የሰለሞን ምቅናይ ምስል ወድምጽ /ቪሲዲ/ ተመረቀ
ኅዳር 6/2004 ዓ.ም
በፈትለወርቅ ደስታ
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን “የሰለሞን ምቅናይ በተክሌ ዝማሜ በሚል ርእስ የተዘጋጀ ምስል ወድምጽ /ቪሲዲ/ ቅዳሜ ኅዳር 2/2004 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ተመረቀ፡፡
በምረቃው ላይ ብፁዕ አቡነ ሰላማ የአክሱም ጽዮን ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የደቡብ ጐንደር ሊቀ ጳጳስና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም በምረቃው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆነውን የዜማ፣ የአቋቋም ሥርዓት ጠብቃ በእንዲህ ዓይነት መልኩ ለምእመናን እንዲዳረስ ማኅበሩ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣና ወደፊትም ከዚህ በተሻለ መልኩ እንደሚሠራ ገልፀዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ እንድርያስም በዕለቱ “ምቅናይ” በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም ይህ የቤተ ክርስቲያን ቅርስና ሀብት ዜማ ዝም ብሎ የተገኘ ሳይሆን ሊቃውንቱ እድሜያቸውን ሙሉ ሲማሩት የኖሩት መሆኑንና ይህን የቤተ ክርስቲያን ሀብት ደግሞ በእንዲህ ዓይነት መልኩ ለትውልድ የማስረከብ ኃላፊነት የሁሉም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ በየኔታ ተክሌ ሲራክ አማካይነት በተክሌ አቋቋምና ዝማሜ ታሪክ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ የቀረበ ሲሆን ይህ የተክሌ ዝማሜ በደብረ ታቦር ኢየሱስ ገዳም እስከ አሁን ድረስ የተክሌ አቋቋም ጉባኤ ምስክር ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ይህ ጅማሮ ጥሩ መሆኑን ገልፀው ይህ ዝማሜ የሊቃውንቱ ቢሆንም ለእይታ የበቃው በማኅበረ ቅዱሳን አማካይነት መሆኑና ማኅበሩም በዚህ ዙሪያ ከፍተኛ ኃላፊነትን ወስዶ የድርሻውን እየተወጣ እንደሆነ ገልጸው ነገር ግን ገና አልተነካም ወደፊት ብዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ቪሲዲው የተዘጋጀው በማኅበረ ቅዱሳን በሙያ አገልግሎት እና አቅም ማጎልበቻ ክፍል ዘርፍ ፕሮጀክት ተጠንቶና ሊቃውንቱ መክረውበት ነው፡፡