የ33ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችን ሪፖርት አደመጠ፡፡
ጥቅምት 8 ቀን 2007 ዓ.ም.
መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
- የማኅበረ ቅዱሳን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በየሀገረ ስብከቶቹ በሪፖርት ቀርቧል፡፡
ሦስተኛ ቀኑን የጠናቀቀው የ33ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችና ሪፖርት አድምጦ አጠናቋል፡፡
ሪፖርት አቅራቢ ሥራ አስኪያጆችና የሰሜን አሜሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በ2006 ዓ.ም የሥራ ዘመን ክንውን ሪፖርታቸውን የጉባኤው ታዳሚዎች ሲያቀርቡ የሪፖርቱ ይዘት ጉባኤውን በሐሴት እንዲሞላ፣ አንገት እንዲደፋና የዕንባ ዘለላ እንዲወርድ ያደረገ ነበር፡፡
ጉባኤው በሐሴት የተሞላባቸው ሪፖርቶች በርካታ ሀገረ ስብከቶች በልማት ሥራዎች ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸው፡፡
ዘመናዊ የመልካም አስተዳደርና ዘመናዊ የሒሳብ አሠራር ግንዛቤ አየጨመረ መምጣቱ፡፡
በጠረፋማ አካባቢ የሚገኙ ሀገረ ስብከቶች የስብከተ ወንጌልን አገልግሎት በማጠናከር በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ዜጎችን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን እንዲቀላቀሉ ያደረጉ መሆናቸው፡፡
የቅርስና ንዋያተ ቅዱሳት አያያዝን በተመለከተ ካለፉት ዓመታት በተሻለ ሁኔታ የቅርስና ንዋያተ ቅድሳት አያያዝና አጠባበቅ የተሻለ መሆኑ የተዘገበ ሲሆን አንዳንድ ሀገረ ስብከቶችም የተዘረፉ ቅርሶችን በማስመለስ ቅርሶቹ በክብር እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡
ዓመታዊ ገቢ ማሳደግን በተመለከተ በርካታ ሀገረ ስብከቶች ካለፈው ዓመት ገቢ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ዕድገት ማሳየት መዘገቡ ይበል የሚያሰኝ ሲሆን ለነዚህ አገልግሎቶች ስኬታነት የማኅበረ ቅዱሳን ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበርና በሥልጠና፣ በስብከተ ወንጌል፣ በሕንፃ ዲዛይን በገዳማትና አብነት ትምህርት ቤት ድጋፍ ወዘተ የተደረገው ድጋፍ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን በተለይ በተደረገ ሥልጠና አንዳንድ ሀገረ ስብከቶች የሀገረ ስብከቶች ዓመታዊ ገቢያቸው የሥራ ተነሳሽነታቸው መጨመሩም በሪፖርቱ ተወስቷል፡፡
ጉባኤውን ያሳዘነና ያስለቀሰ ለቀጣዩ የአገልግሎት ዘመን በትጋት ለመሥራት ቁጭት የፈጠረው
-
የቤተ ክርስቲያን አባላት ቁጥር መቀነስ
-
የተሐድሶ እንቅስቃሴ እጅግ በጣም ረቅቆ የቤተ ክርስቲያኒቷን መዋቅር በመጠቀም ሥርዓተ አምልኮዋን ቀኖና ሥርዓቷን ለማጥፋት የሚደረገው ቅሰጣና ሁከት መፍጠር፡፡
-
የቤተ ክርስቲያኒቱ አንዳንድ አገልጋዮች በንብረትና ቅርስ ዘረፋ ላይ ተሰማርተው መገኘት፡፡
-
የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች በሙስና ተግባር ላር ተሰማርተው በመገኘታቸው የቤተ ክርስቲያንን መልካም ስም ያጎደፈ፣ ምእመናንን አንገት ያስደፋና ከእናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲወጡ ምክንያት እንደነበር ተወስቷል፡፡
ጥቅምት 6 ቀን 2007 ዓ.ም እና ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም ትምህርተ ወንጌል በብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ትምህርተ ወንጌል የጉባኤው ታዳሚ ስለ እናት ቤተ ክርስቲያን ይበልጥ እንዲያስብ፣ እንዲሠራ፣ እንዲተጋ ያሳሰበ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስም በተለይ የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ስውር ተልዕኮ ተረድቶ ቤተ ክርስቲያኒቷን እንዲጠብቅ የሚያሳስብ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ጥቅምት 9 ቀን የጠዋት ውሎ በቀረቡት ሪፓርቶች ላይ ውይይት ተደርጎ የአቋም መግለጫ ከቀረበ በኋላ የሽልማትና የምሥጋና መርሐ ግብራት ከተከናወነ በኋላ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለ ምእዳንና መመሪያ የ33ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ይጠናቀቃል፡፡