የገና በዓል አከባበር በቅዱስ ላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት
በወ/ኪዳን ጸጋ ኪሮስ
በብርሃነ ልደቱ ዋዜማ ከቅዱስ ላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት በዓሉን አስመልክቶ የማኅበረ ቅዱሳን የአማርኛ መካነ ድር በስልክ ከደብሩ ዋና አስተዳዳሪ ከሆኑት ቆሞስ አባ ገ/ኢየሱስ መኮንንና ከአገልጋይ ካህናት ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበናል መልካም ንባብ።
አማርኛ መካነ ድር፦ የበዓል አከባበር ሥርዐቱ ምን ይመስላል?
ቆሞስ አባ ገ/ኢየሱስ መኮንን፦ በዛሬው ዕለት ማለትም ታህሣሥ 29 ቀን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልና የገናናው ንጉሥ የቅዱስ ላልይበላ የልደት በዓል በአንድነት ይከበራል።
በዓሉ በቦታው አገልጋይ በሆኑ 670 ካህናትና በአካባቢው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በሚያገለግሉ ከ500 በላይ በሚሆኑ ካህናት ታጅቦ ማህሌቱ ይካሄዳል፤ በዚህ በዓል መላው ነዋሪ ‘ካህን’ የመስሎ ሚታይበት አከባበር ነው፤ የማህሌት ሥነ ሥርዐቱ 2፡30 (ማታ) ብጹእ አቡነ ቄርሎስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መሪነትና ሌሎች ብጹአን አባቶች በሚገኙበት በየዓመቱ ይከበራል።
በዓሉ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ መከበር የጀመረው ከ900 ዓመት በፊት ነው። ከታህሳስ 23(በዓለ ጊዮርጊስ) ጀምሮ እስከ ዛሬ (ታህሳስ 28) ድረስ ሁሌም 2፡00 ሰዓት ሲሆን የሥርዐተ ማህሌት ደወል ይደወልና በአገልግሎት ይታደራል።
ይህ በዋዜማው የሚካሄደው የማህሌት ሥርዐት 1፡30 አካባቢ የሚጀመር ሲሆን ልዩ የሚያደርገው የራሱ ቀለምና ዜማ ያለውና ሙሉ ሌሊቱን በወረብ ዝማሬ እየቀረበ የሚታደር መሆኑ ነው።
የማህሌት ሥነ ሥርዓቱ በብጹዕ አቡነ ቄርሎስ አባታዊ መሪነትና በአስተዳዳሪው አስተባባሪነት እንዲሁም በመሪጌታው በሚመሩ ከ7 ባልበለጡ አስተናጋጆች በሥርዓት ይካሄዳል።የማህሌቱን አካሄድ ስንመለከትም አንድ ጊዜ ከ 12 ያልበለጡ ጥንግ ድርብ የለበሱ’ አንድ ጊዜ ደግሞ ከ 12 ያልበለጡ ጥቁር ካባ የለበሱ በድምሩ 24 ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ከቀኝና ከግራ ሆነው በተራ እያሸበሸቡ ያስኬዱታል፡፡
ማህሌቱም ማዕጠንት በያዙ 4 ካህናትና ከ8 ያላነሱ ዲያቆናት ወርቅ ካባ ለብሰው፣ የወርቅ አክሊል ደፍተው፣ የወርቅ መስቀል ይዘው መለከት እየነፉ ዙሪያውን በመዞር ማህሌቱን ያጅቡታል። የዚህም ምሳሌነቱ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ መላእክት መለከት እንደሚነፉ ለመግለጥ ሲሆን ለማህሌቱ ትልቅ ድባብ ይፈጥራል። የማዕጠንት ሥርዐቱ ካህናቱ በሊቀ ካህናቱ፤ ዲያቆናቱ በሊቀ ዲያቆኑ ይመራሉ።
ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በአስራ አንዱም ቤተመቅደስ የቅዳሴ ሥርዐት ይፈጸማል። በተለይም ያሉትን ቆራብያን በተቀላጠፈ መልኩ ለማስተናገድ በቤተ ማርያምና በቤተ መድኃኒዓለም በሁለት ልዑክ ቅዳሴው ይከናወናል።
ከ12፡00 ሰዓት ጀምሮ ጥንግ ድርብ፣ ካባ እንዲሁም ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናት ከአስራ አንዱ ቤተመቅደስ ከእያንዳንዳቸው ከአስራ ሁለት ያላነሱ ካህናት ይህንን ያሬዳዊ ዜማ ለማጀብ ወደ ማሜ ጋራ /ቤዛ ኩሉ ዓለም ሥነ ሥርዓት የሚካሄድበት ቦታ/ ይወጣሉ።
ልክ አንድ ሰዓት ሲሆን ከላይና ከታች የሚሰለፉ ካህናት ቦታቸውን ይይዙና እስከ 4 ሰዓት በሚፈጅ ክንውን እየተቀባበሉ ለሀገር፣ ለወገን፣ ለምድር ሰላም በረከት የሚጸለይበት ‘ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ’ የተባለው የቀለም ክንውን ይካሄዳል። እንግዲህ የበዓሉን አከባበር በቅዱስ ላልይበላ ልዩ የሚያደርገው አንዱ ይህ “ቤዛ ኩሉ ዓለም” የሚባለው የቀለም ዓይነት ነው።
አማርኛ መካነ ድር፡- የቅኔ ሥርዐቱስ ምን ይመስላል?
ቆሞስ አባ ገ/ኢየሱስ መኮንን፡-ቅኔ የሚሠጠው የሠዓቱ ሁኔታ ታይቶ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ተጠይቀው ሲፈቅዱ ከ3 ያላነሱ የቅኔ ባለሞያዎች (የቅኔ መምህራን) ያራምዱታል (ያስኬዱታል)። በዚህ ክብረ በዓል ላይ የሚቀርቡት ቅኔዎች ጥልቅ ምስጢር ያዘሉ ናቸው፡፡
አማርኛ መካነ ድር፡-አባታችን በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
ቆሞስ አባ ገ/ኢየሱስ መኮንን፡- ይህ በዓል ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ኩራት በመሆኑ በውጪ ላሉ ሰዎች መተዋወቅ ያለበትና ሁላችንም ለዚህ የበኩላችንን አስተዋፅኦ መወጣት ይገባናል፡፡ ይልቁንም በመንፈሳዊ አገልግሎታችን በቤተክርስቲያናችን ሥርዐት የሚከበረው ይህ በዓል ልዩ ስሜት የሚፈጥር በመሆኑ ለሁሉም መተዋወቅ የሚገባው ነው፡፡
በመጨረሻም በዓሉን ለማክበር ከተለያየ ቦታ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከኤዥያ፣ ከአፍሪካ እንዲሁም ከመላው ኢትዮጵያ የመጡ ምዕምናን በዓሉን በሰላም አክብረው ወደየመጡበት በሰላም እንዲመለሱ የእግዚአብሔር ቸርነት ይሁንልን፡፡ የጻድቁ የቅዱስ ላሊበላ በረከትም ከሁላችን ጋር ይሁን።
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በመላው ዓለም የሚከበር ሲሆን በቅዱስ ላልይበላ በድምቀት የሚከበረው ከቅዱስ ላልይበላ የልደት በዓል ጋር አብሮ በመሆኑ ነው።በዚህ በዓል በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ምዕመናን መንፈሳዊ በዓሉን ለማክበርና በረከት ለመሳተፍ የሚጓዙ ሲሆን ሌሎቹም አብያተ ክርስቲያናቱንና መንፈሳዊ የበዓል ሥርዐቱን ለመጎብኘት ነው። ይህም በዓል ሃይማኖታዊ፣ መንፈሳዊ፣ ትውፊታዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሀገራዊ ፋይዳ አለው።ይህንንም ለማስረገጥ በየዓመቱ ያለማቋረጥ ምዕመናን ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች መምጣታቸው ነው።
በተጨማሪ ኢአማንያን ይህንን መንፈሳዊ ቦታ ካዩ በኋላ ከሥላሴ ልጅነት አግኝተው ወደተለያዩ ዓለም ተመልሰዋል። ይህም በዓሉ ለአካባቢውና ለሀገራችን ብሎም ለውጭ ሀገር ዜጎች በየዓመቱ እንዲናፈቅ ሆኗል።
በተጨማሪ ኢአማንያን ይህንን መንፈሳዊ ቦታ ካዩ በኋላ ከሥላሴ ልጅነት አግኝተው ወደተለያዩ ዓለም ተመልሰዋል። ይህም በዓሉ ለአካባቢውና ለሀገራችን ብሎም ለውጭ ሀገር ዜጎች በየዓመቱ እንዲናፈቅ ሆኗል።
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሣህልና ምሕረት
የጻድቁ የቅዱስ ላሊበላ ረድኤትና በረከትም ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።
የጻድቁ የቅዱስ ላሊበላ ረድኤትና በረከትም ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።