አርዮስ እና መንፈቀ አርዮሳውያን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱት ችግር – ክፍል ሦስት
በቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል
ኅዳር ፲፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
በስብሰባው ላይ አርዮሳውያን በኒቆምዲያው ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስ አማካይነት የሃይማኖት መግለጫ (confession of faith) አቀረቡ፡፡ የተሰበሰቡት አባቶች አብዛኛዎቹ በጩኸትና በቁጣ ድምፅ የእምነት መግለጫውን ተቃወሙት፡፡ ጽሑፉንም በእሳት አቃጠሉት፡፡ ከዚህ በኋላ የቂሣርያው አውሳብዮስ በሀገረ ስብከቱ በጥምቀት ጊዜ የሚጠመቁ ሁሉ የሚያነቡት የሃይማኖት ጸሎት (መግለጫ) አቀረበ፡፡ ይህ መግለጫ ከኒቅያው የሃይማኖት ጸሎት ጋር ተመሳሳይነት ስለነበረው ለጊዜው ተቀባይነትን አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ‹‹ዋሕደ ባሕርይ ምስለ አብ›› ወይም ‹‹ዘዋሕድ ምስለ አብ በመለኮቱ›› (omoousios) የሚለውን አገላለጽ ባለማካተቱ ጠንከር ባሉ ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በስብሰባው ወቅት አርዮስ ትክክለኛ የእምነት አቋሙን እንዲገልጽ ተጠይቆ ‹‹ሀሎ አመ ኢሀሎ ወልድ፤ ወልድ ያልነበረበት ጊዜ ነበረ፡፡ አብ ወልድን ከምንም (እምኀበ አልቦ) ፈጠረውና የእግዚአብሔር ልጅ አደረገው፡፡ አብም ወልድን ከፈጠረው በኋላ ሥልጣንን ሰጥቶት ዓለሙን ሁሉ እንዲፈጥር አደረገው፤›› ብሎ ሲናገር አብዛኞቹ የጉባኤው አባላት በጌታችን ላይ የተናገረውን የጽርፈት (የስድብ) ቃል ላለመስማት ጆሯቸውን ሸፈኑ ይባላል፡፡
በክርክሩ ጊዜ ‹‹ወልደ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት ነው፤ አዳኛችን ነው፡፡ አዳኝ መሆኑን ካመንን የባሕርይ አምላክነቱን ማመን አለብን፡፡ የሚያድን እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት የወልድ አምላክነት ከሰው ልጆች የመዳን ምሥጢር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ወልድ የባሕርይ አምላክ ካልሆነ ግን እኛም አልዳንም ማለት ነው፡፡ በእርሱ መዳናችንን ካመንን ግን ያዳነን እርሱ አምላክ መሆኑን ማወቅና ማመን አለብን፡፡ ፍጡር ፍጡራንን ማዳን አይችልምና፤›› ብሎ አትናቴዎስ አርዮስን ሲጠይቀውና ሲከራከረው የሰሙት አብዛኞቹ የጉባኤው አባላት በደስታ ተዋጡ፡፡ አርዮስ ‹‹ወልድ በምድር ሕይወቱ ታላቅ ትሕትናንና ተጋድሎን በማሳየቱ በባሕርይ ሳይሆን በጸጋ የአምላክነትን ክብር ስላገኘ ስግደት ይገባዋል፤›› ይላል፡፡ አትናቴዎስም ‹‹ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር አንድ ነው፡፡ ነገር ግን ‹ወልድ ፍጡር ነው› ካልን ለእርሱ የአምልኮ ስግደት ማቅረብ አማልኮ ባዕድ ነዋ!›› ሲለው አርዮስ መልስ አላገኘም፡፡
ከአርዮሳውያን ጋር የከረረ ክርክር የተደረገው በሁለት ጉዳዮች ነበር፤ እነዚህም ፩ኛ አርዮስ ወልድን ‹‹ፍጡር ነው›› ለማለት ‹‹ሀሎ አመ ኢሀሎ ወልድ፤ ወልድ ያልነበረበት ጊዜ ነበር›› ሲል ኦርቶዶክሳውያን ወልድን ዘለዓለማዊ ነው ለማለት ‹‹አልቦ አመ ኢሀሎ ወልድ፤ ወልድ ያልኖረበት ጊዜ የለም›› ብለው የአርዮሳውያንን ክሕደት አጥላልተው አወገዙት፡፡ ፪ኛ አርዮስና ደጋፊዎቹ ‹‹ወልድ በባሕርዩ (በመለኮት) ከአብ ጋር አንድ አይደለም፤›› የሚሉትን ጉባኤው ካወገዘ በኋላ፣ ኦርቶዶክሳውያን ወልድን “Omo-ousios” (ዋሕደ ባሕርይ ምስለ አብ ወይም ዘዋሕድ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ወልድ ከአብ ጋር በባሕርዩ በመለኮቱ አንድ ነው)›› አሉ፡፡ የአርዮስ ደጋፊዎች የነበሩትም የአርዮስን የክሕደት ትምህርት ያልተቀበሉ በማስመሰልና ኦርቶዶክሳውያን በመምሰል “Omoi-ousios” (የወልድ ባሕርይ ከአብ ባሕርይ ጋር ተመሳሳይ ነው) ብለው ሐሳብ አቀረቡ፡፡ የእነዚህንም ሐሳብ ጉባኤው ፈጽሞ አልተቀበለውም ነበር፡፡ እነዚህም መንፈቀ አርዮሳውያን (Semi-Arians) ተብለው ተወግዙ፡፡
“Omo-ousios” (ዋሕደ ባሕርይ ምስለ አብ በመለኮቱ ወይም ዘዋሕድ ምስለ አብ በመለኮቱ) የሚለውን ሐረግ አርዮሳውያንና መንፈቀ አርዮሳውያን አጥብቀው ተቃውመውት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ የኮርዶቫው ኤጲስቆጶስ ኦስዮስና የእስክንድርያው ሊቀ ዲያቆን አትናቴዎስ ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት “Omo-ousios” (ዋሕደ ባሕርይ ምስለ አብ በመለኮቱ ወይም ዘዋሕድ ምስለ አብ በመለኮቱ ወይም ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ) የሚለው ሐረግ ተጨምሮበት፣ የወልደ አብ ኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የሚያረጋግጥ ፯ አናቅጽ ያሉት ቃለ ሃይማኖት (ጸሎተ ሃይማኖት) ተዘጋጅቶ ቀረበና የጉባኤው አባቶች ሁሉ ፈረሙበት፡፡ ከጸሎተ ሃይማኖት ፯ አንቀጾች መካከል የመጀመሪያው አንቀጽ የሚከተለው ነው፤
‹‹ሁሉን በያዘ፣ ሰማይንና ምድርን፣ የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፡፡ ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ በተወለደ፣ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፡፡ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፣ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሚሆን፣ ሁሉ በእርሱ የሆነ (የተፈጠረ) በሰማይም በምድርም፡፡ ስለ እኛ ስለ ሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ የወረደ፤ ሥጋ የሆነ፡፡ ሰው ሆኖም ስለ እኛ የታመመ፡፡ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ የተነሣ፡፡ ወደ ሰማይ የዐረገ፡፡ በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ዳግመኛ የሚመጣ፡፡ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን፡፡››
በመጨረሻም ከዚህ በላይ እንደተገለጠው ጉባኤው የወልድን አምላክነትና በባሕርይ (በመለኮት) ከአብ ጋር አንድ መሆኑን በውል አረጋግጦና ወስኖ አርዮስንና መንፈቀ አርዮሳውያንን አውግዞ ከማኅበረ ክርስቲያን ለይቷቸዋል፡፡ አርዮስና የተወገዙት አርዮሳውያን ሁሉ በንጉሠ ነገሥቱ እንዲጋዙ ተደርገዋል፡፡
፪. በኢትዮጵያ ጸሎተ ሃይማኖት በተለይ የ‹‹Omoousios tw patri›› ትርጕም
‹‹Omoousios tw patri›› የሚለው የግሪኩ ሐረግ በግእዝ የተተረጐመው ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ›› ተብሎ ሲሆን፣ በአማርኛው ነጠላ ትርጕም ግን ‹‹በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል›› ተብሎ ነው የተተረጐመው፡፡ የግሪኩ ቃል የሚገልጠው ‹‹በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሚሆን›› ማለትን ነው፡፡ ‹‹የሚተካከል›› የሚለው ቃል ግን የግሪኩንም ሆነ የግእዙን ሐረግ አይወክልም፡፡ እንዳውም ‹‹መተካከል›› የሚለው ቃል መመሳሰልን ወይም ምንታዌን (ሁለትዮሽን) ነው እንጂ አንድነትን አይገልጥም፡፡ ይህ ደግሞ የመንፈቀ አርዮሳውያንን ሐሳብ ስለሚመስል የኢትዮጵያ ሊቃውንት የአማርኛውን ትርጕም እንደገና ሊያስቡበት ይገባል፡፡ በእርግጥ ‹‹ዐረየ›› ማለት ‹‹ተካከለ›› ማለት ነው፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደሚሉት በሌላ መንገድ ግን ‹‹ዐረየ›› የሚለው ግስ ‹‹አንድ ሆነ›› የሚል ትርጕም አለው፡፡ ለምሳሌ ‹‹ወምስለ ብሉይ ኢይዔሪ›› የሚለው ኃይለ ቃል ‹‹ከአሮጌው ጋር አንድ አይሆንም›› ተብሎ ይተረጐማል፡፡ እንደዚሁም በመዝሙረ ዳዊት ‹‹እስመ ተማከሩ ኅቡረ ወዐረዩ›› የሚለው ኃይለ ቃል ‹‹አንድ ሆነው በአንድነት ተማክረዋልና›› የሚል ትርጕም አለው፡፡
ስለዚህ ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ›› የሚለው ሐረግ ‹‹በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሚሆን›› ተብሎ መተርጐም አለበት፡፡ ‹‹በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል›› ከተባለ ግን ይህ መንፈቀ አርዮሳዊ አነጋገር ይሆናል፡፡ ምክንያቱም መንፈቀ አርዮሳውያን ‹‹ወልድ ከአብ ጋር በመለኮት ይመሳሰላል እንጂ አንድ አይደለም›› ነው የሚሉት፡፡ ሃይማኖተ አበውን የተረጐሙ አባቶችም ‹‹ዐረየ›› ወይም ‹‹ዕሩይ›› የሚለውን ቃል ‹‹አንድ የሆነ›› ብለው ነው የተረጐሙት፡፡ ለምሳሌ ‹‹ወውእቱ ዕሩይ ምስሌሁ በመለኮት›› የሚለውን ሲተረጕሙ ‹‹እርሱም በመለኮት ከአብ ጋር አንድ ነው›› ብለውታል፡፡ እንደዚሁም ‹‹ነአምን በሥላሴ ዕሩይ በመለኮት›› ሲተረጐም ‹‹በመለኮት አንድ በሚሆኑ በሥላሴ እናምናለን›› ተብሎ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ‹‹ወበከመ ወልድ ዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ›› የሚለው ኃይለ ቃል ትርጕም ‹‹ወልድ በባሕርዩ ከአብ ጋር አንድ እንደ ሆነ›› ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም የቅዳሴው የአንድምታ ትርጕም ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ›› የሚለውን ኃይለ ቃል የተረጐሙት ሊቅ ‹‹ከአብ ጋር በመለኮቱ አንድ የሚሆን›› በማለት ነው፡፡
እንግዲህ ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ›› የሚለው ኃይለ ቃል ‹‹ከአብ ጋር በመለኮቱ አንድ የሚሆን›› ተብሎ ከተተረጐመ ምንም የእምነት ጕድለት ወይም ስሕተት አይኖረውም፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስም ይህን ኃይለ ቃል ‹‹ዘዕሩይ – የሚተካከል›› ተብሎ እንዳይተረጐም ብለው ‹‹ዘዋሕድ ምስለ አብ በመለኮቱ›› በማለት አርመዉታል፡፡ ትርጕሙ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ‹‹ዘዕሩይ›› የሚለው ቃል የወጣበት ‹‹ዐረየ›› የሚለው ግስ ከላይ እንደተገለጸው ‹‹አንድ ሆነ›› የሚል ትርጕም ስላለው ‹‹ዘዕሩይ›› የሚለው ግእዙ ባይለወጥ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ መስተካከል ያለበት ግእዙ ሳይሆን የአማርኛው ትርጕም ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስም በዋናው ጸሎተ ሃይማኖት ላይ ‹‹ዘዕሩይ›› የሚለውን ቃል ሳያርሙ እንዳለ አስቀምጠውታል፡፡
ይቆየን