በጥምቀት በዓል የሃይማኖት አባቶች የሰላም ጥሪያቸውን አስተላለፉ!
ሕይወት ሳልለው
የጥምቀት በዓል አከባበር በጃንሜዳ እና በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በድምቀት በተከበረበት ቀን፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ለቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ባስተላላፉት መልእክት ላይ ምእመናን በተለይም ወጣቶች በፍቅርና በመቻቻል መኖር እንዳለባቸው አሳሰቡ፡፡“የዛሬ ፵ ዓመት የሆነውን ዓይነት አካሄድና ታሪካዊ ስሕተት እንዳትፈጽሙ ተጠንቀቁ! የምትሹትንና የምትመኙትን ማግኘት የምትችሉት አንድነትና ሰላም እስካለ ብቻ ነው፡፡ አርቆ በማየትና አስተውሎ በመራመድ፤በትዕግሥትና በመቻቻል ሳይሆን በኃይልና በጉልበት የምንፈልገውን ማግኘት እንችላለን ብላችሁ ከሆነ ሁሉንም ልታጡ ትችላላችሁና አስተውሉ!” በማለት ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፤ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ ፤ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ፤እንዲሁም የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኂሩት ካሣው፤ ረ/ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ የአዲስ አበባ ከተማ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና ከተለያዩ ሥፍራዋች ለመጡ ምእመናን መልካም የጥምቀት በዓልን የተመኙት ፓትርያኩ፤ ይህ በዓል የንስሓ ጥሪ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡‹‹መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ››፤ብሎ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እንዳስተማረን፤በዚህ አስከፊ ዘመን የንስሓን አስፈላጊነት መረዳትና መተግበር እንዳለብን አሳስበዋል፡፡
በዓለ ጥምቀት በዋነኛ የመዳን ሥርዓት መጀመሪያ መሆኑና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥር ፲፩ ቀን በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ እኛ እንድንጠመቅ እንዳስተማረን ‹‹ወውእቱ ያጠምቀክሙ በመንፈስ ቅዱስ ወበእሳት፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤››ተብሎ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፲፮ ላይ እንደ ተገለፀውም ለእኛ ድኅነት ሆኖልናል፡፡
‹‹ጥምቀት ማለት ሰፋ ያለ ትርጒም ቢኖረውም ምሥጢራዊ ትርጒሙን ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው መንፃት፤መለወጥ፤ መሻገር፤ አዲስ ሕይወት፤ አዲስ ልደት፤ አዲስ ምሕረት የሚሉትን ሐሳቦች ያመሰጥራል›› በማለትም ቅዱስ ፓትርያርኩ አብራርተዋል፡፡ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ማርቶማ የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ሶርያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፤የቅዱስነታቸውን ሐሳብ በመደገፍ እንዲህ በማለት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
‹‹ይህ በዓል የብርሃን በዓል ቢሆንም እኛ እንደምናውቀው ዓለማችን በድቅድቅ ጨለማ የምትገኝ ሲሆን ለዚህ ጨለማ ብርሃን ያስፈልገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ተስፋ ናት፡፡ ምክንያቱም ይህን የመሰለ በዓል በየትኛውም ዓለም አይከበርምና፡፡እኛም በዚህ ታላቅ በዓል ወቅት በጸሎት ከእናንት ጋር ነን፤››በማለት ከማጽናናታቸውም በተጨማሪ በክርስቲያኖች መካከል መልካም የሆነና የጠነከረ ግንኙነት ሰላም እንዲኖር ያደረገ እግዚአብሔርን ዘወትር እንደሚያመሰግኑና እግዚአብሔር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲጠብቅልንና ኢትዮጵያን እንዲባርክ በመመኘት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡