“ታሪክ የሚሠራው ከታሪክ ነው።”

  በኪ/ማርያም

በአዲስ አበባ የስብሰባ ማዕከል አዳራሽ ጥር 01 ቀን 2003 ዓ.ም በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ‘ሕያው እውነት’ በሚል ርዕስ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የኦዲዮ ቪዥዋልና ሥነ ጥበባት ሥራዎች ማእከል አማካኝነት የተዘጋጀው መንፈሳዊ ፊልም ብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ተመረቀ።

በፊልሙ ምርቃት ላይ ብጹእ አቡነ ሚካኤል የወላይታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ ብጹእ አቡነ ያሬድ የምሥራቅ ሐረርጌ ሊቀጳጳስ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም መለሠ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያ ሓላፊ፣ መጋቢ ሥርዐት ዳንኤል ወልደ ገሪማ የቁልቢ ገብርኤል ንዋያተ ቅድሳት ማደራጃ መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የቅ/ሥ/መ/ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ መምህር ደጉ ዓለም ካሣ፣ አባ ምንይችል ከሠተ፣ ሊቀመዘምራን ኪነጥበብ ወልደ ቂርቆስ፣ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያም የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ፣ በፊልሙ የተሳተፉና ተጋባዥ አርቲስቶች እንዲሁም ምዕመናን ተገኝተዋል።

hyawEwnet.jpg

የዚህን የፊልም ምረቃ ከሌሎች በሀገራችን ከተመረቁ ፊልሞች ለየት የሚያደርገው፣ ብዙ ሕዝብ ተገኝቶ የመረቀው ፊልም በመሆኑ ነው። የመርሐ ግብሩ መሪ ዲ/ን አባይነህ ካሴ ከዚህ በፊት በሌሎች የፊልም ምርቃት ላይ መገኘቱን አውስቶ ብዙዎቹ ፊልሞች ሲመረቁ የሚገኘው የሕዝብ /የተመልካች/ ብዛት እምብዛም ነው በማለት በመድረክ ላይ አስታውቋል።

በፊልሙ ምርቃት ላይ ሊቀመዘምራን ኪነ ጥበብ ወልደ ቂርቆስ ዝማሬ አቅርበዋል፣ ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ “የተደፈኑትን ጉድጓዶች አስቆፈረ”ዘጸ 26፥18 በሚል ርዕስ ትምህርተ ወንጌል ሠጥተዋል። ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሲሳይ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ሰብሳቢ  የማኅበረ ቅዱሳንን መልእክት አስተላልፈዋል።
 
የማኅበሩን አመሠራረት ከመነሻው ጠቅሰው የአገልግሎቱን ዘርፈ ብዙነትም፤ ይህም አገልግሎት ከሀገራችን አልፎ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እንዲሁም በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በልዩ ልዩ የህትመት ውጤቶች፣ በራዲዮ፣ በመካነ ድርና የተለያዩ ዐውደ ርዕዮችን በማዘጋጀት ቤተ ክርስቲያንንና ሀገራችን ኢትዮጵያን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት አስተዋውቋል፤ በማስተዋወቅም ላይ ይገኛል። አሁንም አገልግሎቱን በማጠናከር በሀገራችን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን መንፈሳዊ ፊልም አዘጋጅቶ አቅርቦላችኋል በማለት ገልጸዋል።

በመቀጠል የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያንም የሥነ ጽሑፍና የሥነ ጥበብ ምንጭ እንደመሆኗ መጠን ያላት ታሪክና የሥነ ጽሑፍ ሀብት ገና በአግባቡ ያልተዳሰሰና ብዙ  የሚያሠራ ነው። በዚህም ምክንያት ማንኛውም የፊልም ጸሐፊ የመረጠውን ጭብጥ የማቅረብ እድሉ እጅግ ሰፊ ነው። በዚህም በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ሰ/ማ/መ/ ማኅበረ ቅዱሳን የኦዲዮ ቪዥዋልና ሥነ ጥበባት ሥራዎች ማእከል ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በዋናነት በማንሳትና የሀገራችንን ባህልና ወግ የሚያንፀባርቅና በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚሠራውን ደባ መንፈሳዊ ቀናኢነት፣ ሃይማኖትን ሥልጣኔን የአባቶቻችን ጽኑ ሀገራዊ ጀግንነት በጉልህ የሚታይበት መንፈሳዊ ፊልም ሰርቶ እነሆ ዛሬ ለምረቃ አቅርቧል።

ፊልሙም በእውነት ኢትዮጵያዊ በሆነ አቀራረብ የተዘጋጀ ሲሆን በተመስጦ በዘመናት መካከል ወደ ኋላ ወስዶ የቤተ ክርስቲያንን የሥልጣኔ በር ከፋችነት በማስረዳት በቁጭት የሚያነሳሳ፣ የሚያስተምር፣ ማንነትን የሚያሳውቅ፣ አርዓያና ምሳሌ እንዲሁም ማሣያ የሚሆን መንፈሳዊ ፊልም ነው።

ዝግጅቱም በታዋቂ አርቲስቶችና ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያኗ አካላት የተውጣጡ ከ400 በላይ በሆኑ የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች የተሠራ ነው። ‘ሕያው እውነት’ ፊልም አጠቃላይ ሥራው በአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት መሥራት የተቻለ ሲሆን የአርቲስቶቹንና የተሳታፊዎችን ነፃ ድጋፍ ሳይጨምር ከ285,000.00 ብር በላይ ወጪ እንደወጣበት ለመረዳት ተችሏል።

ይህ ፊልም ከምረቃ በኋላ ሁሉም ኅብረተሰብ እንዲያየው የማኅበሩ መዋቅር በሚደርስባቸው ቦታዎች ሁሉ ለእይታ ይቀርባል። በመጨረሻም በቪ ሲዲ ና በዲቪዲ ታትሞ ለምዕመናን የሚቀርብ ይሆናል።

በፊልሙ የሚገኘው ገቢ ማኅበሩ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚማሩ ወጣት ተማሪዎችን ለማስተማርና ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም የአባላትንና የምዕመናንን ጉልበትና እውቀት አስተባብሮ ገዳማትና አድባራትን በጊዜያዊነት እንዲረዱና በቋሚነት ከችግር እንዲወጡ ለማድረግ የሚውል ይሆናል።

የማኅበሩ ኦ/ቪ/ሥ/ማእከል ይህ ለቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ የሆነውን መንፈሳዊ ፊልም የማዘጋጀት ሂደት ከፍተኛ ልምድ አግኝቶበታል። በቀጣይም ይህን ልምድ በመጠቀም የተሻለ ሥራ ይዞ ለመቅረብ፣ የአፄ ዘርዐ ያዕቆብን ታሪክ ና የቅድስት እናታችን የወለተ ጴጥሮስን ገድል በፊልም መልክ በመሥራት ጽሑፉን የማዋቀር ሥራ ጀምሯል። በአጭር ጊዜም ለማጠናቀቅ ይታሰባል።

በአጠቃላይ በዚህ ደረጃውን ጠብቆ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዐትና ትውፊት ሣያፋልስ ቤተ ክርስቲያን ለሀገሪቱ ያበረከተችውን ሥልጣኔ እንዲያሳይ እንዲሁም የሀገራችንን ባህልና ወግ እንዲያንፀባርቅ ተደርጎ በተሠራው መንፈሳዊ ፊልም ላይ ለተሳተፋችሁ የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ አርቲስቶች እንኳን ደስ! አላችሁ እያልኩ በቀጣይም ምክራችሁና የሙያ ድጋፋችሁ እንዳይለየን በእግዚአብሔር ስም እጠይቃለሁ፤ ከፊልሙ ጋር መልካም ቆይታ እንድታደርጉ እጋብዛለሁ። በማለት ንግግራቸውን ጨርሰው የፊልሙን ምርቃት አብስረዋል።

ፊልሙም ታይቶ ሲያበቃ በምረቃው ላይ በተገኙ ብጹአን አባቶች፣ ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፣ ከፊልም ባለሞያዎችና አርቲስቶች አንዲሁም ከተሣታፊዎች መካከል አስተያየቶቻቸውን እንዲሰጡ እድሎች ቀርበው ሃሳብ ተሰጥቷል።

ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም መለሠ በመጀመሪያም ይህን ፊልም ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ ላደረገ ለማኅበረ ቅዱሳን ምስጋናቸውን አቅርበው ከፊልሙም ያገኙትን ጭብጥ “ፊልሙ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ያለው ነው በማለት አስረድተዋል። ይህ ደግሞ ለአዲሱ ትውልድ ፈር ቀዳጅና አስተማሪ ነው። ወደ ኋላ ራሱን እንዲያስተውል የሚያደርግና ጽናቱን የሚፈትሽ በመሆኑ ፍጹም አስተማሪ ነው። ታሪክ የሚሠራው ከታሪክ ነው። ታሪክ ሕይወት አለውና በየዘመኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል። ታሪክ እንደ ሰው አካል ስላለው አካሉ እንደተጠበቀ መቆየት ይኖርበታል። አካሉን ማጉደል ተጠያቂ ያደርጋልና ከዚህ መንፈሳዊ ፊልም የተማርነው መንፈሳዊ የፍትሕ አሰጣጥ፣ ጥንታዊ እይታን ወደ ኋላ እንድናስብ፣ የሽማግሌዎች ሚና እንዲሁም ባህሎቻችን፣ ሥርዐቶቻችን ምን ያህል ጠንካራ እንደነበሩ እንደናስተውልም የሚያስተምር መንፈሳዊ ፊልም ነው። ታሪክ የአንድ ሕዝብ መለኪያ መነሻና መደረሻ እንደመሆኑ መጠን ራሱን ማየት የሚችለው ራሱን ሆኖ በመሆኑ ይህ ፊልም ለኢትዮጵያውያን ራሳችንን በመስታወት እንድናይ ያስቻለ ፊልም ነው። ዘመኑንም ራስን እንዳለ ጠብቆ ነገር ግን ወደኋላ ራሱን እንዲያይ ዘመኑን እንደ መስታወት ተጠቅሞ /ቴክኖሎጂውን/ በእድገት ላይ እድገት ለመጨመር መጀመሪያ ከራስ እድገት መነሣት ስለሚገባ ፍጹም አስተማሪ ነው።” በማለት በዚህ ፊልም መደሰታቸውንና ሌሎች ፊልሞች ተዘጋጅተው አማራጮች ቢኖሩ የቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የሀገራችንን ታሪክ እንድናስተውል ያደርጋል ሲሉ ሀሳባቸውን ገልጸዋል።

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር የሆኑት መምህር ደጉዓለም ካሣ ይህን ፊልም ያዘጋጁትን አካላት አመስግነው ይህ ፊልም በከተማ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር በተለይም በገጠሪቷ የሀገራችን ክፍል የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ያልተበረዘ እምነት የያዙ ምዕመናንን ቢያዩት ለዚህም የተለየ ቦታ ተፈልጎ ችግሩን የማያውቁት እነርሱ ናቸውና ፊልሙ ቢታይ በጣም ጥሩ ነው ብለዋል። በመጨረሻም በአቡጊዳ ትምህርት፣ በመልእክተ ዮሐንስ፣ በዳዊት፣ በዜማ፣ በቅኔ ብዙ ያልሄዳችሁ በዘመናዊ ትምህርት የበለጸጋችሁ ስትሆኑ የእናንተን አካሄድ በቤተ ክርስቲያን ቀጥ አድርጎ ያቆመ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል።

ከመንፈሳዊና ከሙያዊ አንጻር የተሰጡ አስተያየቶችን የመድረክ መሪው በይፋ በመቀበል በመጨረሻም ስፖንሰር ላደረጉ ድርጅቶች፣ በፊልሙ ለተሳተፉ አርቲስቶችና የተለያዩ እገዛዎችን ላደረጉ ሰዎች በብጹአን አባቶች የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን በብጹእ አቡነ ሚካኤል ቡራኬ የፊልሙ ምርቃት መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል።
                                                         ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                                                             አሜን።