ማኅበረ ቅዱሳን በሬድዮ አገልግሎቱ የሞገድና ሰዓት ለውጥ አደረገ
ሚያዚያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን ድምጸ ተዋሕዶ የተሰኘውንና ዘወትር ዓርብ ከምሽቱ 3፡30 እስከ 4፡30 በአጭር ሞገድ 9850 kHz 19 ሜትር ባንድ ሲሰጠው በነበረው ሳምንታዊ የሬድዮ አገልግሎት ላይ የሥርጭት ሞገድና ሰዓት ለውጥ ማድረጉን አሳወቀ፡፡ ለውጡን ለማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ የማኅበሩ ሚድያ ዋና ክፍል ሓላፊ ሲያስረዱ «ቀድሞ መርሐ ግብሩ ይተላለፍበት የነበረው ሰዓት፤ ዘወትር ዓርብ ከምሽቱ 3፡30 እስከ 4፡30፤ በንጽጽር ምሽት ስለነበር በተለይ በክልል የሚገኙ አድማጮቻችን አገልግሎቱን አለማግኘታቸውን በልዩ ልዩ መንገድ ሲገልጹልን ቆይተዋል፡፡
በዚህ መሠረት ምእመናን አገልገሎቱን በሚመቻቸው ጊዜ ማግኘት እንዲችሉ ይተላለፍበት የነበረውን አጭር ሞገድ ወደ 17.515 kHz 16 ሜትር ባንድ በመቀየር ዘወትር ዓርብ ከአመሻሹ 12፡30 እስከ 1፡30 ለማቅረብ ለውጥ አድርገናል» ብለዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኗ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ እምነትና ታሪክ በሊቃውንት ተተንትኖ የሚቀርብበት ይህ የሬድዮ መርሐ ግብር ማሠራጫ ጣቢያውን አውሮፓ ባደረገ የአሜሪካ ራድዮ ካምፓኒ አማካይነት የሚተላለፍ ነው፡፡ «እግዚአብሔር የሰጠንን መልካም አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ቃሉን ለሁሉም ማድረስ ይገባናል´ ያሉት ዲ/ን ዶ/ር መርሻ «የአበው ትምህርትና ምክር በዓለም ዙሪያ ሁሉ እንዲዳረስ ምእመናን ሬድዮውን በማስተዋወቅ፣ በፕሮግራሞች ላይ የሚኖሩ አስተያየቶችንም በማድረስና በጸሎት እንዲያግዙን´ በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ አክለውም በውጭው ዓለም የሚኖሩና የኢንተርኔት አገልግሎትን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉ ምእመናን ዝግጅቶችን www.dtradio.org ላይ ተጭነው እንደሚያገኟቸው ገልጸዋል፡፡