በማኅበረ ቅዱሳን የኅትመት ውጤቶች ላይ ተጥሎ የነበረው የአባ ሠረቀ ሕገ ወጥ ደብዳቤ ተሻረ

ተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሣሙኤል ማኅበረ ቅዱሳን የሚያሳትማቸው መጽሔትና ጋዜጣ ለኅትመት እንዳይውሉ የጻፉት ሕገ ወጥ የእግድ ደብዳቤ እንዲነሣ መደረጉን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፊርማ በቀን 01/10/2003 ዓ.ም ተጽፎ ለሚመለከታቸው አካላት የተሠራጨው ደብዳቤ እንዳመለከተው የማኅበረ ቅዱሳንና የመምሪያው ጉዳይ በወርኃ ግንቦት በተደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ በአጀንዳነት ቀርቦ ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት አጣሪ ኮሚቴ ተሰይሞ ባለበት ሁኔታ የመምሪያው ሓላፊ ሕገ ወጥ የእግድ ደብዳቤ መጻፉ አግባብ አይደለም ይላል፡፡

ማኅበሩ እገዳው አግባብ አለመሆኑን ለሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ባቀረበው አቤቱታ ገልጿል።

ብፁዕነታቸው ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ በቀን 29/09/2003 ዓ.ም በጻፉት ደብዳቤ «የመምሪያው ሓላፊ የማኅበሩ መጽሔትና ጋዜጣ ኅትመት ላይ እንዳይውሉ በማለት ለተለያዩ ማተሚያ ድርጅቶችና ብሮድካስት ባለሥልጣን መጻፉን አመልክቶ፥ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ በአጀንዳነት ቀርቦ ችግሩን በዘለቄታው ለመፍታት ያስችል ዘንድ ጉዳዩን አጥንቶ የሚያቀርብ ከብፁዓን አበውና ከሊቃውንቱ የተውጣጡ አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ ባለበት ወቅት ይህ የእግድ ደብዳቤ መጻፉ አስፈላጊ ነው ብዬ ባላምንም ከእኔ በላይ ሆኖ ስላገኘሁት ይህንኑ ጉዳይ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በትኩረት ተመልክቶ መፍትሔ እንዲሰጥበት» ማለታቸውን ተጠቅሷል፡፡

ይህንን የማደራጃ መምሪያውን የበላይ ሊቀ ጳጳስ ማሳሰቢያ ተከትሎም «የመጽሔትና ጋዜጣ ሕትመት እገዳው እንዲነሳ የተደረገ መሆኑን እናሳውቃለን» የሚለው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ደብዳቤ ነው። በተጨማሪም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ስላለ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ እንቅስቃሴ ጉዳይ ተጣርቶ የሚያቀርብ ብፁዓን አባቶች ያሉበት ኮሚቴ ተሰይሞ ሥራውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ ባለበት ወቅት ንትርክና ጭቅጭቅ መፈጠሩ የማጣራቱ ሥራ ሒደት ላይ እንቅፋት ሊፈጠር እንደሚችል ጠቁሟል፡፡

ይኸው የእገዳ ደብዳቤ እንደተነሣ ለብሮድካስት ባለሥልጣን እና ለሌሎች ስድስት ማተሚያ ቤቶች የተጻፈ ሲሆን ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም በግልባጭ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡

 
የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሣሙኤል በጻፉት ተገቢ ያልሆነ የእገዳ ደብዳቤ ባለፈው ቅዳሜ ለኅትመት ገብታ የነበረችው 18ኛ ዓመት ቁጥር 18 ቅጽ 18 ቁጥር 226 /ከሰኔ 1 እስከ 15 ቀን 2003 ዓ.ም/ እትም ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የኅትመት ጊዜዋ እንደተስተጓጎለ ታውቋል፡፡

ይሁንና ጋዜጣው በትናንትናው ዕለት ማለትም ግንቦት 30 ቀን 2003 ዓ.ም ለኅትመት በቅታ ምእመናን ዘንድ ደርሳለች፡፡

በቤተ ክርስቲያኗ መዋቅር ሥር ሆኖ በሚንቀሳቀሰው ማኅበረ ቅዱሳን አሳታሚነት ኅትመቷን ከጳጉሜን 5 ቀን 1985 ዓ.ም የጀመረችው ስምዐ ጽድቅ ለአንድም ዘመን ኅትመቷ ሳይስተጓጎል ምእመናንን ትምህርተ ሃይማኖትን በማስተማር፣ እምነትን በማጽናት፣ መናፍቃንንና አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን በማጋለጥ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በመዳሰስ ስታበረታና ስታጽናና እንደቆየች ይታወቃል፡፡