የአዳማ ማእከል የሕክምና አገልግሎት ሰጠ፡፡
ግንቦት ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በአዳማ ማእከል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአዳማ ማእከል የቅዱሳት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ለሚገኙ አባቶችና እናቶች መነኮሳት እንዲሁም ለአብነት ተማሪዎች ግንቦት ፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የሕክምና አገልግሎት ሰጠ፡፡
በሕክምና አገልግሎቱም በአዳማ ማእከል፣ በደብረ ዘይት ወረዳ ማእከልና በአዱላላ ግንኙነት ጣቢያ የሚገኙ ስፔሻሊስት ሐኪሞች፣ ሜዲካል ዶክተሮች፣ የጤና መኮንኖች፣ የላቦራቶሪ ቴክኒሻኖች እና የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ግቢ ጉባኤ የሕክምና ተማሪዎች በአጠቃላይ ፴፰ የሕክምና ባለሞያዎች ተሳትፈዋል፡፡
በሕክምና አገልግሎቱም ለገዳሙ መነኮሳት እና አብነት ተማሪዎች ሙሉ የጤና ምርመራና የመድኃኒት ድጋፍም ተደርጓል፡፡ ለአባቶች መነኮሳትና ለእናቶች መነኮሳይያት የስኳር፣ የደም ግፊት እና የዓይን ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡ የመድኃኒት አቅርቦቱም ከዋናው ማእከል ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል እና ከአንድ በጎ አድራጊ ወንድም የተገኘ ነው፡፡ የአዳማ ኢዮር ክሊኒክ የመድኃኒትና የሕክምና መመርመሪያ መሣሪያ ከማቅረቡ ባሻገር የክሊኒኩ ስፔሻሊስት ሐኪሞችም ከፍተኛ አገልግሎት ፈጽመዋል፡፡
በዕለቱ ሕክምና የተደረገላቸው አባቶች መነኮሳት፣ እናቶች መነኮሳይያትና የአብነት ተማሪዎች ከ፪፻፶ የሚበልጡ ሲኾን፣ ከሕክምናው በተጨማሪ ለአብነት ተማሪዎች የግልና የአካባቢን ጤና አጠባበቅ የተመለከተ ሥልጠና በጤና ባለሞያዎች ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዳማ ማእከል የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ለአብነት ተማሪዎች የተዘጋጀው አልባሳት፣ የገላና የልብስ ሳሙና በገዳሙ በኩል ለአብነት ተማሪዎቹ እንዲከፋፈል ተደርጓል፡፡
የገዳሙ አባቶች፣ እናቶች መነኮሳትና እና የአብነት ተማሪዎቹ በተደረገላቸው የሕክምና፣ የአልባሳት እና የጤና መጠበቂያ ድጋፍ እጅግ መደሰታቸውን ገልጸው ማኅበረ ቅዱሳን በገዳማት ላይ እየሠራ ያለው አገልግሎት የሚያስመሰግነው መኾኑንና ይህንንም ሁልጊዜ ሲያስታውሱት እንደሚኖሩ በመጥቀስ ማኅበሩ በገዳማት ላይ የሚያደርገውን አገልግሎት አጠናክሮ እንዲቀጥል በማሳሰብ ማኅበሩን ያስፋልን ይጠብቅልን በማለት መርቀው የሕክምና ቡድኑን በቡራኬና በጸሎት አሰናብተዋል፡፡