የዝቋላ ገዳም እንዴት አደረ?
መጋቢት 12/2004 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ገዳም ደን ላይ ከቅዳሜ ጀምሮ የተቀሰቀሰው ቃጠሎ እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ የዘለቀ ሲሆን ሌሊቱን ግን በሰላም እንዳደረና የመርገብ ሁኔታ እየታየበት መሆኑን በስፍራው የሚገኙ ምእመናን ገለጹ፡፡ ቃጠሎው ቢበርድም የተዳፈነው ፍም ነፋሱ እያራገበው በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ጭስ እየታየ እንደሆነ በተለይም የቅዱሳን ከተማ የተሰኘው የአባቶች የጸሎት ሥፍራ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጪስ በመጨስ ላይ መሆኑን በስጋት በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ቃጠሎው ዳግም ካገረሸ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሊያመራ እንደሚችል መነኮሳቱ ይናገራሉ፡፡
ከሥፍራው በደረሰን መረጃ መሠረት ምእመናን የመዳከም ሁኔታ የሚታይባቸው ሲሆን የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ሌሎችም ምእመናን ወደየመጡበት በመመለስ ላይ ናቸው፡፡ የፌደራል ፓሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ ከቀሩት ምእመናን ጋር በመሆን የሚጨሰውን ፍም በማጥፋት ሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ ወደ ዝቋላ ገዳም ከተለያዩ አቅጣጫዎች ምእመናን እየሔዱ ሲሆን በሥፍራው የሚገኙ ምእመናን አሁንም ተጨማሪ የሰው ኀይል እንዲደርስላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡