ማኅበረ ቅዱሳን የመጀመሪያ ፊልሙን ሊያስመርቅ በዝግጅት ላይ ነው፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን ኦዲዮ ቪዥዋልና የሥነ ጥበባት ሥራዎች ማእከል ‹‹ሕያው እውነት›› በሚል ርዕስ የተሠራው ፊልም በአዲስ አበባ የስብሰባ ማእከል ጥር 1 ቀን 2003 ዓ.ም ይመረቃል፡፡
በፋሲል ግርማ የተዘጋጀው ይህ ፊልም የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክ ለሀገሪቱ ሥልጣኔ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በዋናነት ያወሣል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚሰራው ደባ፣ መንፈሳዊ ቀናዒነት፣ ሃይማኖትና ስልጣኔ የአባቶቻችን ጽኑ ሀገራዊ ጀግንነት ከታሪክ ማኅደር እየተቀዳ በጉልህ የሚታይበት ነው፡፡
ከ400 በላይ ሰዎች የተሳተፉበት ይህ ፊልም ከ250.000 ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ወጪውን የትራንስፖርት፣ የምግብ፣ የቁሳቁስ፣ የአልባሳት፣ ወዘተ ወጪ ብቻ ሲሆን ታዋቂ ተዋንያን በፊልሙ ላይ የተወኑት ያለ ክፍያ ለአገልግሎት እንደሆነ አርቲስት ቶማስ ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም የኪነጥበብ ምንጭ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ ማንኛውም ክርስቲያን ሙያዊ አስራት ማቅረብ አለባቸው፡፡ የኪነ ጥበብና የሙያ ሰዎችም በሙያቸው ቤተክርስቲያንን ሊያገለግሉ ይችላሉ ብለዋል፡፡
አሁንም ሊሠራ ተጽፎ ኤዲቶሪያል ቦርድ የገባ እንዲሁም ገና እየተዘጋጀ ያለ ፊልም አለን በእነዚህ ፊልሞች የካሜራ ባለሞያዎች፣ ኤዲተሮች፣ ዳይሬክተሮች የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት የልጅነት ድርሻቸውን ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ሊወጡ ይችላሉ ብለዋል፡፡
የፊልሙ ገቢም በዋናነት የማኅበሩን የስብከተ ወንጌል ለመደገፍ እንደሚውል የገለጹት አቶ ቶማስ በተጨማሪም የማኅበሩን ህንጻ ማስፈጸሚያ ገቢ እንደሚስያስገኝ ይታመናል፡፡ ስለሆነም ምዕመናን በፊልሙ እየተማሩ ትሩፋትን እንዲሠሩ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በማለት ይጠቀልላሉ፡፡
ፊልሙ በማኅበሩ የሀገር ውስጥ 39 ማእከላትና በውጭም በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓ፣ በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በግብጽ፣ በጅቡቲ፣ በኢየሩሳሌም፣ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስና በሌሎችም አገሮች ለእይታ ይቀርባል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ቴአትር ቤቶች በመከራየትና በቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ መድረኮች ለዕይታ ይበቃል፤ በመጨረሻም በዲቪዲና ሲዲ ታትሞ ለገበያ ይቀርባል፡፡