ለሐመር መጽሔት መካነ ድር /website/ ተሠራለት፡፡
በቀደመው ጊዜ ብዙ የተደከመባቸውና ዋጋ የተከፈለባቸው የኅትመት ውጤቶች ምዕመናን እንዲጠቀሙበት ታስቦ እንደተሠራ በማኅበረ ቅዱሳን የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ሓላፊ ዲ/ን ዘላለም ቻላቸው ተናግረዋል፡፡
ለወደፊቱም የሚወጡትን የመጽሔቷን ዝግጅቶች በሽፋን /cover/ ገጽ በማስተዋወቅ ሥርጭቷን ከፍ የማድረግና በዚህም ስብከተ ወንጌልን የማስፋፋት ተልዕኮን የበለጠ ማሳለጥን ዓላማ ያደረገ እንደሆነ የገለጹት ዲ/ን ዘላለም ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ የጽሕፈትና የመገናኛ ቴክኖሎጂውን በቀዳሚነት ስትጠቀም ቆይታለች፡፡ አሁን ደግሞ የሰዎች ኢንተርኔትን የመጠቀም እውነታ ቤተ ክርስቲያንን ተወዳዳሪ ሊያደርጋት ይገባል በማለት አያይዘው አስረድተዋል፡፡
በአንዳንድ አቻ መካነ ድሮች ከጥንት አባቶች እስከ ቅርብ ጊዜ ያሉት ጽሑፎችና ሥራዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡ በአገራችንም አንዳንድ የኅትመት ውጤቶች የቀጥታ የኢንተርኔት/Online Journalism/ ዘገባ እየጀመሩ እንደሆነ ሌሎችም የቆዩ ሕትመቶቻቸውን የሚያስነብቡበት መካነ ድር እንዳላቸው ይታወቃል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ቅድሚያ እንደሚሰጥ የሚገልጹት ዲ/ን ዘላለም በብዙ ሀገሮች መድረስ የሚችል መካነ ድር በአሁኑ ጊዜ ተመራጭ ሚዲያ እንደሆነ ነው፡፡
ለወደፊቱም ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ ለጥናትና ምርምር ማእከል፣ ለቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሁም ለሌሎች ዋና ክፍሎች ድረ ገጾችን የመሥራት ሐሳብ እንዳለ ሓላፊው አስታውቀዋል፡፡
መካነ ድሩን ያዘጋጁት አቶ ደመላሽ ጋሻው በኤሌክትሮኒክስ ሚድያ ክፍል የቴክኖሎጂ ንዑስ ክፍል አባል ሲሆኑ በዚህ ወቅት መካነ ድሩ ከ45 እትሞች የሚበልጡ ከ1985 እስከ 2001 ዓ.ም የሚገኙ እትሞችን /ከጠቅላላው እትም ከ45-50% የሚሆን /እንዳካተተ ተናግረዋል፡፡ በሰው ኃይል እጥረት፣ በአንዳንድ እትሞች አለመገኘት ወይም ተጠርዘው መቀመጣቸው ስካን /Scan/ ለማድረግ አለመመቸቱ ሁሉንም የቀድሞ እትም መልቀቅ አልተቻለም በማለት አስረድተዋል፡፡ያልተሟሉ ቀሪ ሕትመቶችም በየጊዜው ስካን እየተደረጉ እንደሚጨመሩ አክለው ገልጸዋል።
መካነ ድሩ በአሁኑ ጊዜ ለመጠቀም ምቹና ቀላል ሲሆን እትሞቹንም በዓመት ማግኘት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ምን እንደተለወጠ የሚገልጽ አካል አካቷል፡፡ ለወደፊትም የሕትመት ውጤቶችን በደራሲ፣ በእትም ቁጥር፣ በውስጡ ይዘት /content/፣ የመጽሔቱን ዓምዶች መሠረት ባደረገ ክፍፍል የፍለጋ /Search/ ሥርዓትን ያካትታል፡፡ ከዚህም በላይ የቀጥታ ሽያጭ /Online selling/ እና የቀጥታ ምዝገባ /Online Registration/ እንደ ቴክኖሎጂው ተጨባጭ ሁኔታ ይይዛል በማለት አቶ ደመላሽ አስታውቀዋል፡፡
መካነ ድሩን ለመስራት የሚያስፈልገው ወጪ ከ10,000-15,000 ብር የሚገመት ሲሆን ሥራውም ከዓመት በፊት እንደተጀመረ ታውቋል፡፡ ሐመር መጽሔት በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻና በ21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት፣ በእቅበተ ቤተ ክርስቲያን /Apology/፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዲጠበቅ በማሳሰብ /በማስተማር/ ታዋቂነት ያላት መጽሔት ናት።
መጽሔቷም በስርጭት ስፋትና በሽያጭ የመጀመሪያ ስትሆን ላለፉት ተከታታይ 18 ዓመታትም ያለ ማቋረጥ በማገልገል ታሪካዊ ናት፡፡