የ5ኛው ዙር ዐውደ ርእይ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለጸ
የካቲት 19 ቀን 2008 ዓ.ም
ማኅበረ ቅዱሳን ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፣ ድርሻችንን እንወቅ በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 15-21 ቀን 2008 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማእከል የሚያቀርበው ዐውደ ርእይ ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን የዐውደ ርእዩ ዐቢይ ኮሚቴ ገለጸ፡፡
ዐውደ ርእዩን ለማዘጋጀት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ፈቃድ ከማግኘት ጀምሮ፣ ኤግዚቢሽን ማእከሉን በመከራየትና ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር ዐወደ ርእዩ ተጀምሮ እስኪፈጸም ድረስ በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ ገልጸው፣ ያሰብነውን በትክክል እንድናሳካ ጸሎት አስፈላጊ ነው፡፡ ሁሉም ነገር በጸሎት ኃይል ነው የሚከናወነው፤ የሚያጋጥመንን ፈተና ሁሉ እንድናልፍ በጸሎት እንድታሰቡን ይገባል ብለዋል፡፡ በዐውደ ርእዩም ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ምእመናን ይጎበኙታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ዋና ጸሓፊው ሰፊ ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበትና የቤተ ክርስቲያንን ዓለም አቀፋዊነት የሚያሳይ፤ እንዲሁም በይበልጥ ቤተ ክርስቲያያንን እንድናውቃት የሚያደረገን ስለሆነ ምእመናን ዐውደ ርእዩን እንዲመለከቱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የዐውደ ርእዩ ዐቢይ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ ተሾመ በበኩላቸው ቅድመ ዝግጅቱን በሰው ኃይልና አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን በማሟላት ምእመናን ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ግንዛቤ ለማስፋት፣ ከእነሱም የሚጠበቀውን ማበርከት እንዲችሉ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የዐውደ ርእዩ ዓርማ እና መሪ ቃል በአባቶች ቡራኬ የተመረቀ ሲሆን፤ በዓርማው የተካተቱና ማስተላለፍ የተፈለገውን መልእክት አስመልክቶ በዲ/ን ዋሲሁን በላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
የዐውደ ርእዩ ይዘት በዐራት አበይት ትእይንቶች የተከፈለ ሲሆን፤ በእያንዳንዱ ትእይንት ውስጥ በርካታ ንዑሳን ክፍሎች ተካትተዋል፡፡ ዐራቱ ዐበይት ትእይንቶች፡-
1.የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት እና ቤተ ክርስቲያን ማን ናት?
2.የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ
3.የቤተ ክርስቲያን ተጋድሎ
4.ምን እናድርግ? በሚል ተከፋፍለው ይቀርባሉ፡፡
በተጨማሪም ኦርቶዶክሳውያን ክውን ጥበባት የሚቀርቡበት ዝግጅትም በስፋት ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ በከውን ጥበባት ልዩ ዝግጅት የአብነት ትምህርት ቤቶችና የትምህርት አሰጣጣቸው፣ ሊቃውንቱ ከነደቀመዛሙርቶቻቸው ተገኝተው የሚያቀርቡ ሲሆን በሰባቱም ቀናት በተለያዩ ርእሶች የአደባባይ ተዋስኦ/Public Lecture Speeches/ ይቀርባል፡፡
በዐውደ ርእዩ ላይ ገለጻውን ለሚያካሄዱ የማኅበሩ አባላት፣ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች እና ግቢ ጉበኤያት ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን የተናገሩት የዐቢይ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዐውደ ርእዩ ለአንድ ሳምንት ብቻ የሚቆይ በመሆኑ በመዝጊያው ቀን ሊከሰት የሚችለውን መጨናነቅ ለመቀነስ ከተከፈተበት ቀንና ስዓት ጀምሮ ምእመናን ተገኝተው እንዲመለከቱ አሳስበዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ ቀደም በ1988፣ በ1992፣ በ1994፣ በ2000 ዓ.ም ለዐራት ጊዜያት በተለያየ ይዘት ላይ ያተኮረ ዐውደ ርእይ ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ከመጋቢት 15-21 ቀን 2008 ዓ.ም የሚካሔደው ለአምስተኛ ጊዜ ነው፡፡