ሃይማኖታውያን መስለው ከሚመጡ መናፍቃን ተጠንቀቁ ማቴ 7፥15
መስከረም 8 ቀን 2005 ዓ.ም.
አባ ዘሚካኤል
- የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ያቆየችውን ትውፊት፣ ቅርስና ሀብት፣ ቋንቋና ዜማ የመቀራመቱ ዘመቻ ይቁም!
ትላንት ተዋሕዶን በማናናቅ ምእመናኑን ለማስኮብለል ያልተሳካላቸው መናፍቃን፣ ዛሬ ደግሞ ስልት ቀይሰው የተዋሕዶን ታሪክ፣ ግዕዝ ጠቀሳና ያሬዳዊ ዜማን ያደነቁ በመምሰልየመፈታተናቸው አንድምታው ምን ይሆን? የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ያቆየችውን ትውፊት፣ ቅርስና ሀብት የመቀራመቱ ድፍረትሳ ተመሳስሎ ተጠግቶ ማንነትዋን ለመጋራት ይሆን?ዓላማው መጀመሪያ ምእመኑን የማዘናጋት ቀጥሎ አንድነን ለማለትና ወደመናፍቅነት ለመሳብ ከዚያም እንደ ሰለጠነው ዓለም ፍጹም ዓለማዊ ለማድረግ ይሆንን?
መጽሐፍ ተዓቀቡኬ እምሐሳውያን ነቢያት እለይመጽኡ ሀቤክሙ በአልባሰ አባግዕ፣ የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡ ሐሰተኞች፣ መናፍቃን፣ መምህራን ተጠንቀቁ፣ ወእንተ ውስጦሙሰ ተኩላት መሰጥ እሙንቱ፡፡በውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላ ናቸው፣ ቢመረምሩዋቸው ግን ሰውን እየነጠቁ ወደ ገኀነም የሚያወርዱ የሰይጣን ሰራዊት ናቸው፡፡ (ወንጌል አንድምታማቴ 7፥15)
ይህን የወንጌል አሳብ እንደሚያስረዳን መናፍቃን ዓለማውያን የሚጠነስሱት ሴራና ፈጠራ ጌታችን መድኀኒታችንኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማረው የማስጠንቀቂያ ትንቢት ቃል ውጭ የሆነ ያልታወቀ፣ ያልተረዳአዲስ ነገር ሊሆን አይችልም፡፡አስቀድሞ”በስሜ ይመጣሉ” ብሎ ተናግሯልና፡፡ ለዚህምቀጥሎ የተመለከተውን የበግ ለምድ ምሳሌ ዝርዘር እንመልከት፣
-
የበግ ለምድ ለብሰው የሚመጡ ተኩላ ያላቸውእውነተኛ መስለው የሚመጡ ሐሰተኞች መምህራንን ነው፣ ነገር ግን በእውነተኛ ሃይማኖት ጸንተው ያሉትን ክርስቲያኖች ተመሳስለው ገብተው በተለያየ ዘዴ ምእመኑን በመቀሰጥናከእምነቱ በማናጋት ወደገሃነም ለማውረድ የሚሠሩትን የዲያብሎስንሠራተኞች ነው፡፡
-
የበግ ለምድ መልበስምሳሌ የሚያሳየውማስመሰያአሠራራቸውን፣ ድራማ መሰል ጥረታቸውን ነው፡፡ተኩላ ለምድ የሚለብስሆኖ አይደለም፣ ተኩላ ለምድን ከሚለበስ ቢበላው ይመርጣልና፡፡ መናፍቃንም የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ባትኖር ይመርጣሉ፣ ነገር ግን ሊውጡት ያሰቡትን ምእመን እንደ ተኩላ ለመንጠቅ ያመቻቸው ዘንድ የቤተ ክርስቲያኗን ግእዝና ዜማ የወደዱ መስለው መታየት የጀመሩትምእመኑን ለማዘናጋት የፈጠሩት አዲሱ ዘዴ ነው፡፡ ነገር ግን ግብራቸው የተኩላ ግብርእንዲመስል፣ ለነዚህ ቀሳጥያን ጌታችንአስቀድሞ ሲመስልባቸው የበግ ለምድ ለብሰው የሚመጡ ተኩላ ነጣቂ አላቸው፡፡ ይህም ተኩላ በግን ለመምሰል የበግን ቆዳ ቢለብስ እንዳይዋሐደውና በግን እንዳይመስል እነሱም እንደ ድራማ ትምህርቱን ልስበከው፣ ዜማውን ላዚመው፣ ቅዳሴውን ልቀድሰው፣መዝሙሩን ልዘምረው ወዘተ ብለው ቢጥሩ እውነተኛውን የተዋሕዶ አገልጋይ፣ አማኝእና ክርስቲያን መሆን አይቻላቸውም፡፡
-
የበግ ለምድ የተባለው ምሳሌ፣ለምድ የበግ አካል የነበረ እንጂ የተኩላ አካል አይደለም፣ተኩላው ከላይ ለምዱን ቢደርበው አካል ሆኖት ደመ ነፍስ እንዳይዘራና ተኩላ በግ እንዳይሆን ሁሉ መናፍቃንም የተዋሕዶን አሠራር ሳያምኑበት በማስመሰልና ማቅረብ ቢሞክሩም እንኳን ውጤቱ ሕይወት አልባ ዳንኪራ፣ በቀቢጸ ተስፋ ያቀረቡት ሙሾ አስመስሎባቸዋል፡፡ በእሁኑ ወቅት የጀመሩት የተዋሕዶ ምእመናን የሚወዱትን ግዕዝ መጥቀስ፣ ያሬዳዊ ዜማን አስመስሎ ለማቅረብ የተሞከረው ሕይወት አልባ እንቅስቃሴየዚህ ማሳያ ነው፡፡የተዋሕዶ ሕዝብ ማስተዋል ያለበትይህን ሕይወት አልባ ሩጫ፣ ክርስቲያን ሳይሆኑ ክርስቲያንን ለማታለል ያደረጉት የቅስጥ ድራማ መሆኑን ነው፡፡
በወንጌል ትርጓሜ እነዚህን ቀሳጥያን በሁለት ዓይነት ይገልጻቸዋል፣
-
ሃይማኖተኛ የሚመስሉ መናፍቃን መምህራን
-
መንፈሳውያን የሚመሰሉ ሥጋውያን መምህራን ይላቸዋል፡፡ እነዚህ የተጠቀሱት ሁለቱ በተገቢው ሃይማኖት ላልተረዱ ሰዎች አደገኛ ናቸው፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ይገልጻቸዋል ስለመናፍቅነታቸው፣ የዋጃቸውን ጌታ ክደው … የሚያጠፋ ኑፋቄ አሾልከው ያገባሉ፡፡ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሏቸዋል፡፡ ስለ ሥጋዊነታቸው ደግሞ … ይልቁንም በርኲሰት ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱ … ነውረኞችና ርኲሳን … ምንዝር የሞላባቸው ኀጢአትንም የማይተው ዓይኖች አሏቸው የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፣ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው የተረገሙ ናቸው (1ጴጥ 2፥1-16)ይላል፡፡
እነዚህ ሃይማኖተኛና መንፈሳውያን የሚመሰሉ የቤተ ክርሰቲያን ጠላቶችን ከላይ ከቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው፣ ምእመናን ማንነታቸውንና ዓላማቸውን መረዳት አለብን፡፡ ማንነታቸው መጽሐፍ እንደጠቀሰው ተኩላነት ነው፣ ማለትም ምንም ግእዝ ቢጠቅሱ ወይም ላላዋቂ ያሬዳዊ ዜማ ያዜምኩ ቢመስሉ እነሱ በልባቸው ከሃዲያን ናቸው፡፡ዓላማቸውም በመመሳሰልአቀራረብ ተቀባይነትን አግኝተው፣ ይህን እግዚአብሔርን የሚያከብር ሕዝብ ከእምነቱ ለማናጋት ነው፡፡
በመመሳሰል ”የማይጸኑ ነፍሳትን ያታልላሉ” እንዲል፣ ክርሰቲያን ልብ ሊለው የሚገባው ዋናው ነገር፣ የተዋሕዶ ተጻራሪዎች ሁሉ ሁል ጊዜ የመመሳሰል ስልታቸውን በመቀያየር ያልጸኑትን ምእመንዋን መሻማት የዘመናት አሠራራቸው እንደሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ የፖርቱጋል ካቶሊክ ሚሲዮናውያን የካቶሊክ እምነትን ወደ አገራችን ለማስገባት በተለይ ቤርሙዴዝ፣ አንድሬ አብያዶ፣ ጴጥሮስ ፖኤዝና አልፎኑስ ሜንደዝ ወዘተ ተልከው ነበር፡፡ ከእነዚህ አብዛኞቹ ወደ አገራችን ሲመጡ ሆን ብለው አጥንተው ግእዝን መናገርናየያሬዳዊን ዜማ እስከማዜም የደረሱ ነበሩ፡፡ እንዲያውም በሮም ቫቲካን የኢትዮጵያ ኮሌጅ በማቋቋም የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያንን ቋንቋግእዝን የሚናገሩና ያሬዳዊን ዜማ የሚያዜሙ ነጮችን በመላክ የጎንደርን ቤተ መንግሥት እንዴት ሲያተራምሱት እንደ ነበሩ ታሪክያስረዳናል፡፡ ዛሬም የመመሳሰል ዓላማቸውን እውን ለማድረግ በአገር ውስጥ እንቅስቃሴአቸው የተለያየ ገጽታዎች ሲያሳዩ ይታያል፡፡ ለምሳሌ ይህንኑ ክብር ታቦትና ማኅሌት የሚወድ ህዝብን ለማታለልና ወደራሳቸው ለማስገባት አንድ ነን የሚል ስብከት፣ በዋና ዋና ከተሞች ባላቸው የጸሎት ቤት ታቦት አለን፣ ማኅሌት ይቆማል ሲሉ፣ ፕሮቴስታንት በበዙበት በሚመሰላቸው አካባቢ ደግሞ ፕሮቴስታንትንመመሳሰልይስተዋልባቸዋል፡፡ ሌሎችምየመመሳሰል አባዜ የተጠናወታቸው መናፍቃን እና ሥጋውያን እንደተለመደው ውጫውያንም ሆኑ የአገራችን በተለይ ከተዋሕዶ የወጡ ማለትም በቀሳጢዎች የተበሉ ካፈርኩ አይመልሰኝ እንዲል በቁጭት ሁል ጊዜ ይህንን ሕዝብ በመጎምዠት ለአጋንንት አሳልፈው ለመሰጠት ሲቋምጡና ለመንጠቅ ሲተጉይገኛሉ፡፡
ከላይ በግልጽ ለይተን አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ማንነት ባጭሩ ማብራራት እንደሞከርነው ሁሉ፣ ለምን ስልታቸውን መቀያየር አስፈለጋቸው የሚለውን ማየት ግድ ይለናል፡፡ ስልታቸውን መቀያየር ያስፈለገበት ምክንያት የተዋሕዶ እምነትና ሥርዓት አንዳች የማመን ፍላጎት አድሮባቸው አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን ሲወቅሱና ሲከሱ ነበርና፡፡
ለዚህ ምክንያት የደረሰባቸውን ክስረት መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ይህም፡-
-
የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባደረገችው ጸረ ተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ ህዝቡን በማስተማሯ ህዝቡ እኲይ ተግባራቸውን ስለተረዳ
-
ህዝቡ ራሱ መልስ በመስጠት ራሱን መከላከል ስለጀመረ
-
በስህተት መንገዳቸው ተጉዞ የነበረው ሕዝብ ወደ ቤቱ መመለስ ስለጀመረ
-
ቤተ ክርስቲያኗን በማጥላላት ያደረጉት ዘመቻ በመክሸፉ እንደማያዋጣቸው ስለተረዱ
-
ከቤተ ክርሰቲያኗ ህዘቡን እየደለሉ በማስኮብለል የሚያገኙት ይሁዳዊ ምንደኝነት ስለቀረባቸው
-
የካሴት ሽያጭ፣ የህዝቡ መዋጮ ወዘተ ገቢ ስለቀረባቸው ፤ ወዘተ ነው፡፡
ከላይ የተዘረዘረውና ሌላም የኪሳራ ምክንያቶቻቸውሳይወዱ በግድ ልባቸውን ጸፍቶ አፋቸውን ከፍቶ አነጋግሯቸዋል፡፡ ክርስቲያኑ ሁሉ ይህን ሁኔታ በቀላሉ ማየትናበዝምታ ማለፉ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ክስረት ያናጋው መናፍቅ ከዚህ የበለጠ ሌላ የድፍረት ዘዴ ለመፍጠር መሞከሩ አይቀሬ ነው፡፡ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይበግእዝና በያሬዳዊ ዜማ ያዘጋጁት ዝግጅት ገበያ ተኮርያውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናንን ማእከል ያደረገ መሆኑን ነው፡፡ልንረዳው የሚገባን አንዳንድ ምእመናን የማስመሰል ተንኮላቸውን ባለመረዳት ካሴታቸውን መግዛትና ማዳመጥ ሁለት አደጋ ያመጣባቸዋል፣ አንደኛው በመናፍቅ መንፈስ የተዘጋጀው ዜማ ማዳመጥ ራሱ ቆይቶ መናፍቅ ሚያደርግ መሆኑን፣ ሁለተኛው የመናፍቃን ከኪሳራቸው አንዱ ገንዘብ በመሆኑ አማኙን ህዝብ የሚያስቱበትን ገንዘብ ለነሱ መገበር ራሱ ከመናፍቅነት አይለይም፡፡
የአሁኑየለየላቸው መናፍቃን ወዳጅ የመምስል ስልታቸው ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ተኩላ በግን ለመምሰል ቆዳ ብትደርት ተኩላነቷን እንዳይቀይር ሁሉ ምእመናንን ያታልላሉ መስሎአቸው አንዴ ግእዙን አንዴ ዜማውን ያልኩ ቢመስላቸውም ”ዪህቺ ጠጋጠጋ … ” እንዲሉ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ይህ መሰሪነታቸው ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም ዓላማቸው የቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ፣ ታሪኳን ተናጋሪ፣ ዜማዋን ወዳጅ፣ ጥንታዊነቷን አክባሪ ወዘተ በመምሰል የህዝቡን ልብ ለማግኘት የተዘየደ ዘዴ ለማንም አይጠፋውም፡፡ ነገር ግን ዘዴው ጊዜ ያለፈበት ድሮ በነ ዐጼ ሱሱንዮስ ዘመን እነ አልፎኑስ ሜንደዝ የሞከሩት ነገር ግን እነ ዐጼ ፋሲል አውቀውት ምላሽ የሰጡበት፣ የማይረሳ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ መሆኑ ወገኔ ትዝ ሊለው ግድ ይለዋል፣ የብዙ ክርስቲያን ደም ተከፍሎበታልና፡፡ አሁንም ይህች መመሳሰልና ቀይ መስመር መጣስ የነ አልፎኑስ ሜንደዝ ድፍረት ጋር አንድ ናትና ከወዲሁ ካልታሰበባት በኋላ ከባድ ዋጋ እንዳታስከፍል ስጋታችን ነው፡፡
ዋናው ጉዳይ ባለፈው በተካሄደው የጸረ ተሐድሶ ዘመቻ መናፍቃን የፈራረሰባቸውን ሁለንተናዊ ክስረት ማለት በቤተ ክርሰቲያኗ ውስጥ ምእመኑን መናፍቅ የማድረግ ቅሰጣ ሲመታባቸውና ሴራው ሲከሽፍባቸው፣ ውድቀታቸውን መልሶ ለመገንባት ስፖንሰራቸው የሰጣቸው አዲሱ አሰራር በግልጽ ውዳሴ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንቋንቋ ግእዝ፣ ዜማዋ፣ ታሪኳ ወዘተ ማቅረብ ነው፡፡ ይህ የለየላቸው መናፍቃን ደርሶ የቤተ ክርስቲያኗወዳጅ መምሰል ለኛ አዲስ ነገር አይደለም፤ ተሐድሶቹም ሲጠቀሙበት የነበረ ስልት ነው፡፡ የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ በሚለው መጽሐፍ (በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያየማኅበረ ቅዱሳን ዶክሜንቴሽን ክፍል፣ ቁጥር 1፣ ሚያዝያ 2003 ዓም ገጽ 58) እንደተጠቀሰው ተሐድሶዎች ያቀዱት ዋና ጉዳይ ተሐድሶ እንኳን እንደሆነ የማያውቅ ግን ተሐድሶ የሆነ ትውልድ መፍጠር እና ሳያውቀው የሚደግፍ ቲፎዞ ማፍራት ነበር፡፡ ማለትም በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ሆኖ የመናፍቅን ዶግማ የተቀበለ የእነሱን ዜማ የሚያዜም ወዘተ ቡድን ማመቻቸት ነበረ፡፡ ስልቶቹን መጽሐፉ እንዲህ ይጠቅሳቸዋል፣
-
ተቆርቋሪ መምሰል፣ ገንዘብና እርዳታ በመስጠት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማትና ሕዝቡን መያዝ እና ቲፎዞ እንዲሆን ማድረግ፣
-
ኦርቶዶክስን የማያውቅ፣ ፕሮቴስታንት የሆነ፣ ነገር ግን ተሐድሶ (ፕሮቴስታንት) መሆኑን እንኳ የማያውቅ ምእመን ማፍራት፡፡ ማተብ ያሰረ፣ ነጠላ የሚያጣፋ፣ እምነቱና መንፈሱ ግንፕሮቴሰታንት የሆነ፣ ሆኖም ፕሮቴስታንት ነኝ የማይል (ፕሮቴስታንት መሆኑን ሳያውቅ ስለተለወጠ)፣ ”እኔ ኦርቶዶክስ ነኝ” እያለ የሚናገር(ሀርድ ዌሩ ሳይቀየር ሶፍት ዌሩ የተቀየረ)ትውልድ ማፍራት ነው፡፡
እንዲሁም በዚህ ወቅት ፕሮቴስታንቱ በግልጽ መሰደቡንና መወገዙን በውስጥ አድርገው በውጪ ውዳሴ የጀመሩት፣ የኦርቶዶክስ ምእመናንን በመመሳሰል ለመሳብና ቢቻላቸው ፕሮቴስታንት ለማድረግ ባይሆንም ቲፎዞ ለማድረግ፣ እንዲሁም ቲፎዞ በመሆን መካከል በሚፈጠረው ያለመግባባት ክፍተት ያልጸኑትን ለማግኘት ነው፡፡
ባጠቃላይምከላይ እንደገለጽነው መናፍቃን ምን ጊዜም የተወሰነ ሃይማኖታዊ የትውፊት፣ የዶግማ፣ የሥርዓት ወዘተ ገደብ የሌላቸው በመሆኑ የሌላውን መንጋ ለመቀሰጥ ቢቻላቸው በማጥላላት ባይቻላቸው በመመሳሰል ራሳቸውን እየለዋወጡ የተለያየ ስልት እንሚጠቀሙ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ለመመሳሰል በሚያደርጉት ቅሰጣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ያቆየችውን ትውፊት፣ ቅርስና ሀብት እንዲሁም ግእዝ ቋንቋና ያሬዳዊ ዜማን ማንም እንደፈለገ አስመስሎ ባልተገባ መንገድ የመቀራመቱ ድፍረት ቤተ ክርስቲያን እንዴት ታየዋለች? ያውም ቤተ ክርስቲያን የማትፈቅደው የመናፍቅ ድርጅት በሀብቷ ላይ ሲፈነጭ፣ ይህስ ጉዳይ ከህግ አንጻር እንዴት ይታያል? አንድ ተቋም ያላትን ሀብት ያለፈቃዷ ማንም መጠቀም ይችላልን? ምእመናን በሙሉ በተለይ የሕግ ባለሙያ ልጆቿ እንዲነጋገሩበት የሚስፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ምእመናን መገንዘብ የሚገባን መናፍቅ ያወጣውን የቅስጥ ዜማ ያሬዳዊ መስሎን በመጠቀም የዓላማቸው ሰለባ እንዳንሆን አንዱ ለሌላው ማሳሰብና ማስረዳት ተገቢ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የበግ ለምድ ለብሰው ማለት እውነተኞች መስለው ከሚመጡ ሐሰተኞች፣ ሃይማኖታውያን መስለው ከሚመጡ መናፍቃን፣ መንፈሳውያን መስለው ከሚመጡ ሥጋውያን መምህራን ተጠንቀቁ ብሎ አስተምሮናልና እንጠንቀቅ፣ እርስ በርሳችንም እንጠባበቅ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡