የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት በአፋን ኦሮሞ
ሐምሌ ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሒዱና አሕዛብን ዅሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ዅሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው›› (ማቴ. ፳፰፥፲፱) ሲል በአምላካዊ ቃሉ ያዘዘውን መሠረት በማድረግና የቅዱሳን ሐዋርያትን ፈለግ በመከተል ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በርካታ ሰባክያንን እያስተማረች በየቦታው ስታሰማራ ኖራለች፤ ወደፊትም ይህንን ተልእኮዋን አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡ ምክንያቱም ስብከተ ወንጌል ቃለ እግዚአብሔርን ለማስተማር ብቻ ሳይኾን የሰውን አእምሮ ለማልማት (መልካም አስተሳሰብን ለመገንባት) የሚያስችል ዋነኛው የቤተ ክርስቲያን መሣርያ ነውና፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሥራቿ የዅሉም አምላክ፣ የዅሉም ጌታ፣ የዅሉም መድኀኒት የኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና እንደ ጌታዋ ዘር፣ ጎሣ፣ ቀለም፣ ጾታ ሳትለይ በተዋሕዶ ሃይማኖት ጥላ ሥር የተሰባሰቡ ምእመናንን በአንድነት ተቀብላ ታስተናግዳቸዋለች፡፡ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መፋጠን በልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፍ የሚሳተፉ ልጆቿም ይህንኑ ዓላማዋን ለማሳካት የመትጋት መንፈሳዊ ግዴታ አለባቸው፡፡ ‹‹ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው፤ እነሆም ያማረ ነው፤›› (መዝ. ፻፴፪፥፩) ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተጻፈው፣ በዓለማዊ ብሂልም ‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኀኒቱ›› እንደሚባለው በኅብረት በመሰባሰብ የሚፈጸም መንፈሳዊ ተግባር ውጤታማነቱ የሠመረ ነው፡፡
በማኅበር ተሰባስበው መንፈሳዊ አገልግሎት ከሚሰጡ ማኅበራት መካከል አንዱ የኾነው፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ክፍተት ለመሸፈን የሚያስችል መንፈሳዊ ዓላማ እና ርእይን ሰንቆ በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተመሠረተው ማኅበረ ቅዱሳንም ለሃያ አምስት ዓመታት ያህል ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በትጋት ሲያገለግል እስከ ዛሬ ድረስ ቆይቷል፡፡ ለወደፊቱም እግዚአብሔር እስከፈቀደለት ጊዜ ድረስ አገልግሎት መስጠቱን ይቀጥላል፡፡ በልዩ ልዩ መገናኛ መንገዶች እንደሚገለጸው ማኅበረ ቅዱሳን ከአመሠራረቱ ጀምሮ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን አስፋፍታ፣ መንፈሳዊ ዓላማዋን ከግብ አድርሳ፣ ከችግሮቿ ወጥታ ለሕዝቦቿ መንፈሳዊና ማኅበራዊ የሕይወት ለውጥ ቀዳሚ ሚናዋን እንድትወጣ ለመደገፍ የሚተጋ መንፈሳዊ ማኅበር ነው፡፡
ማኅበሩ በየግቢ ጉባኤያቱ ትምህርተ ሃይማኖትን ከሚያስተምራቸው ወንድሞችና እኅቶች በተጨማሪ ከአባቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር በልዩ ልዩ የአገራችን ክፍሎች የሚገኙ ሰባክያነ ወንጌልን በየቋንቋቸው እያሠለጠነ፣ በአባቶች ቡራኬ እያስመረቀ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲሠማሩ አድርጓል፡፡ በእነዚህ ሰባክያን አገልግሎትም ከሰማንያ አምስት ሺሕ ሰባት መቶ የሚበልጡ በልዩ ልዩ ጠረፋማ አካባቢዎች የሚኖሩ አዳዲስ አማንያን የሥላሴ ልጅነትን አግኝተዋል፡፡ በዚህ መልኩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እያገለገለ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን በአጠቃላይ በልዩ ልዩ ቋንቋ በርካታ መንፈሳውያን ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ‹‹ይህን ሠርቻለሁ›› ብሎ መናገር ተገቢ ባይኾንም፣ ለቍጥጥር እና ለግምገማ ያመች ዘንድ ማኅበሩ በየጊዜው የአገልግሎት ሪፖርት ያቀርባል፡፡ በዚህ ጽሑፍም በአፋን ኦሮሞ የሚሰጠውን አገልግሎት በሚመለከት አጠር ያለ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መልእክት ይዘን ቀርበናል፡፡
የተወደዳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ምእመናን!
ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎቱን ሲጀምር ከነበረበት የሰው ኃይል እና እጥረት አኳያ በአማርኛ ቋንቋ በመጽሔት፣ በጋዜጣ፣ በበራሪ ወረቀት፣ በመጻሕፍት፣ በካሴት፣ በምስል ወድምፅ የሚቻለውን ዅሉ መንፈሳዊ ተግባር ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ የምእመናን ፍላጎት እየጨመረ፤ ማኅበሩም በሰው ኃይል እየተጠናከረ በመምጣቱ አገልግሎቱን ይበልጥ አሳድጎ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ፣ በወላይትኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በመሳሰሉት የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ቋንቋዎች ወንጌልን ለማስተማር በመፋጠን ላይ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በአፋን ኦሮሞ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-
- በግእዝና አማርኛ ቋንቋዎች የታተሙ የትምህርተ ሃይማኖት እና የጸሎት መጻሕፍትን ወደ አፋን ኦሮሞ አስተርጕሟል፤ ከእነዚህ መካከል የዘወትር ጸሎት፣ ውዳሴ ማርያም፣ ውዳሴ አምላክ እና ሰይፈ ሥላሴ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
- ሌሎች አዳዲስ መጻሕፍትንም በቋንቋው አዘጋጅቶ አሠራጭቷል፡፡
- በሦስት ወር አንድ ጊዜ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የምትዘጋጀው ጉባኤ ቃና መጽሔትን ወደ ቋንቋው አስተርጕሞ በየግቢ ጉባኤያቱ አሠራጭቷል፡፡
- Dhangaa Lubbuu (ዳንጋ ሉቡ) የተሰኘችውን መጽሔት ለዅሉም ክርስቲያን በሚመጥን ዐምድ በየሦስት ወሩ በማዘጋጀት እያሠራጨ ይገኛል፡፡
- በአፋን ኦሮሞ አራት የመዝሙር አልበሞችን አሠራጭቷል፤ ኦርቶዶክሳዊ የመዝሙር ጥራዝም አሳትሟል፡፡
- ልዩ ልዩ የቪሲዲ ስብከቶችንና መዝሙሮችን አዘጋጅቶ ለምእመናን እንዲዳረሱ አድርጓል፡፡
- በክልሉ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን አገልግሎትና ታሪክ የተመለከቱ ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን አዘጋጅቶ አሳትሟል፡፡
- በአፋን ኦሮሞ ለሚያስተምሩ ሰባክያነ ወንጌል በዐሥራ ሦስት ዙር የክረምት ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፤ በዚህ ዓመትም ከዘጠና በላይ አገልጋዮችን ለማሠልጠን ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
- ከአሁን በፊት በአፋን ኦሮሞ የሚተላለፍ ሳምንታዊ መንፈሳዊ የቴሌቭዥን መርሐ ግብር እያዘጋጀ ሲያቀርብ የቆየ ሲኾን፣ ለወደፊቱም ይህንኑ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
- መካነ ድር ከማዘጋጀት ባሻገር ወቅታዊ ትምህርት የሚሰጥበት ወርኃዊ ጉባኤ በማካሔድም ሕዝበ ክርስቲያኑን በአፋን ኦሮሞ ወንጌልን በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡
- በአገራችን ግቢ ጉባኤያት ካሏቸው ዐርባ ሰባት ማእከላት በሠላሳ ስምንቱ የአፋን ኦሮሞ መርሐ ግብር እንዲኖርና ተማሪዎች በቋንቋቸው ኮርስ እንዲማሩ፣ የጽዋ እና ጸሎት መርሐ ግብራት እንዲያካሔዱ፣ መዝሙራትን እንዲያጠኑና እንዲያቀርቡ አድርጓል፤ በማድረግ ላይም ነው፡፡
- በተጠኑ የክልሉ ቦታዎች አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በመመሥረት አፋን ኦሮሞ የሚችሉ ዲያቆናትና ካህናትን እንዲሁም ሰባክያነ ወንጌልን አስተምሮ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በማሠማራት ላይ ሲኾን ለዚሁም በምዕራብ ወለጋ የሚገኘውን የቂልጡ ካራ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና በጅማ ሀገረ ስብከት ሥር ያለውን የአበልቲ ኪዳነ ምሕረት ገዳማት የአብነት ትምህርት ቤቶችን እንደ ማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
- በግቢ ጉባኤያት የምረቃ መጽሔት ላይ ልዩ ልዩ ትምህርታዊ ጽሑፎችና መልእክቶችን በአፋን ኦሮሞ እያቀረበ ነው፡፡
- በክልሉ ያሉ ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች እንዲጠናከሩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በመተግበር፣ መምህራንና ደቀ መዛሙርትን በመደጎም፣ ቋንቋውን የሚችሉ ዲያቆናትና ካህናት እንዲፈሩ በማደረግ በርካታ የክልሉ ምእመናን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፣ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት ተከፍተው አገልግሎት እንዲሰጡ የበኩሉን አስተዋጽዖ አበርክቷል፤ የባሌ፣ የምሥራቅ ሐረርጌና የነገሌ ቦረና አህጉረ ስብከት አብነት ትምህርት ቤቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
- ከዚሁ ዅሉ ጋርም የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ሲያዘጋጅ ለኦሮምያ ክልል ቅድሚያ በመስጠት፣ የጉባኤው ተሳታፊዎችን በማስተባበር የገቢ እጥረት ላለባቸው የክልሉ አብያተ ክርስቲያናት በመቶ ሺሕ የሚቈጠር የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በመርሐ ግብሮቹ የሚቀርቡ ትምህርቶችንም በአፋን ኦሮሞ በማስተርጐም ለአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን አቅርቧል፡፡
ማኅበሩ ለወደፊት በአፋን ኦሮሞ ለመሥራት ካቀዳቸው ተግባራት መካከል ከፊሎቹ
- መንፈሳዊ የቴሌቭዥን እና የሬድዮ መርሐ ግብር ማዘጋጀት፣
- ወርኃዊ የሬድዮ መጽሔት ማዘጋጀት፣
- ዕቅበተ እምነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ልዩ ልዩ መጻሕፍትን ማሳተም፣
- ልዩ ልዩ ቅዱሳት መጻፍትን ወደ አፋን ኦሮሞ ማስተርጐም፣
- የሕፃናት መጻሕፍትንና መንፈሳዊ ፊልሞችን ማዘጋጀት፣
- ወጣቶች ምእመናን የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ጠንቅቀው እንዲያውቁ የሚያግዙ ማስተማሪያ አፕሊኬሽኖችን ማዘጋጀት ማኅበሩ በዕቅድ የያዛቸው ተግባራት ናቸው፡፡ በተጨማሪም የሬድዮና ቴሌቭዥን መርሐ ግብሮችን መከታተል ለማይችሉ የገጠር ምእመናን የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በሚኖሩበት ቦታ ኾነው ቃለ እግዚአብሔርን እንዲማሩ ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድም አለው፡፡
የተወደዳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ምእመናን!
ቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን ሓላፊነትና የአባቶችን አደራ ተቀብሎ ወንጌለ መንግሥትን በመላው ዓለም ለማዳረስ የሚተጋው ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ሥር ያለ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮና መሠረተ እምነት የሚጠብቅና የሚያስጠብቅ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀ ደንብ የተሰጠውና በደንቡ መሠረት ብቻ የሚመራ ማኅበር እንጂ ራሱን የቻለ የእምነት ተቋም አይደለም፡፡ አባላቱም ለአንድ መንፈሳዊ ዓላማ ከመላው ኢትዮጵያ የተሰባሰቡ የተዋሕዶ ልጆች እንጂ የአንድ አካባቢ ተወላጆችና አንድ ብቻ ቋንቋ ተናጋሪዎች አይደሉም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ምእመናን በሚሰሙት ቋንቋ ዅሉ ቃለ እግዚአብሔርን ተምረው ለመንግሥተ ሰማይ ይበቁ ዘንድ የሚጠበቅበትን መንፈሳዊና አገራዊ ድርሻ በአግባቡ ለመወጣት የሚሠራ፤ በአጠቃላይ ለመንፈሳዊ ተልእኮ የሚፋጠን ማኅበር ነው፡፡
ማኅበሩ በግልጽና በይፋ ከሚፈጽመው መንፈሳዊ አገልግሎት ውጪ በስውር የሚሠራው አንዳችም የተለየ ተልእኮ የለውም፡፡ ምእመናን በሚሰሙት ቋንቋ ቃለ እግዚአብሔርን እንዳይማሩም እንቅፋት አይፈጥርም፡፡ እንደዚህ ዓይነት አሠራርም በፍጹም የለውም፡፡ ማኅበሩ የዅሉንም ሕዝበ ክርስቲያን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ አሟልቻለሁ ባይልም ምእመናን በየቋንቋቸው ወንልን እንዳይማሩ አለማድረጉን፤ ለወደፊትም እንደዚህ ዓይነት ተልእኮ የሚፈጽም ማኅበር አለመኾኑን ቅዱስ ሲኖዶስ እና መላው ሕዝበ ክርስቲያን እንዲገነዘቡለት ያሳስባል፡፡ በመጨረሻም ማኅበረ ቅዱሳን በኦሮምያ ለሚገኙ ምእመናን ሰፊ አገልግሎት ለመስጠት ካለው ቁርጠኝነት የተነሣ የአፋን ኦሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት በሚል ስያሜ መርሐ ግብር አቋቁሞ፣ በጀት መድቦ በተጠናከረ መልኩ አገልግሎቱን በመፈጸም ላይ መኾኑን በዚህ አጋጣሚ እየገለጸ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን አገልግሎት ከዚህ በበለጠ መልኩ እንዲቀላጠፍ ለማድረግ ይቻል ዘንድም መላው ሕዝበ ክርስቲያን ማኅበሩ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀርባችሁ ደግፉ ሲል በእግዚአብሔር ስም መንፈሳዊ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!
ማኅበረ ቅዱሳን