ክሳቸው ሰንበትን ይሽራል የሚል ስለነበር መጻጉዕ በሰንበት የፈወሰኝ እሱ ነው በማለት ቢመሰክርም ለ፴፰ ዓመት ከተያዘበት ሥቃይ የገላገለውን አምላኩን በመካድ በጥፊ እስከ መማታት ደርሷል፡፡

ጻድቁ ኢዮብ መንገዴን ፈጽሞ ዐወቀ፣ እንደ ወርቅም ፈተነኝ፣ እንደ ትእዛዙ እወጣለሁ፣ መንገዱንም ጠብቄያለሁ፣ ፈቀቅም አላልሁም በማለት በመከራው ዘመናት ለአምላኩ የነበረውን ፍጹም እምነት መስክሯል፤ (ኢዮ.፳፫፣፲፩)፡፡ መጻጉዕ ግን ምላሹን በክህደት ገለጸ፡፡

ምርጥ ዕቃ የተሰኘው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም አምላኩንም ከማሳደድ መልሶ የወንጌል ገበሬ ሲያደረገው እንግዲህስ የጽደቅ አክሊል ይቆየኛል እንዲል (፪ኛ ጢሞ.፬፥፰) እስከ ሞት ድረስ ታመነ፡፡ አንገቱንም ለሰይፍ አሳልፎ እስከ መስጠት አደረሰው፡፡ መጻጉዕ ግን ለክህደት ራሱን አሳልፎ ሰጠ፣ ክህደቱንም በጥፊ በመማታት ገለጸ፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ሁሉንም በሥርዓት የምታከናውን ስንዱ እመቤት ናትና በዐቢይ ጾም ከሚገኙት ሰንበታት ውስጥ ዐራተኛውን ሰንበት መጻጉዕ ብላ ሰይማዋለች፡፡ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብንወድቅ እንደሚያነሣን፣ ብንታመም እንደሚፈውሰን ለማስተማር፣ እንዲሁም ደግሞ ከመጻጉዕ ሕይወት እንማር ዘንድ መታሰቢያውን አደረገች፡፡ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ እንዳለ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ እንሸጋገር ዘንድ፣ የአምላካችንን ቃል መፈጸም እንደሚገባን፣ እሰከ ሞትም መታመን እንዳለብን ያስተምረናል፡፡ በተለይም በንስሐ ሕይወት ውስጥ መኖርና እያንዳንዱን እንቅስቃሴያችን እግዚአብሔርን በመፍራት ልንፈጽም ይገባል፡፡ ሰው ኃጢአት ሰርቶ ንስሐ ከገባ በኋላ ዳግም የሚበድልና ፈጣሪውን የሚያሳዝን ከሆነ የሚያገኘው ሁለተኛ ጥፋትና ሞት ነው፡፡ ይህን ሁሌም በማሰብ በሕገ እግዚአብሔር በመኖርና እስከ ኅልፈተ ሕይወታችን በእምነት ልንጸና ይገባል፡፡ ጌታችንም ስለ እምነት ጽናት በዚያን ጊዜ እንዳስተማረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል፡፡ ለዚህም ምሳሌ ጌታችን ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ ልጁን እንዲያድንለት የጠየቀውን የመቶ አለቃውን ታሪክ ማየት ይቻላል፡፡ እርሱም ወደ ጌታችን መጥቶ አቤቱ ልጄ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተጨነቀ በቤት ተኝቷልብሎ ለመነው፡፡ ጌታችንም እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ አለው፡፡ የመቶ አለቃውም አቤቱ አንተ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፡፡ ነገር ግን በቃልህ እዘዝ ልጄም ይድናል አለ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መቶ አለቃውን እጅግ አደነቀ፡፡ እውነት እላችኋለሁ፣ በእስራኤል ሁሉ እንዲህ ያለ እምነት አላገኘሁም ብሎም መሰከረለት፡፡ በመቶ አለቃውም እምነት ተደነቀ፡፡ እንደ እምነትህ ይሁን አለው፤ ከዚያም ሰዓት ጀምሮ ልጁ ዳነ፡፡(ማቴ.፰፤፭-፲፫)

ይህ በእምነት ጽናት የተገለጸ ሕይወት ነው፡፡ መጻጉዕ ግን ያዳነውን አምላኩን በዓይኑ አይቶ፣ በእጁ ዳስሶ፣ ለ፴፰ ዓመታት የተኛበትን (የተሸከመውን አልጋ) እንደገና እሱ ተሸክሞት እንዲሄድ ዕድሉን የሰጠውን አምላኩን ካደ፡፡ በእምነት የጸኑ፣ እንደ ቃሉም የተጓዙ፣ እስከ ሞትም የታመኑት ድነው ኑ የአባቴ ቡሩካን እንዲባሉና፤ በክህደት ያጠናቀቁት ደግሞ አላውቃችሁም ተብለው ጥርስ ወደ ማፋጨት፣ እሳቱ ወደማይጠፋበት ጥልቅ እንዲወረወሩ ሁሉ፤ መጻጉዕ ዕድሉን አበላሸ፡፡ ጽድቅ በፊቱ ቀርቦለት መርገምን መረጠ፣ ከዘለዓለማዊ ሕይወት ዘለዓለማዊ ሞትን ምርጫው አደረገ፡፡

እኛስ ምርጫችን የቱ ይሆን? በዐቢይ ጾም ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን ሰንበታቱን እንድናከብር የምታዘን እንማርባቸው ዘንድ ነው፡፡ ጽድቅን በመሻት ሕይወታችን ከእግዚአብሔር ጋር እንድናደርግ፣ መንገዱንም እንከተል ዘንድ ነው፡፡ ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው (መዝ.፻፲፱፤፻፭) ተብሎ እንደተጻፈው፡፡

እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው እንደተባለው አምላካችን የጎደለንን እንዲሞላልን በጾም፣ በጸሎት፣ በፍጹም ትህትና እና እምነት ልንተጋ ያስፈልጋል፤ (፩ኛ ዜና.፲፮፤፲)፡፡ መጻጉዕ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ እንደተባለውም የአምላካችንን ቃል ዘንግተን፣ የተደረገልንን መልካም ነገር ሁሉ በክፉ እንዳንለውጥ መጠንቀቅ ከእኛ ኦርቶዶክሳውያን ይጠበቃል፡፡

በዘመነ ሥጋዌ ጌታችን ወደዚህ ምድር የመጣበት ምክንያትም የአዳምን ዘር በሙሉ ከኃጢአት ቁራኛነት ለማላቀቅ በመሆኑ በዚያን ጊዜ አምላካችን ታመው ወደእርሱ በመቅረባቸው ድኀነተ ሥጋን ያገኙ ሰዎች ከኃጢአት ሁሉ ተጠብቀው ድኀነተ ነፍስንም ያገኙ ዘንድ ዳግም እንዳይበድሉ አስጠንቅቋቸዋል፡፡ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ አባታችን አዳምንና እናታችን ሔዋንን አስቶ ዕፀ በለስን (የሞት ፍሬን) እንዲበሉ ካደረጋቸው በኋላ ከገነት ወጥተዋል፡፡ ምድርም በእነርሱ በደል ምክንያት የተረገመች ሆነች፤ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና÷ ከእርሱ እንዳትበላ ከአዘዙህ ከዚያ ዛፍም በልተሃልና ምድር በሥራህ የተረገመች ትሁን (ዘፍ. ፫፥፲፯) እንደተባለው፤ ይህም በምድር ብዙ መከራን እንዲቀበሉና በሠሩት ኃጢአት እንዲቀጡ አድርጓቸዋል፡፡ አዳም በኃዘንና በስቃይ ለብዙ ዘመን ሲያለቅስ እንደኖረም ቅዱሳት መጻሕፍት ይጠቅሳሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም የአዳምን እንባ አይቶ ልመናውንም ሰምቶ ሊያድነው ስለፈቀደ ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ፣ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅዬ አድንሀለው›› ብሎ ቃል ኪዳን እንደሰጠው ሁሉ የአዳም ዘር በሙሉ በክርስቶስ ሞት ከእርግማን ተላቆ ድኅነትን አገኘ፡፡ እኛም ይህን ቃል በመቀበል እንደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀሉን በመሸከም ለእምነታችንና ለሃይማኖታችን መስዋዕት በመክፈል እንዲሁም በመስቀሉ ላይ የተቆረሰውን ቅዱስ ሥጋውንና የተቀዳውን ክቡር ደሙን በመብላትና በመጠጣት ልንድን ያስፈልገናል፡፡ ከዚህም ባሻገር የሰው ልጅ በሙሉ የተፈጠረበትን ምክንያት በመረዳት ዘወትር በሕገ እግዚአብሔር በመኖር ፈጣሪያችንን ልናገለግል ይገባል፡፡ የአምላካችንን ቃል በሕይወታችን ዘመን ሁሉ በመፈጸም፣ እስከ መጨረሻው እንድንጸና አምላካችን ይርዳን፡፡ አሜን!