የቅዱስ ሲኖዶስ ምልኣተ ጉባኤ የ2006 ዓ.ም. ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ተጀመረ

ግንቦት 6 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

  • ለቤተ ክርስቲያን አይደለም ለራሱ እንኳን በአግባቡ መቆም ያልቻለ የሰው ኃይል ይዘን የትም መድረስ አንችልም / ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ/

seno 2006የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የግንቦቱ ርክበ ካህናት ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ግንቦት 5 ቀን 2006 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በጸሎት ተጀምሯል፡፡ ግንቦት 6 ቀን 2006 ዓ.ም. በቅዱስ ፓትርያርኩ የመክፈቻ መልእክት ጉባኤው ቀጥሏል፡፡

ብፀዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃማኖት ለቅዱስ ሲኖዶስ ባስተላለፉት መልእክት “ ወንጌልን ለዓለም የማድረስ ተልእኮ የኛ የሊቃነ ጳጳሳቱ እስከሆነ ከሁሉም ዘንድ ለመድረስ ጠንክሮ መሮጥ የኛ ግዴታ ነው፤ ሆኖም ሩጫው እንቅፋት አጋጥሞት ለጉዳት እንዳይዳርገን ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ትዕግስትና ማስተዋል ያልተለየው ሊሆን ይገባል፡፡ ትዕግስትንና ማስተዋልን ገንዘብ አድርጎ ሥራን መሥራት ትልቅ ጥበብ እንጂ ቸልተኝነት አይደለም፤ ሃይማኖት የሚጠበቀው ድኅነትም የሚገኘው በትዕግስት እንደሆነ ራሱ ባለቤቱ “በትዕግስትክሙ ታጠርይዋ ለነፍስክሙ” በማለት አስተምሮናል” ብለዋል፡፡

 

a holy syno 2006
ቅዱስነታቸው ባለፈው ዓመት ርክበ ካህናት ጉባኤ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያን መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፤ ብልሹ አሰራር እንዲታረም፤ ቤተ ክርስስቲያን ልዕልናዋን፤ ክብሯን፤ ንፅሕናዋንና ቅድስናዋን ጠብቃ እንድትቀጥል የሚያስችሉ ውሳኔዎችን አሳልፎ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ውሳኔዎቹም በጥናት ተመሥርተው በተግባር ይተረጎሙ ዘንድ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ጠቅሰው፤ ኮሚቴዎቹ የመጀመሪያ ዙር ጥናታቸውን ለጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አቅርበው እንዲታይ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ጥናቶቹ በሊቃውንትና በባለሙያዎች እየታገዙ የቀጠሉ ቢሆንም በሥራው ሂደት በመጠኑም ቢሆን መሰናክሎች እንደነበሩና ቋሚ ሲኖዶስ በሚያደርገው ክትትልና በሚሰጠው አመራር መልክ እያያዙ በመምጣታቸው ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በማዕከል የተቋቋመው ኮሚቴና ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ደንብ አጥኚ ተብሎ በድጋሚ የተሰየመው ኮሚቴም በአንድነት ለመሥራት ያሳዩት ተነሳሽነት፤ ጥራትና ቅልጥፍና ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

“በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ላይ የሚታየው ክፍተት ሥር የሰደደ ከመሆኑ አንጻር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይስተካከላል የሚል እምነት ብዙ ላይኖረን ይችላል” ያሉት ቅዱስነታቸው ይሁንና በጀመርነው መስመር ከቀጠልን ሩቅ በማይባል ጊዜ ውስጥ ለውጦችን ማየት እንደምንችል ጥርጥር የለንም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

መልካም አስተዳደርን በፍጥነት ለማስፈን “በየአቅጫው ለሚነፍሱ የውጭ ነፋሳት የማይበገር አንድነት፤ ሕግ ቤተ ክርስቲያንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ብቻ ማእከል አድርጎ መሥራት፤ በእናውቅላችኋለን ባዮች ግራ ሳይጋቡ በራስ በመተማመን መወሰን፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ ሥልጣን በማንም ይሁን በማን እንዳይገሰስ ጥብቅና መቆም የመሳሰሉ ባሕርያት ለዚህ ጉባኤ አስፈላጊ መሳሪያዎች ናቸው” ብለዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያን ያላትን የሰው ኃይል እንደሌላው ዓለም አጠቃቀም ብንጠቀምበት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ ይበቃ እንደነበር ጠቁመው፤ የሰው ኃይልን በእውቀት አምልቶ ክፍተቱን ከመሙላት ይልቅ ከመቶ ዓመት በፊት የነበሩት አስገዳጅ ሁኔታዎች ያመጡብንን የዘመናት ልምዶች እንደመልካም ባህል ይዘን በዚያው በመቀጠላችን ክፍተቱ ተፈጥሯል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
“ለቤተ ክርስቲያን አይደለም ለራሱ እንኳን በአግባቡ መቆም ያልቻለ የሰው ኃይል ይዘን የትም መድረስ አንችልም፤ ሆኖም ይህን ችግር ለማስተካከል ያለውን በማፍለስ ሌላ አዲስ ተክልን መትከል ሳይሆን ያለውን የሰው ኃይል ማስተካከል እንዳለብን ሊሰመርበት ይገባል” ብለዋል፡፡

በዓለም ላይ የሚገኙ ካህናት ብዛት በአጠቃላይ ቢበዛ ከሁለት ሚሊዮን ላይበልጥ ይችላል፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያናችን ከግማሽ ሚሊዮን ካህናት በላይ ይዛ ለምን ብዙ የሥራ ክፍተቶች ይከሰታሉ የሚለውን ጥያቄ ቅዱስ ሲኖዶስ በውል ሊያጤነው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ልማትን አስመልክቶ ሲናገሩም “ቤተ ክርስቲያናችን የልማት በረከቱ ባለበት ብቻ እንዲቀጥል ሳይሆን ካለበት በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሕዝቡን በማስተማር ለልማቱና ለእድገቱ በሰፊው መንቀሳቀስ አለባት፤ የተለመደውን ሀገራዊ ሓላፊነቷንም መወጣት አለባት” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

“ቤተ ክርስቲያናችን ለዚህች ሀገር አንድነት መጠበቅና ለሕልውናዋ ቀጣይነት ለሦስት ሺሕ ዘመናት ያህል የሰራችው ጉልህና ደማቅ ሥራ አሁንም መድገም አለባት፡፡ ቤተ ክርስተያናቸችን ዛሬም እንደቀድሞው ሃይማኖታዊና ልማታዊ ሥራን በመሥራት የመሪነት ሚናዋን የምታጠናክርበት አቅጣጫ ይህ ጉባኤ መቀየስ አለበት” በማለት ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡