ጼዴንያ ማርያም
መስከረም 9 ቀን 2007 ዓ.ም.
“ሰላም ለሥዕልኪ እንተ ሠዓላ በእዱ፡፡ ሉቃስ ጠቢብ እምወንጌላውያን አሐዱ፡፡ አመ ተቀብዑ ማርያም እምሐፈ ሥዕልኪ ቅብዐ ናርዱ፡፡ በሕማም እኩይ እለ ደወዩ ወውሕዱ፡፡ ፅዑራነ ዓለም ጥዕዩ ወጥቀ ፈድፈዱ፡፡” አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ዐሥር በዚች ቀን ጼዴንያ በምትባል አገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል ሥዕል ከሠሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ተአምር ተገለጠ፡፡
ይቺንም ሥዕል የሣላት ወንጌላዊ ሉቃስ ነው፡፡ ወደ ጼዴንያ አገርም የመጣችበት ምክንያት አንዲት ስሟ ማርታ የሚባል መበለት ሴት ነበረችና ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች ናት አምላክን የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያምንም እጅግ ትወዳት ነበር፡፡ በሚቻላትም ሁሉ ታገለግላታለች፡፡
በአንዲት ቀንም ስሙ ቴዎድሮስ የሚባል መነኲሴ ከእርሷ ዘንድ እንግድነት አደረ በመልካም አቀባበልም ተቀበለችው በማግሥቱም ስትሸኘው አባት ሆይ የምትሔደው ወዴት ነው አለችው፡፡ እርሱም በከበሩ ቦታዎች ውስጥ ልሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም እሔዳለሁ አላት እርሷም ከአኔ ገንዘብ ወስደህ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል ግዛልኝና በመመለሻህ ጊዜ አምጣልኝ አለችው፡፡ እርሱም በራሴ ገንዘብ ገዝቼ አመጣልሻለሁ አላት፡፡
ከዚህም በኋላ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከቅዱሳት መካናት ተባረከና ሥዕሏን ሳይገዛ ወደ ጐዳናው ተመለሰ፡፡ ያን ጊዜም ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰማ ወደ ገበያም ተመልሶ ላሕይዋና መልኳ ያማረና የተወደደ የሆነ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል አግኝቶ ገዛት በሐርና በንጹሕ ልብስም ጠቀለላት፡፡
በጐዳናውም እየተጓዘ ሳለ ከማያስፈራ ዱር ውስጥ ወንበደዎች ተነሡበት ሊሸሽም ወደደ ከዚያቺም ሥዕል መንገድህን ሒድ የሚል ቃል ወጣ የተከተለውም ሳይኖር መንገዱን ተጓዘ፡፡ ሁለተኛም ነጥቆ ሊበላው አንበሳ ተነሣበት ያን ጊዜም ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረው፡፡
አባ ቴዎድሮስም ይህን ሁሉ ድንቅ ተአምር በአየ ጊዜ ያቺን ሥዕል ወደ አገሩ ሊወስዳት ወደደ ግዛልኝ ላለችው መበለት ይሰጣት ዘንድ አልፈለገም፡፡ ከዚህም በኋላ በመርከብ ተሳፍሮ በሌላ አቅጣጫ ሲጓዝ ታላቅ ነፋስ ተነሣበት ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያም ወሰደው ከመርከብም ወርዶ ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ሔደ ማንነቱንም አልገለጣላትም እርሷም አላወቀችውም፡፡
በማግሥቱም ተሰውሮ ወጥቶ ወደ አገሩ ሊሔድ በፈለገ ጊዜ የቅጽሩን ደጃፍ አጥቶ ሲያጥመሰምስ ዋለ በመሸ ጊዜም ወደ ማደሪያው ተመለሰ፡፡ ያቺም መበለት በአየችው ጊዜ ታደንቃለች እንዲህም ሁኖ እስከ ሦስት ቀን ኖረ በመሸ ጊዜ በሩን ያየዋል ነግቶ መሔድን ሲሻ የበሩ መንገድ ይሠወረዋል፡፡ ያቺም መበለት ያዝ አድርጋ አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን ስትቅበዘበዝ አይሀለሁና ምን ሁነህ ነው አለችው፡፡
ከዚህም በኋላ ከዚያች ሥዕል የሆነውን ሁሉ ነገራት ራሱንም ገለጠላት፡፡ ያቺንም ሥዕል ሰጣት ተቀብላም የተጠቀለለችበትን ልብስ ፈታች ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች፡፡ ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የዚያን መነኲሴ እጆቹንና እግሮቹን ሳመች፡፡
ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር የምትቀመጥበትን አዘጋጅታ አኖረቻት ማንም እንዳይዳስሳትም የነሐስ መስኮትን ሠራችላት በቀንና በሌሊትም የሚበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች ከመቅረዞም ውጭ የሐር መጋረጃን ጋረደች፡፡ ከሥዕሊቱ በታችም ከሥዕሊቱ እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሠራ ወጭት አኖረች ያም መነኰስ እስከሚሞትበት ቀን ድረስ የእመቤታችንን ድንግል ማርያምን ሥዕል እያገለገለ ኖረ፡፡
የሀገሩም ሊቀ ጳጳሳት የዚያችን ሥዕል ዜና በሰማ ጊዜ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከካህናት ከሕዝቡም ሁሉ ጋር መጣ፡፡ በሠሌዳዋም ውስጥ በአዩዋት ጊዜ ሥጋ የለበሰች ሁና አገኙዋት ከዚህ ከአምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ ከዚያም ቅባት ቀድተው ለበረከት በተካፈሉ ጊዜ ወዲያውኑ በወጭቱ ውስጥ ይመላል፡፡
ወደ ሌላ ቦታም ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜ ንውጽውጽታ ሁኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ በዚያች አገር ትኖራለች፡፡ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእናቱ በእመቤታችን በድንግል ማርያም ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን፡፡
- ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ከመስከረም እስከ የካቲት