‹‹በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡›› ፊልጵስዩስ 2፡6
በጌታችን ልደት ያገኘናቸውን በረከት እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡
1.ልጅነትን አግኝተናል፡፡
የሰው ልጅ የተፈጠረው በአርአያ እግዚአብሔር ሲሆን የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስሙን ይቀድስ ክብሩን ይወርስ ዘንድ ነው፡፡ ነገር ግን የምኞት ፈረስ ከልጅነት ይልቅ አምላክነት እንዲመርጥ ገፋፋው፡፡ ስለዚህም ልጅነቱን በፈቃዱ አጣ፡፡ ምንም አንኳን የሰው ልጆች ልጅነታቸውን ቢጥሉ እግዚአብሔር አምላክ ግን አባትነቱን አልተወም፡፡ በነቢያት እያደረ መምህራንን እያስነሳ ዳግመኛ ልጆቹ እንዲሆኑ መክሯል፣ አስመክሯል፣ ‹‹እናት ልጇን እንደምታጽናና እንዲሁ እኔም አጽናናችኋለሁ›› ኢሳ 66:13 በማለት አባትነቱን ተናግሯል፡፡ ይህን ያጣነውን ልጅነት ሊያስመልስልን ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም ሰው ሆነ፡፡ ባርነታችን ወደ ልጅነት፣ ባዕድነታችን ወደ ወራሽነት ተለወጠ፡፡ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንደ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ›› ገላ 4፡7 በማለት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ በልደቱ እንዳገኘን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ገልጧል፡፡ በክርስቶስ ልደት ማመን ከልደቱም በረከት መካፈል ልጅነትን የሚያሰጥ ታላቅ ምስጢር ነው፡፡ መጽሐፍም ‹‹የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፤የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም፤ ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው›› ዮሐ 1፡11 በማለት ልጅነታችንን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ልጆቹም ስለሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮህ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ›› ገላ 4:6 በማለት ልጅነታችንን እንዳገኘን ያረጋግጣል፡፡
2. ነጻነታችን አግኝተናል፡፡
ሰው ነጻ መሆኑ የሚታወቀው ፈቅዶ በመረጠው ነገር ያለምንም ከልካይ መኖር ሲችል ነው፡፡ ከውድቀቱ በኋላ የሰው ልጅ ያጣው ታላቅ ነገር ቢኖር ነጻ ፈቃዱን ነበር፡፡ ጽድቅን መርጦ በጽድቅ መንገድ ቢጓዝ እንኳ መንግሥቱን ለመውረስ አይችልም ነበር፡፡ ነቢያትም አምርረው ሲያለቅሱ የነበረው ‹‹ጽድቃችን የመርገም ጨርቅ ሆነ›› በማለት ነበር፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ይህን ነጻነታችንን አስመልሶልናል፡፡ ‹‹በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን›› ገላ 5፡1 እንዳለ፡፡ የጌታን ልደት መላእክቱ ለኖሎቱ ሲያበስሩም እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ›› ሉቃ 2፡14፡፡ ከእስር የተለቀቀ ሰው ነጻ እንደሆነ ሁሉ የሰው ልጅም ለሺህ ዘመናት በዲያብሎስ ግዞት ይኖር ስለነበር በልደቱ ከዚህ እስር በመላቀቁ ነጻነቱን አግኝቷል፡፡
3. ሰላማችን ተመልሷል ተስፋችን ተሳክቷል፡፡
በቀደመው ዘመን ከልደተ ክርስቶስ በፊት ሰው ሰላሙን አጥቶ ይኖር ነበር፡፡ ‹‹ የሰላምን መንገድ አያውቁም… መንገዳቸውን አጣመዋል፤ የሚሄዱባትም ሁሉ ሰላምን አያውቁም›› ኢሳ 59፡7 በማለት ሰላም አንዳልነበረ አስረድቷል፡፡ ልደት እውነተኛ ሰላማችንን ያገኘንባት፣ ተስፋችንም የተረጋገጠበት ልዩ ቀን ናት፡፡ ከእግዚአብሔር ፈቃድ በመውጣት ያጣነው ሰላም በልደቱ ተመልሷል፡፡ ሰላምን የሚያድል እርሱ ስለሆነም ‹‹ሰላሜን እሰጣችኋለሁ›› ብሏል፡፡ ለብዙ ዘመናት ሰላምን ብንነፈግም እውነተኛ ሰላምን ያገኘነው በክርስቶስ ልደት ነው፡፡ ‹‹ሰላም በምድር ሆነ›› ብለው መላእክት የዘመሩትም በልደቱ ነው፡፡በልደት ካገኘናቸው ገጸ በረከቶች በተጨማሪ ሌሎች ለሕይወታችን ጠቃሚ የሆኑ መልእክቶችንም አግኝተናል፡፡ በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ምሳሌ የሆነ ዐቢይ ቁም ነገሮችንም በልደቱ ገብይተናል፡፡
ሀ. ትህትና
እግዚአብሔር አምላክ ‹‹እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝ›› በማለት ትህትና የባህርይ ገንዘቡ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ በልደቱም ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለማመን በሚከብድ ፍፁም ትህትና ራሱን ዝቅ አድርጎ ለሰዎች ተገልጧል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያዕቆብ ‹‹በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም›› ዘፍ 40:9 የሚለው የትንቢት ቃል ተፈጻሚ እንዲሆን ከይሁዳ ወገን ቢወለድም ቅሉ ከይሁዳ ግዛትም ታናሽ በሆነችው ቤተልሔም እንደተወለደ መጻሕፍት ይነግረናል፡፡ ‹‹አንቺም ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ አንቺ ከይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ›› ሚክ 5:2፣ ሉቃ 1:5 ማቴ 1:1 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከታናሿ ቤተልሔም ለመወለድ የመረጠው በበረት ግርግም ውስጥ ነው፡፡ ሁሉ የእርሱ የሆነ አምላክ ምንም እንደሌለው የሆነው የትህትናን ልዕልና ሊገልጽልን ፈልጎ ነው፡፡ ፍፁም የሆነ ትህትና መገለጫው ያለንን ነገር እንደሌለን መቁጠርና መተው ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስም ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡ ባለፀጋ ሳለ ደሀ ሆነ ፤ ሁሉ የሞላለት ሳለ ማደሪያ ስፍራ አጥቶ በበረት (ግርግም)ተወለደ፡፡ ይህንን ትህትናውን በጥምቀቱ ገልጿል፤ ወደ ፈጠረው ዮሐንስ ሄደ ‹‹እንግዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል›› በማለት ጽድቅ ለፍፁም ትህትና የሚደረግ ሕይወት እደሆነ አስረድቶናል፤ ማቴ 3:14፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ትህትና እንዲህ በማለት ገልጾታል፡፡ ‹‹የባሪያውን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ›› ፊሊ 2:6 ‹‹ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አነሰ›› ዕብ 2፡9 ‹‹ስለዚህ የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተሰረይ….በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው›› ዕብ 2፡17 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጀመሪያው እስከ ፍጻሜው ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በትህትና የተደረጉ ናቸው፡፡ ወደ ምድር ሲመጣ ፍፁም ትህትና ባላት በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አድሮ መጣ፡፡ ሲወለድ በቤተልሔም በበረት ግርግም፣ ሲጠመቅ ባገልጋዩ በዮሐንስ እጅ፣ ወደ መስቀል ሲወጣም በፈጠራቸው ፍጡራን እጅ መሆንን ስንመለከት እውነትም እግዚአብሔር የትህትና ባለቤትና የትሁታን ወዳድ መሆኑን እንረዳለን፡፡
ለ. ፍቅር
እግዚአብሔር ሰውን ለምን ወደደው; ብለን ብንጠይቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠን መልስ ቀላልና ግልፅ ነው፡፡ ‹‹…እንዲሁ…›› ዮሐ 3:16፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለመውደድ /ለማፍቀር/ ምክንያት የለውም፡፡ ኃጢአተኛና ጻድቅ፣ ንጹሕና ቆሻሻ፣ ምሁርና ያልተማረ፣ የሚል መመዘኛም በአምላክ ዘንድ የለም፡፡ እግዚአብሔር እንዲወደን ሰው መሆናችን ብቻ በቂ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከማፍቀሩ የተነሳ ዓለምን እንዲያድን አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከው፡፡ በልደትም የምናየው ይህን የአምላካችንን ልዩ ፍቅር ነው፡፡ ቀድሞ በነቢያት ‹‹በዘላለም ፍቅር ወድጃችኋለሁ›› ኤር 31:3 በማለት ፍቅሩን ገልጦ ነበር፡፡ ይህን ፍቅሩን ደግሞ በልደቱ በይበልጥ ገለጠው፡፡ ሰውን ለመውደድ ምክንያት የምናበዛ ሰዎች ስንቶች ነን? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልደቱ ያሳየንን ግሩም ፍቅር ለእህት ለወንድሞቻችን በማሳየት ክርስቶስን በግብር ልንመስለው ይገባል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ወርዶ በበረት ግርግም የተወለደው እስከ መስቀል ሞትም የደረሰው ለሰው ልጅ ባለው ፍፁም ፍቅር መሆኑን መገንዘብ ያደረገውን የትህትና ስራ መመልከት የልደትን መንፈሳዊ ምስጢር እንድንረዳ ያደርገናል፡፡ ካለዚያ ልደትን ለመታሠቢያነት ብቻ ከማክበር የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በእግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረ ሰውን ፍፁም በሆነ ፍቅር መውደድ ከባድ ቢሆንም እንኳ የማይቻል ነገር ግን አይደለም! ሰውን መውደድ ቀስ በቀስ እየዳበረ እስከ ፍጽምና የሚያደርስ መንፈሳዊ ሀብት ነው፡፡ በፍቅር ላይ ያልተመሠረተ መንፈሳዊ ሱታፌ፤ መንፈሳዊ ሕይወት መጨረሻው አያምርም፡፡ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ሕይወት ‹‹በሁሉ ይጸናል›› 1ኛ ቆሮ 13:7 የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደትም የፍቅር የመጨረሻው ማሳያ መሆኑን መገንዘብ ሕይወታችንን በዚህ መነጸርነት እንድናይ ያግዘናል፡፡
ሐ. ተስፋን መፈጸም፡-
እስራኤል ዘሥጋ የመሲሑን መምጣት በተስፋ ሲጠብቁ ቢቆዩም የክርስቶስን ሰው ሆኖ መምጣት ለመቀበል ዳተኞች ነበሩ፡፡ መጽሐፍም ‹‹የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም›› ዮሐ 1:7 ይላል፡፡ ነቢያት በሙሉ እግዚአብሔር የሰው ዘር ማዳኑን በተስፋ ሲጠብቁ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ተስፋውን ሊፈጽም አንድያ ልጁን ወደ ምድር ላከ፡፡ ተስፋችንም ተፈጸመ፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ›› ገላ 4:4 ይላል፡፡ ነቢያት ይህን ቀን በተስፋ ሲጠብቁ እንደነበር በትንቢታቸው ገልጸዋል፡፡ ኢሳ 7:14 ፣ ኢሳ 9:6 ፡፡ አምላካችን ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ የሰጠን ነገር ቢኖር ተስፋን ነው ‹‹እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፡፡›› ዘፍ 3:22 በማለት ሰው ሆኖ ወደ ምድር እንደሚመጣ ተስፋን ሰጠን፡፡ ይህንም ተስፋ ይዘን ለሺህ ዘመናት በጉጉት ጠበቅን ነቢዩ አንደተናገረው አምላክ ጻሕቀ ልቡናችን ፈጸመልን፡፡ ‹‹ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች›› ኢሳ 40:80 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው የገባውን ቃል አስታውሶ ወደ ምድር እንደመጣ ሁሉ በእርሱ ስም የሚጠሩ ክርስቲያኖችም የገቡትን ቃል፣ የሰጡትን ተስፋ በመፈጸም አምላካቸውን መምሰል ይገባቸዋል፡፡ የተሰጣቸውን ሥራ በጊዜ የማይጨርሱ፣ ጉባኤ የሚያስተጓጉሉ፣ ሰው ቀጥረው ሲያረፍዱ እንኳ ቅንጣት የማይሰማቸው ክርስቲያኖች ካሉ በእውነትም በልደት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረንን ቀጠሮ የማክበር ቃልን የመጠበቅ አሰረ ፍኖት የዘነጉ መሆናቸውን መረዳት አለባቸው፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሚያስተላልፈው ዐቢይ መልእክትም ይህን ነው፡፡ ‹‹ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም›› እንደተባለ በቃላችን የምንገኝ፣ ባልነው የምንጸና ተአማኒ መሆን ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡
ባጠቃላይ በልደቱ ያገኘናቸውን ሀብታት በመጠበቅ፣ የተማርናቸውን ትምህርቶች በመፈጸም እውነተኛ የልደት በዓል ተካፋዮች መሆን ይገባናል፡፡ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ሰማያውያን መላእክት ከምድራውያን እረኞች ጋር በአንድ ላይ እንዳመሰገኑ እኛም በዝማሬና በምስጋና በፍፁም ደስታ ልናመሰግን ይገባል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡