ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ጾመ?
ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ
በገዳም ቆሮንቶስ ፵ ቀንና ለሊት የጾመው
ሀ/ ሕግን ሊፈጽም
የሕግ ሁሉ ባለቤት የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ጾምን ለአዳም የሰጠው ጥንታዊው ሕግ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰማያዊ ዋጋ የሚያገኝበት ጸንቶ እንዲቆም የሚያስችለውና ከክፉ የሚጠብቀው መንፈሳዊ መከላከያው መድኃኒት ሆኖ የተሰጠው ፤ ኦሪትም የተሰራችው በጾም ነበር፡፡ አባታችን ሙሴ ኦሪት ዘዳግም ፱፥፱ ላይ “ሁለቱን የድንጋይ ጽላት እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የተማማለባቸውን የቃልኪዳን ጽላት እቀበል ዘንድ ወደ ተራራ በወጣሁ ጊዜ በተራራውም አርባ ቀንና አርባ ለሊት ተቀምጬ ነበር፤ እንጀራ አልበላሁም፤ ውሃም አልጠጣሁም”፤ አለ፡፡ በዚህም ሙሴ የኦሪትን ሕግ ተቀበለ፤ እናም ሕግን ለመቀበል በቅድሚያ መጾም ያስፈልጋል ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕግን ሲፈጽም በቅድሚያ የወንጌል መጀመሪያ ያደረገው ጾምን ነው፤ የማቴዎስ ወንጌል ፬፥፩-፲፩ ላይ “እኔ ሕግ ልሽር ሳይሆን ልፈጽም ወደ ምድር ወርጃለሁ”፤ አለ፡፡
ለ/ዕዳችንን ሊከፍል (ካሳ ሊሆነን)፤
እግዚአብሔር ለአባታችን አዳም “ይህንን ዕፀ በለስ አትብላ፤ የበላህ እንደሆነ ትሞታለህ”፤ ብሎት የነበረውን ትእዛዝ ተላልፎ በራሱ ፍቃዱ ተጠቅሞ የተከለከለችዋን ፍሬ በላ፤ ሕግንም ጣሰ፡፡ ስለዚህ አዳም በመብላት ያመጣውን ሞት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ለ፵ ቀን ለ፵ ለሊት ባለመብላት ባለመጠጣት ዕዳችንን ከፈለ፡፡ ደሙን አፍሶ፤ ሥጋውን ቆርሶ፤ በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ አዳምን ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከሲኦል ወደ ገነት መለሰው፡፡
ሐ/ለአርያነት፤ የመንፈሳዊና የበጎ ምግባር ሁሉ መነሻው ጾም ነው፡፡ የዕለተ ዐርብ የማዳኑን ሥራ በጾም ጀመረ፤ የወንጌል ሥራ መጀመሪያም አደረጋት፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በዮርዳኖስ ከተጠመቀ በኋላ ሥራውን በጾም እንደ ጀመረ ሐዋርያትም ስለተረዱ እርሱን በመምሰል ሥራቸውን በጾም ጀመሩት፡፡ አባቶቻችን ጾምን የትምህርት መጀመሪያ አደረጓት፤ በዚህም ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር ጋር በመንግሥቱ እንዲኖሩ በር ስለከፈተላቸው ለአርአያነት ነው ብለን ተቀበልነው፡፡ ሆኖም ሳይጾም ጹሙ አላለንም፤ በምድር እስካለንና እርሱ አርአያ እስከሆነን ድረስ ከመዓትና ከዘላለም እሳት ለመዳን በጾምና ጸሎት ልንኖር ያስፈልጋል፡፡፡
መ/ሊያስተምረን፤ የተፈቀደውን እየፈጸምን፤ የተከለከልነውን በመተው ሕግ እያከበርን በትምህርተ ወንጌል ድኅነትን እንድናገኝና የነፍሳችን ቁስል እንዲፈወስ ለክርስቶስ ሕይወታችንን መስጠት አለብን፡፡ እንዲሁም ለመጾም ድፍረት ያላት ነፍስ ቀጣይነት ባለው መንፈሳዊ ልምምድ ራስን መግዛት ለሥጋ ፈቃድ የሚያስፈልገውን ምግብና መጠጥ በመተው የሥጋ ፈቃድን ድል በመንሣት ለነፍስ ፈቃድ ማስገዛት ይቻላል ፡፡ ይህቺ ነፍስ ክርስቶስ ያስተማራትን ከተገበረች የሚመጣባትን ከባድ ነገር ሁሉ እስራቱንና ግርፋትን መቋቋም ይቻላታል፡፡ ስለዚህ መጾም በኃጢአታችን እንድንጸጸትና ወደ አግዚአብሔር እንድንመለስ (እንድንቀርብ )ብቻ ሳይሆን ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ያለንን ፍቅር ለመግለጽ እንድንችል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡
ሠ/ ዲያብሎስን ድል ለመንሣት፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ፬፥፩-፲፩ ላይ መዋዕለ ጾሙ ሲፈጸም ሰይጣን በሦስት ነገር ማለትም በስስት፣ በትዕቢትና በፍቅረ ንዋይ ተፈታተነው፡፡ በስስት ቢፈትነው በትዕግስት፣ በትዕቢት ቢቀርበው በትሕትና፤ በፍቅረ ንዋይ ሊያታልለው ቢሞክር በጸሊአ ንዋይ ድል ነሣው፡፡ ዛሬ እነዚህን ማሳቻ መንገዶች ለይተን ጠላታችንን ድል መንሣት እንችላለን፤ ክርስቶስ ሳጥናኤልን ስለ እኛም ተዋጋው፤ በገሃነም ጣለው፡፡ በዮሐዋንስ ወንጌል ፲፮፥፴፫ ላይ “ስለዚህ እኔ ዓለምን ድል ነስቼዋለኹና ድል ንሱ” ያለበት ምክንያትም ጾም ደዌ ነፍስን ትፈውሳለችና፡፡ የሥጋ ምኞትን አጥፍታ የነፍስን ረኃብ ታስታግሳለችና፤ ከዲያብሎስ ቁራኝነት በማላቀቅ ከክርስቶስ ጋር አንድ ታደርጋለች፡፡
እኛ ለምን እንጾማለን?
ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጾም ለነፍሳችን ካሳ እንደሆነን ሁሉ እየጾምን፤ ጠላታችን ሳጥናኤልን ድል ነሥተን አባቶቻችን የወረሱትን ርስት እንድንወርስ እንጾማለን፡፡ ጾም በመንፈሳዊ ሕይወት የመበልጸጊያና የሰውነት መሻትን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ የማቅረቢያ መንገድ ነው፡፡ በዚህም ጾም የወንጌልና የበጎ ሥራ ሁሉ መጀመሪያና የትሩፋት ጌጥ እንደሆነ ሁሉ፤ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው፤ አልፋና ኦሜጋ ልዑል እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠው የመጀመሪያ ትእዛዙ ነው፡፡ ዘፍጥረት ፪፡፲፯ ላይ “ነገር ግን መልካሙንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና”፤ ብሎ ያዘዘው ትእዛዝ ይህ ነውና፡፡
ጾም ስንል፤ ፩ኛ እግዚአብሔርን የምንፈራበትና ከእግዚአብሔር ምሕረት የምንለምንበት መንገድ ነው፡፡
ዕዝራ ፰፡፳፫ ላይ “ስለዚህም ነገር ጾምን ወደ እግዚአብሔር ለመንን፤ እርሱም ተለመነን”፤ በማለት ጾም እግዚአብሔርን መለመኛ እና ጸሎታችንን እንዲሰማን የምናደርግበት መሣሪያችን መሆኑን በተግባር እንዳገኙ እንረዳበታለን፡፡
፪ኛ ኀዘናችንን እና ችግራችንን ለእግዚአብሔር የምንነግርበትና የምናቀርብበት መንገድ ነው፡፡
ነቢዩ ኢዩኤልም ሕዝበ እስራኤልን ሐዘን በገጠማቸው ጊዜ፤ በመከራም ሳሉ ትንቢተ ኢዩኤል ፩፥፲፬ ላይ የነገራቸው ቃል “ጾምን ቀድሱ፤ ጉባኤውንም አውጁ፤ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔር ጩኹ”፤ በማለት ወደ እግዚአብሔር መጸለይ እንደሚገባ ነግሮናል፡፡ ትንቢተ ኢዩኤል ፪፡፲፪ ላይም “እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም፣በለቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፤ በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምንም ቀድሱ፤ ጉባኤውንም አውጁ”፤ በማለት ነግሮናል፡፡ ስለዚህ ለእግዚአብሔር በመብላት፣ በመጠጣትና በሥጋ ፍላጎት ሆነን የፍላጎታችን፣ የሰላማችንንና የአንድነታችን መሻት መጠየቅ የለብንም፡፡ መጀመሪያ እራሱ ክርስቶስ ማድረግ ያለብንን የተግባር ሥራ እንድንሰራ የነገረን ከችግራችንና ከሐዘናችን ለመላቀቅ በምድር ለምንኖር ሁሉ መጾም እንዳለብን እራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔር በነቢያት አድሮ ነግሮናል፡፡
፫ኛ ስብራታችን የምንጠግንበትንና መልካም የሆነ ትውልድ የሚታነጽበት መሣሪያ ነው፤
ትንቢተ ኢሳያስ ፶፰፡፲፪ ላይ “ከድሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎችህ ይሠራሉ፤ መሠረትህም ለልጅ ልጅ ዘመን ይሆናል፤ አንተም ሰባራውን ጠጋኝ የመኖሪያ መንገድንም አዳሽ ትባላለህ”፡፡ እንዲሁም በቁጥር ፭ ላይ “እኔ ይህንን ጾም የመረጥሁ አይደለሁም”፤ እንደዚችም ባለች ቀን ሰው ራሱን ማሳዘን እንደሌለበትና በዚህም ጾም ራሱን ቢያስገዛ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ይታመናል፤ በምድርም በረከት ላይ ይኖረዋል፤ እግዚአብሔርም በያዕቆብም ርስት ይመግበዋል፤ እርሱ እግዚአብሔር ተናግሯልና”፡፡
፬ኛ የአምልኮ መንገድ ነው፤
የሐዋርያት ሥራ ፲፫፡፩-፪ ላይ እንደተገለጸው መንፈስ ቅዱስ ለሥራ የጠራቸውን በርናባስንና ሳውልን ያሰናበቷቸውም በጾምና በጸሎት ነበር፡፡ በዚያም ጊዜም ከጾሙ፤ ከጸለዩ፤ እጃቸውንም ከጫኑ በኃላ አሰናበቷቸው፡፡ አንድ ሰው የአምልኮ መንገድ ሲጀምር መጾም መጸለይ እንዳለበት እራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን፤ ጾም የአምልኮ መንገድ ስለሆነች ነው፡፡ ሐዋርያትንም የጠፋውን ትውልድ ለመፈለግ ሐዋርያዊ ጉዞ ከማድረጋቸው በፊት ጾመዋል፡፡
፭ኛ አጋንትን የምናወጣበት እና ርኩሳን መናፍስትን የምንዋጋበት መሣሪያችን ነው፤ማር ፱፡፳፱ ጌታችን ደቀመዛሙርቱ ማውጣት አቅቷቸው የነበረውን ጋኔን እርሱ ካወጣው በኋላ ወደ እርሱ ቀርበው “እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለምን ነው?” ብለው በጠየቁት ጊዜ ስለ እምነታቸው ማነስ መሆኑን ነገራቸው:: “ይህ ወገን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም’ ነው ያላቸው፡፡ ስለሆነም ያለ ጾምና ጸሎት አጋንንት ማውጣት አይቻልም፡፡ ጾምን እየነቀፉና እያጥላሉ እንዲሁም በተግባር ሳይጾሙ አጋንንት እናወጣለን ማለት፤ የአጋንንት መዘባበቻና መጫወቻ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡