ደብረ ታቦር አምሳለ ቤተ ክርስቲያን – ካለፈው የቀጠለ
በመምህር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ
ነሐሴ ፲፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
እንደዚሁም ተራራ ሲወጡት አድካሚ እንደ ኾነ መንግሥተ ሰማያትም በብዙ ድካም ትወረሳለች፡፡ ‹‹እስመ በብዙኅ ጻማ ሀለወነ ንባእ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ አለን›› እንዲል (ሐዋ. ፲፬፥፳፫)፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጸበት ምክንያት ምሥጢር በብዙ ድካም እንጂ ምንም ሳይደክሙ እንደማይገኝ ሲገልጽ ነው፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹን ምሥጢራት የገለጠላቸው ከከተማ ውጭ ነው፡፡ ቀደም ሲልም ለሙሴ የቃል ኪዳኑን ጽላት ሲሰጠው ወደ ሲና ተራራ በመጥራት ነበር፡፡ ነገረ ሥጋዌዉንም በነበልባልና በእሳት አምሳል የገለጠለት በኮሬብ ተራራ በጎቹን አሰማርቶ በነበረበት ጊዜ እንደ ኾነ መጻሕፍት ይመሰክራሉ (ዘፀ. ፫፥፩)፡፡
ምሥጢር ይገለጥልን ባላችሁ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገስግሱ፤ ቤተ ክርስቲያንን ደጅ ጽኑ ለማለት ጌታችን ምሥጢሩን በተራራ ገለጠ፡፡ ወደ ተራራው ሲወጣም ስምንቱን ደቀ መዛሙርቱን ከይሁዳ ጋር ከተራራ እግር ሥር ትቶ ሦስቱን አስከትሎ ወጥቷል፡፡ ለሦስቱ በተራራው ላይ የተገለጠው ድንቅ ምሥጢርም ከእግረ ደብር ላሉት በሳምንቱ ተገልጧል፤ ከይሁዳ በቀር፡፡ ለዚህ ምሥጢር ብቁ ያልነበረው ይሁዳ ብቻ ነው፡፡ ይህም ተገቢውን ምሥጢር ለተገቢው ሰው መንገር እንደሚገባ፤ ለማይገባው ደግሞ ከመንገር መቆጠብ ተገቢ እንደ ኾነ ያስተምረናል፡፡ ‹‹እመኒ ክዱን ትምህርትነ ክዱን ውእቱ ለሕርቱማን ወለንፉቃን …፤ ወንጌላችን የተሰወረ ቢኾንም እንኳን የተሰወረባቸው ለሚጠፉት ነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚመስለው የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው የዚህ ዓለም አምላክ ልባቸውን አሳውሯልና፤›› (፪ኛ ቆሮ. ፬፥፫-፭) በማለት ሐዋርያው የሰጠው ትምህርትም ይህን መሰል ምሥጢር ለሚገባው እንጂ ለማይገባው ሰው መግለጥ ተገቢ አለመኾኑን የሚያስረዳ ነው፡፡
፪ኛ የድል ተራራ ስለ ኾነ
ነቢዪቱ ዲቦራ የእስራኤል ጠላት የነበረው የኢያቢስን የሠራዊት አለቃ ሲሣራን ለመውጋት ወደ ደብረ ታቦር ዐሥር ሺሕ ሰዎችን አስከትሎ እንዲወጣ ለባርቅ ነግራዋለች (መሳ. ፬፥፮)፡፡ በዚህ መልኩ ባርቅ ዐሥር ሺሕ ሰዎችን አሰልፎ ዲቦራን አስከትሎ በደብረ ታቦር ሰፍሮ የነበረውን የሲሣራን ሠራዊት ድል ነሥቶበታል፡፡ ሲሣራ ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገላ እንደዚሁም ብዙ ሠራዊት በታቦር ያሰለፈ ቢኾንም ድል ግን ረድኤተ እግዚብሔርን ጥግ ላደረገው ለባርቅ ኾነ፡፡ በዚህ ጊዜ ዲቦራ በታቦር ተራራ የሙሴ እኅት ማርያም በኤርትራ ባሕር የዘመረችውን መዝሙር የመሰለ ምስጋና አቅርባለች፡፡ ዅሉም እስራኤላውያን የድል መዝሙር ዘምረውበታል፤ ፈጣሪአቸውን አመስግነውበታል፡፡ ጌታችንም የባሕርይ አምላክነቱን ገልጾ ከደቀ መዛሙርቱ ልቡና አጋንንትን የሚያባርርበት ዲያብሎስን ድል የሚነሳበት ስለኾነ ከሌሎች ተራሮች ተመርጧል፡፡
፫ኛ ትንቢት ስለ ተነገረለት
‹‹ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ ወይሴብሑ ለስምከ፤ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል፤›› (መዝ. ፹፰፥፲፪) ብሎ ከክርስቶስ ሰው ኾኖ መገለጥ በፊት አምላካችን ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር እንደሚገልጽ፣ ብርሃኑ ከደብረ ታቦር እስከ አርሞንኤም ድረስ እንደሚታይ፣ ይህም መለኮታዊ ብርሃን በታቦርና በአርሞንኤም ዙሪያ ለነበሩ ሕዝቦች ደስታ እንደሚኾን ቅዱስ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ታቦር የተባለው ተራራ ከገሊላ ባሕር በምዕራብ በኩል በ፲ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲኾን ተራራው እስከ ፭፻፸፪ ሜትር ከባሕር ጠለል (ወለል) ከፍ ይላል፡፡
ቀደም ሲል እንደገለጽነው ባርቅ ሲሣራን ድል ነስቶበታል፤ የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሳዖል በሳሙኤል እጅ ተቀብቶ ሲመለስ ‹‹ሦስት ሰዎች ታገኛለህ አንዱ ሦስት የድል ጠቦቶች፣ ሁለተኛው ሦስት ዳቦ ይዟል፤ ሦስተኛውም የወይን ጠጅ አቆማዳ ይዟል፡፡ ሰላምታ ይሰጡሃል›› ብሎ ሳሙኤል ነግሮት ነበር፡፡ በነገረው መሠረት ሦስት ሰዎችን አግኝቶበታል (፩ኛ ሳሙ. ፲፥፫-፭)፡፡ ስለዚህ ተራራ ቅዱስ ዳዊት በድጋሜ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናግሮለታል፤ ‹‹የእግዚአብሔር ተራራ የለመለመ ተራራ ነው፡፡ የጸና ተራራ የለመለመ ተራራ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህን ተራራ ያድርበት ዘንድ ወደደው›› (መዝ. ፷፯፥፲፭) ብሎ እግዚብሔር ብርሃነ መለኮቱን እንደሚገልጥበት ዘምሮአል፡፡ በእነዚህ ከላይ በአየናቸው ሁለት ምክንያት ደብረ ታቦር ለዚህ ምሥጢር ተመርጧል፡፡
ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠው በምን ምክንያት ነው?
ነሐሴ ሰባት ቀን በቂሣርያ ደቀ መዛሙርቱን ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?›› ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ‹‹ኤርምያስ ነው፤ ኤልያስ ነው፤ ዮሐንስ መጥምቅ ነው፤ ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል›› የሚል የተለያየ መልስ ሰጥተዉት ነበር፡፡ ‹‹እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?›› ባላቸው ጊዜም ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ›› ብሎ መስክሯል፡፡ ስለዚህ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠው በሦስት ምክንያት ነው፤
፩ኛ በፍጡር ቃል የተመሰከረውን እውነት በባሕርይ አባቱ ለማስመስከር፤
፪ኛ ‹‹ከነቢያት አንዱ ነው›› ብለውት ነበርና እግዚአ ነቢያት (የነቢያት ጌታ) እንደ ኾነ ለማስረዳት፤
፫ኛ ክርስቶስ ‹‹እሰቀላለሁ፤ እሞታለሁ›› ባለ ጊዜ፣ ጴጥሮስ ‹‹ሐሰ ለከ፤ ልትሞት አይገባህም›› ብሎት ነበርና ‹‹እርሱን ስሙት›› የሚለዉን የእግዚአብሔር አብን መልእክት ለማሰማት፡፡
በፍጡሩ በጴጥሮስ የተመሰከረውን ምስክርነት የባሕርይ አባቱ ‹‹ይህ የምወደው ልጄ ነው፤ እርሱን ስሙት›› ማለት ‹‹‹እሞታለሁ፤ እሰቀላለሁ› ቢላችሁ ‹አይገባህም› አትበሉት፡፡ ዓለም የሚድነው በእርሱ ሞት ነውና ተቀበሉት›› ለማለት ነው፡፡ ‹‹ይህ ሊኾንብህ አይገባም›› ብሎት ነበርና ለጴጥሮስ መልስ እንዲኾን፡፡ ያዕቆብና ዮሐንስም ‹‹አንዳችን በቀኝህ አንዳችን በግራህ እንሾም›› ብለው ነበርና ፍቅረ ሲመትን ሊያርቅላቸውና የእርሱን የባሕርይ ክብሩን አይተው የመጣለት ዓላማ ልዩ መኾኑን እንዲረዱ ሲያደርጋቸው እነዚህን ሦስቱን ይዞ ወደ ተራራው ወጥቷል፡፡ ‹‹ከነቢያት አንዱ ነው›› ብለውት ነበርና ከነቢያት ሙሴንና ኤልያስን በተራራው ተገኝተው እንዲመሰክሩ አድርጓል፡፡ ሙሴ ‹‹የእኔ የሙሴን አምላክ ‹ሙሴ› የሚልህ ማነው? አምላከ ሙሴ፣ እግዚአ ሙሴ ይበሉህ እንጂ››፤ ኤልያስም ‹‹የእኔን አምላክ ‹ኤልያስ› የሚልህ ማነው? አምላከ ኤልያስ፣ እግዚአ ኤልያስ ይበሉህ እንጂ›› በማለት መስክረውለታል፡፡
ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠው እንዴት ነው?
ይህን ጥያቄ ለማብራራትም ኾነ ለመተንተን ዕውቀትም ቃላትም ያጥረናል፡፡ ወንጌላውያን መግለጥ በሚችሉት መጠን ከገለጹት ያለፈ ልናብራራው የምንችለው አይደለም፡፡ ማቴዎስ እንዲህ ይገልጸዋል፤ ‹‹ወተወለጠ ራዕዩ በቅድሜሆሙ ወአብርሀ ገጹ ከመ ፀሐይ ወአልባሲሁኒ ኮነ ፀዐዳ ከመ በረድ፤ በፊታቸውም ተለወጠ፡፡ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ኾነ፤›› (ማቴ. ፲፯፥፪)፡፡ ወንጌላዊው በዚህ ዓይነት መንገድ የገለጸው ምሳሌ ስላጣለት ነው፡፡ ማርቆስም ይህንኑ ኃይለ ቃል ተጋርቶ ‹‹ልብሱም አንፀባረቀ፤ አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ኾነ፤›› (ማር. ፱፥፪) በማለት ሲገልጸው፣ ሉቃስም በተመሳሳይ መልኩ ‹‹የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ኾነ›› ሲል ገልጾታል (ሉቃ. ፱፥፳፱-፴)፡፡ እኛም ከዚህ ወንጌላውያን ከገለጹበት መንገድ የሚሻል ምሳሌ አናገኝለትም፡፡
ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር በገለጠ ጊዜ ፊቱን ማየት ተስኗቸው ነቢያት ወደየመጡበት መመለሳቸውን ሲያመላክቱ ኢትዮጵያዊቷ የቅኔ መምህርት እማሆይ ገላነሽ በቅኔአቸው እንዲህ በማለት አመሥጥረውታል፤
‹‹በታቦርሂ አመ ቀነፀ መለኮትከ ፈረስ
ኢክህሉ ስሒቦቶ ሙሴ ወኤልያስ››
ትርጕሙም፡- ‹‹መለኮት ፈረስህ በደብረ ታቦር በዘለለ ጊዜ ሙሴና ኤልያስ ሊስቡት አልቻሉም›› ማለት ሲኾን፣ ይህም ክርስቶስ በምን ዓይነት ግርማ እንደ ተገለጸ ያስረዳል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡