አድርሺኝ

ነሐሴ 12 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

a ledeta mariam 2006 01በጎንደር ከተማ በፍልሰታ ለማርያም ጾም ወቅት በካህናቱ፤ በሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና በምእመናን አማካይነት በየዓመቱ የሚከናወን የተለመደ ሥርዓት አለ፡፡ ይህም ሥርዓት “አድርሺኝ” በመባል ይታወቃል፡፡

በጎንደር ከነገሡት ነገሥታት መካከል ከ1703-1708 ዓ.ም. ለአምስት አመታት በንግሥና የቆዩት ዐፄ ዮስጦስ የጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያንን በመትከል የሚታወቁ ሲሆን፤ አድርሽኝ የተሠኘውንም ሥርዓት በእርሳቸው እንደተጀመረ ይነገራል፡፡

ስለ ሥርዓቱ አጀማመር አባቶች ሲናገሩ፣ ዐፄ ዮስጦስ ተቀናቃኞቻቸው የከፈቱባቸውን ጦርነት ለመመከት ወደ ጦርነት ሲዘምቱ “ልደታ ለማርያም ሳትለዪኝ በድል ብትመልሺኝ፤ ለዚህም ታላቅ ክብር ብታደርሺኝ በየዓመቱ በፍልሰታ ለማርያም ሱባኤ ካህናቱን፤ መኳንንቱንና ምእመናንን ሰብስቤ ግብዣ አደርጋለሁ” በማለት ብፅዐት ይገባሉ፡፡ እርሳቸውም ድል አድርገው በመመለሳቸው በቃላቸው መሠረት በጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ደጀ ሰላም ሕዝቡን ሰብስበው ግብዣ ማድረጋቸውን ቀጠሉ፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑም እርሳቸውን ተከትሎ በየዓመቱ በጾመ ፍልሰታ ወቅት ይህንን ሥርዓት ይተገብሩት ጀመር፤ ስያሜውም “አድርሺኝ” ተባለ፡፡

አድርሺኝ በመላው ጎንደር በየአብያተ ክርስቲያናቱና በየአካባቢው በፍልሰታ ጾም ወቅት ይከናወናል፡፡ ምእመናን ከቅዳሴ መልስ ሱባኤው እስኪጠናቀቅ በመረጡት አንድ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ቆሎና ጠላ አዘጋጅተው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ጽዋ ይጠጣሉ። በተለይም መነኮሳይያት እናቶች በሚታደሙበት ጽዋ ላይ “ኦ! ማርያም” የሚለውን የተማጽኖ መዝሙር ይዘምራሉ። ይህ መዝሙር በሚዘመርበት ጊዜ ያለ ምንም ጥርጥር እመቤታችን ፊት ለፊት ትቆማለች ተብሎ ስለሚታሰብ በፍጹም ተመሥጦና በመንበርከክ ያከናውኑታል።

የጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ-ኤስድሮስ ሰንበት ት/ቤት ወጥነት እንዲኖረው በማሰብ ይህንን የእናቶች የምሕላ ዝማሬ ለተተኪ ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል አሰባስቦ አዘጋጅቶታል፡-

ኦ! ማርያም

ኦ! ማርያም እለምንሻለሁ ባሪያሽ፤

እስኪ አንድ ጊዜ ስሚኝ ቀርበሽ፤ ከአጠገቤ ቆመሽ፤

ፅኑ ጉዳይ አለኝ ላንቺ የምነግርሽ፤

የዓለሙን መከራ ያየሽ፤

በእናትሽ በአባችሽ ሀገር፤

በምድረ ግብፅ ዞረሽ ውሃ የለመንሽ፡፡

ከሁሉ ሁሉ ጤፍ ታንሳለች፤

ከጭቃ ወድቃ ትነሳለች፤

ስትነሳ /2/ የአዳም ልጅ ሁሉ ሞትን ረሳ፤

የአዳም ልጅ ሁሉ ሰነፈና የኑሮ ቤቱን ረሳና፤

ተው አትርሳ /2/ ተሠርቶልሃል የእሳት ሳንቃ፡፡

ያን የእሳት ሳንቃ፤ የእሳት በር፤

እንደምን ብዬ ልሻገር፤

ተሻገሩት አሉ የሠሩ ምግባር፤

እኔ ባሪያሽ እንዴት ልሁን? ሰላም ሰጊድ /2/

በመሥቀሉ ሥር ያያትን ተሰናበታት እናቱን፤

እናትዬ ለምን ታለቅሻለሽ ተሰቅዬ፤

ይስቀሉኝ ሐሰት በቃሌ ሣይገኝ፡፡

ንፅሕት የወልደ እግዚአብሔር እናት፤

ንፅህት በፍቅሯ ወዳጆቿን ስትመራ፤

ንፅሕት በቀኝ ወዳጆቿን ስትጎበኝ፤

የእኛስ እመቤት ያች ሩኅሩኅ፤

ከለላችን ናት እንደ ጎጆ፤

እርሷን ብለው ጤዛ ልሰው ኖሩ ትቢያ ለብሰው /2/

ኪዳነ ምሕረት ሩኅሩኅ ተይ አታቁሚኝ ከበሩ፤

የገነሃም እሣት መራራ ነው አሉ፤

እኔ ባሪያሽ እንዴት ልሁን? ሰላም ሰጊድ /2/

ድንግል ማርያም ንፅሕት፤

የምክንያት ድኅነት መሠረት፤

እንለምንሻለን ወደ አንቺ አንጋጠን፤

ከፈጣሪ በይ አማልጅን ሰላም ሰጊድ /2/

ኃያል /2/ ቅዱስ ሚካኤል ኃያል፤

የለበሰው ልብሱ የወርቅ ሐመልማል፤

ይህም ተጽፏል በቅዱስ ቃል ሰላም ሰጊድ /2/

ጊዮርጊስ ስልህ ዘንዶ ሰገደ ከእግርህ፤

እፁብ ድንቅ ይላሉ ገድልህን የሰሙ፤

አንተ አማልደኝ ከሥልጣኑ ሰላም ሰጊድ /2/

አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ደግ አባት፤

መጥቼልሃለሁ ከደጋ፤

ስንቄንም አድርጌ አጋምና ቀጋ፤

አንተ አማልደኝ ከፈጣሪ ሰላም ሰጊድ /2/

ፃድቅስ ባያችሁ ተክለ ሃይማኖት፤

በአንድ እግር ቆመው ሰባት ዓመት፤

በተአምኖ ሰባት ባቄላ ምግብ ሆኖት /2/

ተክለ ሃይማኖት አባቴ፤

መሠላሌ ነህ ለሕይወቴ፤

የዓለሙን ኑሮ መጥፎነቱን፤

የፈጣሪያችን ቤዛነቱን፤

አስተውለኸው አጥንተኸው፤

ደብረ ሊባኖስ የተሰዋኸው፡፡

ክርስቶስ ሠምራ እናታችን፤

ከአምላካችን ፊት መቅረቢያችን፤

ሣጥናኤልን አሸንፈሽ፤

ከግዛቱ ውስጥ ነፍስን ማረክሽ፡፡

ክርስቶስ ሠምራ ቅድስቷ፤

ለጽድቅ ሕይወት አማላጇ፤

እንለምንሻለን ወደ አንቺ አንጋጠን፤

ከፈጣሪ በይ አማልጅን ሰላም ሰጊድ /2/

ኦ! አባቴ አንተ ረኃቤ ነህ ጥማቴ፤

የኔ መድኃኒት ኃያል ተመልከተን ዝቅ በል፤

የነገሩህን የማትረሳ፤

የለመኑህን የማትነሳ፤

አምላኬ አንተ ነህ አምባዬ፤

የሕይወት ብርሃን ጋሻዬ፡፡

ማርያም ስሚን ወደ ሕይወት መንገድ ምሪን፤

ከአጠገባችን ቁጭ ብለሽ አድምጭን፤

ይደረግልን ልመናሽ ስትመጪ /2/

አንቺ እናቴ ሆይ /2/ የሔድሽበትን ትቢያ ቅሜ፤

ያረፍሽበትን ተሳልሜ፤

በሞትኩኝ /2/ የኋላ ኋላ ላይቀር ሞት፡፡ /2/

 

በፍልሰታ ለማርያም ጾም ወቅት ዘወትር ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በቤተ-ኤስድሮስ ሰንበት ት/ቤት ካለፉት 21 ዓመታት ጀምሮ ጸሎት ዘዘወትር፣ ውዳሴ ማርያም፣ ይዌድስዋ መላእክት፣ መዝሙረ ዳዊት 50 እና 135፣ ጸሎተ ምናሴ፣ መሐረነ አብ ጸሎት በዜማ ከተጸለየ በኋላ ኦ! ማርያም የምሕላ መዝሙር ይዘመራል፡፡

  • ማስታወሻ፡- መረጃውን በመስጠት የተባበሩንን ዲያቆን ሙሉቀን ብርሃኑ እና የጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ- ኤስድሮስ ሰንበት ትምህርት ቤትን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡