በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች የአቋም መግለጫ አወጡ።

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
ሐምሌ 11፣ 2003 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ወቅታዊውን የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴና ተዛማጅ ጉዳዮችን አስመልክተው መግለጫ አወጡ። በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ በልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙሃን ከመምሪያው ሊቀ ጳጳስ እውቅና ውጭ «ተሐድሶ የሚባል ነገር የለም» በሚል የተሰጠው መግለጫ ሰ/ት/ቤቶች የማይቀበሉት መሆኑን አሳወቁ።
 
ሐምሌ 11 ቀን 2003 ዓ.ም በአድራሻ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፥ በግልባጭ ለሚመለከታቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነትና የመንግስት አካላት የተሰራጨው ደብዳቤ፥ ሀገረ ስብከቱ ከቤተ ክርስቲያን የበላይ አካላት ጋር በመመካከር አስቸኳይ እልባት እንዲያመጣና ለሕዝብ፣ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ ሥራ እንዲሰራ አጽንኦት ሰጥቶ ያሳስባል።

«የኢትዮጵያ ሀገራችን የአፍሪካ ኩራትነት፥ ለመላው ጥቁር ሕዝብ አለኝታና መመኪያ መሆኗን፥ በዚህም ሠይጣናዊ ቅናት ያደረባቸው ጠብ ያለሽ በዳቦ የሚሉ ምዕራባዊያን ይህችን ለሀገራችን ታላቅ የታሪክ አሻራ ያስቀመጠች ቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት የማይፈነቅሉት ድንጋይና የማይቆፍሩት ጉድጓድ የለም።» በማለት የሚያወሳው ደብዳቤው «በየዘመኑ በነበሩና ረድኤተ እግዚአብሔር ባልተለያቸው ቆራጥ ልጆቿ ተጋድሎ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ እስከ ዘመናቸን ደርሳለች» ይላል።

«ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የወላድ መካን አይደለችምና፥ ‘ዛሬም ከቤተ ክርስቲያን በፊት እኛን ያስቀድመን፣ የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት አያሳየን’ የሚሉ እስከ ሰማዕትነት ራሳቸውን ያዘጋጁ እንደሚኖሩ ማሰቡ ሳይበጅ አይቀርም» በማለት እምነቱን ይገልጻል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያና አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፥ ሕገ ወጥ ሰባክያንንና ዘማርያንን ለማስቆም ደረጃውን ጠብቆ የጻፉትን ደብዳቤና የሰንበት ትምህርት ቤቶችን አንድነት ለማጠናከር የሚያደርጉትን ጥረት የሚያመሰግነው መግለጫው፤ ከተሾሙ ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ አንዳች የሚጠቀስና የሚጠቅም ሥራ አላበረክቱም ያላቸውን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ አባ ሠረቀ ብርሃን ግንቦት 23 ቀን 2003 ዓ.ም የሰጡትን መግለጫ አስደንጋጭና አሳዛኝ እንደሆነበት ያወሳል።

የአባ ሠረቀ መግለጫ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን የማይወክል ከመሆኑም በላይ፥ በአሁኑ ወቅት በየአድባራቱና በየገዳማቱ ተፋፍሞ የቤተ ክርስቲያኗን ሰላምና አንድነት በመፈታተን ላይ የሚገኘውን የመናፍቃን ሴራ ጆሮ ዳባ ልበስ እንደማለት አለዚያም እንደመደገፍ ይቆጠራል፤ በዚህም በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ላይ የነበረን እምነትም እንዲጠፋ ሆኗል ይላል።

ለዚህ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ እየሰጡት ያለው ሽፋን ምእመናንን በከፍተኛ ሁኔታ በማስቆጣቱ በየቦታው ሁከት እየተፈጠረ ይገኛል በማለት የሚጠቁመው መግለጫው፥ በተለያዩ አካባቢዎች ለተከሰተው ችግር ተዋንያን በመሆን የሚታወቁ ግለሰቦችን በተለያዩ የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎች ላይ በኃላፊነት የማስቀመጥ ሂደት እየተካሄደ መሆኑን መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ጠቅሶ፥ የከፋ ችግር ሊያመጣ እንደሚችልና ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያስገነዝባል።

በአሁኑ ሰዓት የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ ለመግታት ብሎም ከቤተ ክርስቲያን ለማጽዳት ባለድርሻ አካላትና ሰንበት ትምህርት ቤቶች እያደረጉ ያለውን ጥረት የሚያደናቅፉት የማደራጃ መምሪያው ኃላፊ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር/የእዝ ሰንሰለት/ ሳይጥብቁ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰጡት አደናጋሪ መመሪያዎች፥ ሰ/ት/ቤቶች የተሃድሶ መናፍቃንን ዘመቻ ለመግታት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ይገልጻል።

የተሐድሶ መናፍቃን የዘመቻ ምልክቶች የሆኑት የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓት ያልጠበቁ ስብከቶችና ዝማሬዎች በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንንና የሰ/ት/ቤቶችን ህልዉና በመፈታተን ላይ ይገኛል እንደሚገኝ የሚያሳስበው መግለጫው፥ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የአቋም መግለጫ አውጥተናል በማለት ይገልጻል።

ሰ/ት/ቤቶቹ ባወጡት ባለ 6 ነጥብ መግለጫ፥ ቅዱስ ሲኖዶስ በተለያዩ ጉባኤያት ያስተላለፈውና የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲከበሩና እንዲተገበሩ፥ በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ በልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙኃን ከመምሪያው ሊቀ ጳጳስ እውቅና ውጭ «ተሐድሶ የሚባል ነገር የለም» በሚል የተሰጠው መግለጫ ሰ/ት/ቤቶች የማይቀበሉት መሆኑን እያሳወቅን ተገቢው እርማት በመገናኛ ብዙኃን እንዲሰጥበት፥ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የተሐድሶ መናፍቃንን ጉዳይ በማስፈጸም ላይ የሚገኙ ሕገ-ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን በየትናውም የቤተ ክርስቲያናችን ዓውደ ምሕረት ላይ እንዳይቆሙ ለተመሳሳይ ዓላማ በሚንቀሳቀሱትም ተጣርቶ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ፥ የተሐድሶ መናፍቃንን ሴራ የማጋለጥ የምእመኑን በቅድስት ተዋሕዶ እምነቱ የማጽናት ሥራ ተጠናክሮ እንዲሠራ፥ ከቤተ ክርስቲያን እውቅና ውጭ በቤተ ክርስቲያኗ ስም የሚተላልፉ የቴሌቪዥን ፕሮግራም፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተምሮ የሚያፋልሱና በኑፋቄ የታጀቡ መጻሕፍት ጋዜጦች፣ ካሴቶችና ቪሲዲዎች እንዲሁም መካነ-ድሮች የቤተ ክርስቲያንን ስም እንዳይጠቀሙ፣ ተጠቅመው ከተገኙ በሕግ እንዲጠየቁ የሚሉና ሌሎች ነጥቦችንም አካትቷል።

መግለጫው በማጠቃለያው እነዚህን ችግሮች ጊዜውን የጠበቀ መፍትሔ ሳይሰጣቸው ቢቀርና ተዳፍነው ቢቆዩ የምእመናንና የሰ/ት/ቤቶች አባላት ቁጣ ውስጥ ውስጡን ሲቀጣጠል ቆይቶ ድንገት ከፈነዳ አደጋው በቤተ ክርስቲያንና በሀገር ላይ የከፋ ጉዳት ስለሚያደርስ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ዛሬ ነገ ሳይባል የእርምት እርምጃ መውሰድ ይበጃል በማለት ይገልጻል።