ቃና ዘገሊላ(ለሕፃናት)
ጥር 17/2004 ዓ.ም
በአቤል ገ/ኪዳን
አንድ ቀን በገሊላ አውራጃ ቃና በሚባል ቦታ የሚኖር አንድ ዶኪማስ የሚባል ሰው ሰርግ ደግሶ እመቤትችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እና ሌሎች ብዙ ሰዎችን ጋበዘ፡፡ እመቤታችንም በግብዣው ላይ ከልጇ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር፣ ከሐዋርያት ጋር ተገኘች፡፡
ምግቡና መጠጡ ቀረበ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ግን የወይን ጠጁ አለቀ፡፡ በዚህ ጊዜ የሰርጉ አስተናጋጆች በጣም መጨነቅ ጀመሩ፡፡ ለእመቤታችንም የወይን ጠጅ ማለቁን አማከሯት እመቤታችንም የሰርጉን ቤት አስተናጋጆች በተለይም ዶኪማስን ተጨንቆ ስታየው በጣም አዘነች፡፡ ለልጇ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የወይን ጠጁ እንዳለቀባቸውና አስተናጋጆቹ እንደተጨነቁ ነገረችው፡፡
ጌታም ባዶ የሆኑት የወይን ጋኖች ላይ ውኃ እንዲሞሉ አዘዛቸው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ጌታችን የሚለውን እንዲያደርጉ ነገረቻቸው፡፡ አስተናጋጆቹም ጋኖቹ ላይ ውኃውን ሞሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ውኃውን ወደ ወይን ለወጠው፡፡ ዶኪማስም በጣም ደስ አለው፡፡ በሰርጉ ላይ የተጋበዙት እንግዶችም አዲሱን የወይን ጠጅ ሲጠጡ በጣዕሙ እጅግ ተደነቁ፡፡ ዶኪማስንም ጠርተው ሌሎች ሰዎች ጥሩውን መጠጥ አስቀድመው ይሰጡና በኋላ ደግሞ ብዙም የማይጥመውን ያቅርባሉ፡፡ አንተ ግን የማይጥመውን አስቀድመህ አቅርበህ ጣፋጩን ወይን ከኋላ አመጣህ በማለት አሞገሱት፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አምላክ መሆኑን ከሚያሳዩት ተአምራት አንዱን በዚያ ዕለት በሰርጉ ቤት አደረገ፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትም በዚያን ዕለት ታወቀ፡፡ ይህ ተአምር የተፈጸመው በጥር 12 ቀን በመሆኑ ሁል ጊዜ ጥር 12 ቀን “የቃና ዘገሊላ” በዓል በመባል ይከበራል፡፡