በልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት
ይህ ዘርፍ ማኅበረ ቅዱሳን ከሚሰጣቸው መንፈሳዊ አገልግሎቶች በተጨማሪ የተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖ ሚያዊ ሥራዎች የሚሠራበት ዘርፍ ነው፡፡ በዚህም ለቅዱሳት መካናት፣ ለአብነት ትምህርት ቤቶች መምህራን እና ተማሪዎች፣ ለምእመናን ብሎም ለጠቅላላው ኅብረተሰብ አቅም በፈቀደ መጠን ዘላቂ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ረገድ በገንዘብ፣ በዓይነት፣ በዕውቀት እንዲሁም በጉልበት እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል ለአብነት ትምህርት ቤቶች መምህራን እና ተማሪዎች ድጎማ፣ ለገዳማት፣ አድባራት እና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ጊዜያዊ ርዳታ፣ የዘላቂ ገቢ ቋሚ የልማት ፕሮጀክት ቀረፃና ትግበራ፣ ጉዳት ለደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ የማድረግ፣ ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ በቀጣይም የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮችን በመፍታት ዙርያ ለመሥራት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በትምህርት መስክ በአዲስ አበባ ሦስት ቦታዎች ላይ፣ በአዋሳ፣ በደብረ ብርሃንና፣ በባሕርዳር፣ ሃገረ ማርያም ወዘተ የራሱን መደበኛ ት/ቤት በመክፈት ሕፃናት በመንፈሳዊና በዘመናዊ ዕውቀታቸው ዳብረው እንዲወጡ እያደረገ ይገኛል፡፡
ሀ. አብነት ት/ቤቶችን ከመደገፍ አንጻር
አብነት ትምህርት ቤት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት፣ ሥርዓት፣ ታሪክና ትውፊት ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ የሚቻልበት ብቸኛ መድረክ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓቷን፣ ትውፊቷንና ትምህርቷን በየዘመኑ የሚቀበል ትውልድ እንዳታጣ የአብነት ት/ቤቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ የአብነት ት/ቤቶች በተለያየ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግር ምክንያት የከፋ አደጋ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይም ጥንታውያን የሆኑት የአብነት ት/ቤቶች እና ሊቃውንቶቻቸው ቀደም ሲል የነበረው የመሬት ባለቤትነታቸውን በማጣታቸው እና የአካባቢው ምእመንም ቀደም ሲል ያደርግላቸው የነበረውን ድጋፍ በኑሮው ጫና ምክንያት በማቆሙ፣ መምህራኑ ወንበራቸውን አጥፈው ለመሰደድ፤ ተማሪዎቻቸውም ለመበታተን ተዳርገዋል፡፡ የነዚህ ለመላው አብያተ ክርስቲያናት የአገልጋይ ምንጭ የሆኑ የአብነት ትምህርት ቤቶች ችግር ምክንያት፤ በደቡብ በምሥራቅ እና በምዕራቡ ላሉት አብያተ ክርስቲያናት የካህናት እጦት መንስኤ በመሆን አብያተ ክርስቲያናቱ እንዲዘጉ አድርጓል፡፡ ማኅበሩ ይህንን ችግር በመረዳት፤ የአብነት ት/ቤቶች መምህራንን እና ተማሪዎችን በመደጎም፣ ጥንታውያን የሆኑት የቀድሞ ይዞታቸው ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ እና በደቡብ፣ በምሥራቅ እና በምዕ ራቡ የሀገሪቱ ክፍል ደግሞ የአካባቢውን ልጆች በማስተማር አገልጋይ ካህናትን በማፍራት የበኩሉን ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ድጎማው በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚገኙ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር በወር ከአንድ መቶ እስከ ሦስት መቶ ሃምሳ ብር፣ ለስልሳ ሦስት መምህራን ድጎማ እንዲሁም አራት መቶ ሃያ ስምንት ለሚሆኑ ተማሪዎች ደግሞ በወር በሁለት መንገድ የሚፈጸም ነው፡፡ የመጀመሪያው ለመምህራኑና ለተማሪዎቹ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የመጻሕፍትና ከሠላሳ እስከ መቶ ሃያ ብር ይደጉማል፡፡ በዚህም ለአብነት ደመወዝ /ለመምህራኑ/ ድጎማ ሲሆን፤ ሁለተኛው የአብነት ት/ቤቶች ራሳቸውን እንዲችሉ ዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶችን መቅረፅና ተግባራዊ ማድረግና ለመምህራን እና ተማሪዎች ድጎማ ያደርጋል፡፡ በዓመት እስከ ዘጠኝ መቶ ሺሕ ብር፣ እንዲሁም የገንዘብ ድጎማ ለማይደረግላቸው አንዳንድ የአብነት ት/ቤቶች በጊዜያዊነት ለልብስ፣ ለምግብ፣ ለመጻሕፍት እና ሌሎች ወጪዎች እስከ ስልሳ ሺሕ ብር በዓመት ያወጣል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተመረጡ የአብ ነት ት/ቤቶች ተማሪዎቹ ከአብነት ትምህርቱ ጎን ለጎን ትምህርተ ሃይማኖት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የስ ብከት ዘዴ እንዲማሩ በማድረግ ለተሻለ አገልግሎት አቅም እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ለ. ገዳማትና አድባራትን ከመደገፍ አንጻር
ማኅበሩ ከአብነት ት/ቤቶች በተጨማሪ ችግር ላለባቸው አድባራትና ገዳማት ጊዜያዊ ርዳታ በማድረግ እና ዘላቂ መፍትሔዎችን በማመቻቸት የገዳማቱንና አድባራቱን ችግር በመጠኑም ቢሆን እየፈታ ይገኛል፡፡ በጊዜያዊ ርዳታ የተለያዩ የመባዕ /ጧፍ፣ ነዕጣን፣ ዘቢብና ሻማ/፣ የተለያዩ ንዋየ ቅድሳት /ልብሰ ተክህኖ፣ መጎናጸፊያ ወዘተ/፣ የዘወትር ልብስ፣ የምግብ እህልና ሌሎችን ርዳታዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ በዓመት በአማካይ ለሠላሳ ቅዱሳት መካናት የልብሰ ተክህኖ ድጋፍ፣ ለሁለት መቶ ቅዱሳት መካናት የመባዕ፣ እንዲሁም የምግብ፣ የአልባሳት እና ለሌሎች ድጋፎች በዓመት እስከ ዘጠና ሺሕ ብር ወጪ ያደርግላቸውል፡፡ በ1995 ዓ.ም በሁለት የአብነት መምህራን የተጀ መረው ድጎማ ዛሬ ቁጥሩን ከፍ በማድረግ ስልሳ ለሚሆኑ ለተመረጡ አብነት ት/ቤቶች ድጎማ ያደርጋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ገዳማትና አድባራት ያሉባቸውን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ማኅበሩ የተለያዩ የልማትና ማኅበራዊ ፕሮጀክቶችን አጥንቶ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ቅዱሳት መካናቱ ያላቸውን ነባራዊ ሁኔታ፣ ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት እና የሰው ኃይል መሠረት በማድረግ የአነስተኛ መስኖና አትክልት ልማት፣ የወተት ላም ርባታ፣ ዘመናዊ ንብ ርባታ፣ የከብት ማድለብ፣ ወፍጮ ቤት፣ ሽመና፣ የጥበበ ዕድ ፕሮጀክቶች የሚከራይ ቤት ግንባታ፣ የአብነት ተማሪዎች መኖሪያ ቤት እና የመሳሰሉትን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ቅዱሳት መካናቱን ወደ ቀደመው የልማት አውታርነታቸው ለመመለስ፣ የአካባቢውን ኅብረተሰብ የምርቶቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማ ድረግ በተጨማሪ ለአካባቢው አርሶ አደሮችም ሠርቶ ማሳያ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡
እስከ 2000 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በተለያዩ አህጉረ ስብከቶች ከአንድ መቶ ሃያ በላይ የተጠኑ የልማት ፕሮጀክቶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል እስከ 2000 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በጠቅላላው ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የፈጁ ሃያ ሦስት የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ገዳማቱ ተረክበዋቸው ሥራ ጀምረዋል፡፡ በ2001 ዓ.ም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጁ ሃያ ስድስት ከአለፈው የቀጠሉ ፕሮጀክቶች እና ሰባት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ከተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር በጎ አድራጊዎች የገንዘብ እርዳታ ማሰባሰብ ሥራ በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡ የእነዚህ ፕሮጀክቶች የእያንዳንዳቸው ጠቅላላ ወጪ ከ35,000 እስከ 350,000 ብር የሚደርስ ሲሆን እንደ ፕሮጀክቱ ዓይነት ሊለያይ ይችላል፡፡ በዚህም የአምስት ዓመት ጉዞ በአብነት ትምህርቱ፣ በገዳማትና አድባ ራት ድጋፍ ከሃያ ሚሊዮን ብር በላይ በዘላቂና ጊዜያዊ ፕሮጀክቶች ላይ ወጪ ተደርጓል፡፡
ሐ. ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረግ
ማኅበሩ በተለያዩ ሰው ሠራሽም ሆኑ ተፈጥሮአዊ ምክንያቶች ችግር ከደረሰባቸው ገዳማትና አድባራት ባሻገር በችግር ውስጥ ያሉ ምእመናንንም በመታደግ እንቅስቃሴ ያደርጋል፡፡ በመስከረምና ጥቅምት 1999 ዓ.ም በአክራሪ እስልምና እንቅስቃሴ ጉዳት ለደረሰባቸው የጅማ፣ ኢሉባቦር እና የምዕራብ ወለጋ አህጉረ ስብከት ምእመናንን እና አባላትን በማስተባበር የመልሶ ማቋቋም ሥራ ሠርቷል፡፡ በዚህም ለተፈናቀሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ርዳታ ጤፍ፣ በቆሎና ማሽላ በጠቅላላው ለዘጠኝ መቶ ሃያ ስድስት አባወራ አምስት መቶ አሥራ አንድ ኩንታል ገዝቶ አከፋፍሏል፡፡ በኢሊባቦር ለተቃጠሉ ቤቶችም መልሶ ግንባታ ለሃምሳ አንድ አባወራ ለእያንዳንዳቸው አርባ ቆርቆሮና ሚስማር ሰጥቷል፡፡ በኢሊባቡር እና በምዕራብ ወለጋ ለተቃጠሉ ሦስት አብያተ ክርስቲያናት ማሠሪያ ሁለት መቶ ሃምሳ ቆርቆሮ፣ ሦስት መቶ ኩንታል ሲሚንቶ እና አንድ መቶ ሺሕ ብር አስረክቧል፡፡ በአካባቢው ያሉ አብያተ ክርስቲያናትንና ሰንበት ት/ቤቶችን ለማጠናከር ለአሥር አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ አልባሳትና አንድ መቶ ዘጠና ሁለት መጽሐፍ ቅዱስ ገዝቶ ያከፋፈለ ሲሆን ለአምስት መምህራንና ለሁለት አብያተ ክርስቲያናት ካህናትና ዲያቆናት የአንድ ዓመት ደመወዝ መድቧል፡፡ የሁለት መምህራንን ቅጥርም አካሒዷል፡፡ በጅማ አካባቢ ያሉትን አብያተ ክርስ ቲያናትና ምእመናን በደረሰው ጉዳት ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችን ለመርዳት ሁለት የኤሌክትሪክ እና ሁለት በናፍጣ የሚሠሩ ወፍጮዎችን ገዝቶ ያስተከለ ሲሆን እንዲሁም ስድስት ክፍል ያለው መጸዳጃ ቤት በማሠራት ለገዳሙ አስረክቧል፡፡ በምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት ላሉ ሠላሳ ሁለት ካህናት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
በ2000 ዓ.ም ደብረ ወገግ አሰቦት ገዳም ላይ ለደረሰው የቃጠሎ አደጋ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ተሠርቷል፡፡ ለገዳሙ መናንያንም በየወሩ ለቀለብ የሚሆን ስምንት ሺሕ ብር ድጎማ ያደርጋል፡፡ ከዚህ ሌላም በገዳሙ የበቀሉ አላስፈላጊ እፅዋትን ለማስወገጃ ከስልሳ ሺሕ ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡ በያዝነው በ2001 ዓ.ም «አንድ መጽሐፍ ይለግሱ» የተሰኘ ፕሮጀክት በመቅረጽ ከአባላትና ከምእመናን ከሶስት ሺሕ አምስት መቶ በላይ መጻሕፍትን በማሰባሰብ ለተለያዩ የአብነት ት/ቤቶችና ሰንበት ት/ቤቶች የማሠራጨት ሥራ ተሠርቷል፡፡
መ. ኤች አይ ቪ/ኤድስን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ
ማኅበሩ ኤች አይ ቪ/ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድም ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን እየሠራ ይገኛል፡፡ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ እያስጨበጠ ይገኛል፡፡ የቤተ ክርስቲ ያን ትምህርትን መሠረት ያደረጉ የመከላከያ እና የመቆጣጠሪያ ዘዴዎች ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ከስዊድን የሕፃናት አድን ድርጅት፣ ከዓለም ባንክ፣ ከአክሽን ኤይድ እና ቪ.ኤስ.ኦ. ከተባሉ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎችንም ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከተሠሩትም ሥራዎች መካከል ተከታታይ ጽሑፎች በ«ስምዐ ጽድቅ» ጋዜጣ እና «ሐመር» መጽሔት በማውጣት፣ አርባ የሚሆኑ ፀረ ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ ክበባትን ማቋቋም፣ ለዘጠኝ መቶ ዘጠና ሦስት ካህናትና ካውንስለሮች ሥልጠና በመስጠት፣ ለስድስት መቶ አምስት የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችና ሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች የአቻ ለአቻ የምክር አገልግሎት በመስጠት፣ ውይይቶችና በሃያ አምስት አህጉረ ስብከት ላይ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ዙሪያ የዳሰሳ ጥናቶች ማድረግ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በ2001 ዓ.ም ከጥቅምት ወር ጀምሮ ከብሔራዊ የኤች አይ ቪ/ ኤድስ መቆጣጠሪያና መከላከያ ጽ/ቤት በተገኘ ከአምስት መቶ ሺሕ ብር በላይ በሆነ ገንዘብ ጠበልን ከፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት ጋር አስማምቶ መጠቀም ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡
በዚህ ዘርፍ ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለምእመናን ብሎም ለጠቅላላው ኅብረተሰብ አቅም በፈቀደ መጠን በገንዘብ፣ በዓይነት፣ በዕውቀት እንዲሁም በጉልበት እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡
ሠ. የሙያ አገልግሎት
የማኅበሩ አባላት በገቡት ቃል መሠረት የተለያየ ሙያ ያላቸው አባላት ማኅበሩንና ቤተ ክርስቲያንን በሙያቸው፣ በዕውቀታቸው፣ በገንዘቸው፣ በጉልበታቸው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በተለይም በምህንድስና እና ጥበበ ዕድ ክፍል ባለሙያዎች ለተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የዲዛይን፣ የቅየሳ፣ የሱፐርቪዥን ወዘተ ሥራ በመሥራት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ለቤተ ክርስቲያን እያዳኑ እና የቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል ከ1995 ዓ.ም ወዲህ ከተሠሩትና በዋነኛነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ለስምንት የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶች ዲዛይንና የዋጋ ዝርዝር፣ ለሰባ አምስት አብያተ ክርስቲያናት ሕንፃ ዲዛይን፣ ከሠላሳ በላይ ለሆኑ አብያተ ክርስቲያናት የጥገና ዲዛይን፤ እንዲሁም ከሠላሳ በላይ ለተለያዩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ዲዛይኖችን ሠርተው አስረክበዋል፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያን ልታወጣ የነበረውን ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ እንዳታወጣና ወጭ እንድትቆጥብ አድርጓታል፡፡ የሕግ ባለሙያዎቹም የሕግ ምክር አገልግሎት ለሚፈልጉ የቤተ ክርስቲያን አካላት የምክር አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ እንዲ ሁም የተለያዩ የሒሳብና የአስተዳደር ማንዋሎች ተሠርተዋል፡፡ ለቱሪዝም ቅርስ ጥበቃና ክብካቤ የሚረዳ ስትራቴጂክ ዕቅድ በማዘጋጀት ለጠቅላይ ቤተ ክህነት አስረክቧል፡፡ «ቅርስና ቱሪዝም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን» በሚል ርዕስ ከቅርስና ቱሪዝም ጋር ግንኙነት ላላቸው ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች በማዘጋጀት ባለድርሻ አካላት ባሉበት አቅርቦ ውይይቶች እንዲካሔዱ አድርጓል፡፡ በማኅበራዊና ምጣኔ ሀብት ክፍል ለአብነት ትምህርት ተማሪዎችና ገዳማዊያን ያሉባቸውን የጤና ችግሮች ላይ መፍትሔና ቅድመ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚመጡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የመገምገምና የማበልጸግ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡
ማኅበሩ አገልግሎቱ እየሰፋ በመጣ ቁጥር በየቦታው በተበታተነ ሁኔታ የሚከራያቸው ቤቶች ለቢሮ አገልግ ሎት አስቸጋሪ በመሆናቸው ቀደም ሲል በጽሕፈት ቤትነት ተከራይቶ ይጠቀምበት የነበረውነ ቦታ በአባላት ልዩ መዋጮና በበጎ አድራጊዎች ርዳታ በ1.3 ሚሊዮን ብር በመግዛት የሕንፃ ግንባታው ሥራ ተጀምሯል፡፡ እስከ ሚያዝያ 2001 ዓ.ም መጨረሻም የመሠረቱንና እስከ አራተኛው ፎቅ ወለል ያለውን ሥራ አጠናቆአል፡፡
ረ. አቡነ ጎርጎርዮስ አፀደ ሕፃናትና አንደኛ ደረጃ ት/ቤት
ማኅበሩ በአሁኑ ጊዜ የቤተ ክርስቲያንን ማንነት የሚያውቁና በግብረ ገብ ትምህርት የታነፁ ሕፃናት ቁጥር ትንሽ መሆኑን በመገንዘብ ትምህርት ቤት ከፍቷል፡፡ ትምህርት ቤቱ ሰባት ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፤ ሦስቱ በአዲስ አበባ፣ አንድ በአዋሳ፣ አንድ በባሕርዳር፣ አንድ በሀገረ ማርያም እና አንድ በደብረ ብርሃን ይገኛሉ፡፡ ትምህርት ቤቱ በ2001 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በሰባቱ ቅርንጫፎች ከአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ተማሪዎች በላይ ተቀብሎ ከአፀደ ሕፃናት እስከ አምስተኛ ክፍል እያስተማረ ይገኛል፡፡ ትምህርት ቤቱ ከሃያ ለሚበልጡ ሕፃናትም የነፃ የትምህርት ዕድል ሰጥቷል፡፡
ሰ. የልማት ተቋማት
ማኅበሩ «ሐመር» መጽሔት፤ «ስምዐ ጽድቅ» ጋዜጣ፤ መጻሕፍት እና ሌሎችም የኅትመት ውጤቶቹን አሳትሞ በማሠራጨት እንዲሁም ሌሎች የማኅበሩን አገልግሎት ለመደገፍ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎችን የሚያከናውን በልማት ተቋማት አስተዳደር ቦርድ የሚመሩ የራሱ የልማት ተቋማት አሉት፡፡ የልማት ተቋማቱ በ18 ማዕከላት /አዲስ አበባን ጨምሮ/ የሚገኙ የማኅበሩን የኅትመት ውጤቶችና ንዋያተ ቅድሳት ማቅረቢያዎች ሲኖሩት በዓይነታቸውም የሚከተሉትን ያካትታሉ፡፡ የካህናት አልባሳት፣ የሞካሽ ሥራ፣ የቆብ እና ጃንጥላ ሥራ ኢንዱስትሪ፣ ንዋያተ ቅድሳት መሸጫ ሱቆች /በቁጥር ሦስት/፣ ምግብ ቤት /በቁጥር ሁለት/፣ ሐመርና ስምዐ ጽድቅ ማከፋፈያዎች /በቁጥር ዐሥራ ዘጠኝ/፣ የመብዐ /የተቀመመ ዕጣን፣ የተለቀመ ነዕጣን፣ ጧፍ፣ ዘቢብ፣ ሻማ/ ማምረቻ ኢንዱስትሪን እንዲሁም የትምህርት ማዕከል በሥሩ ያቅፋል፡፡ ከእነዚህ ገቢ ማስገኛ ተቋማት የሚገኘው ገንዘብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለስብከተ ወንጌል ማጠናከሪያ የአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማትን ለመደገፍ የሚውል ነው፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ሥርዐተ ቤተክርስቲያን ከማስጠበቅና ቤተክርስቲያንን ከአሕዛብና ከመናፍቃን ከመከላከል አንጻር ምን ሥራ ሠራ?
ማኅበረ ቅዱሳን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው የሥራ መመሪያ መሠረት ካከናወናቸው ሥራዎች በተጨማሪ የቅሰጣ ዓላማቸውን በቤተክርስቲያን ላይ ለመጫን በውስጥም በውጪም ከሚንቀሳቀሱ የመናፍቃንና ቤተክርስቲያንን እናድሳለን ብለው እስከተነሱት እኩዮች ሥራቸውን እየተከታተለ በቅዱስ ሲኖዶስና በምእመናን በመረጃ ላይ የተደገፈ ሪፖርት ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ አሁንም እያቀረበ ነው፡፡ ወደፊትም ያቀርባል፡፡ ከዚህም ሌላ በእስልምና ስም የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ አክራሪዎች በቤተክርስቲያን ላይ እያደረሱ ያሉትን የጥፋት ዘመቻ ለማስታገስና ምእመናን እንዲረጋጉ ለማድረግ አክራሪዎቹ በቤተክርስቲያን ላይ ላነሱት ጥያቄ ማብራሪያ ያለው መልስ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን እስልምናን በተመ ለከተ የሠራቸው ሥራዎችን በሚከተ ለው መንገድ ማጠቃለል ይቻላል፡፡
1. ከመጀመሪያው ጀምሮ ምእመናን አክራሪውንና ነባሩን ሰላማዊውን እስልምና ነጥለው እንዲመለከቱ ከፍተኛውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡
2.. ለሚያነሷቸው ታሪካዊና ዶግማዊ ጥያቄዎች በተጻፉት ጽሑፎች መጠንና ቁጥር ጋር ሊነጻጸር ቀርቶ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም መጠነኛ ምላሾችን ሰጥቷል፡፡
3. ተቻችሎና ተከባብሮ ስለመኖር ከየትኛውም አካል በፊት እና በከፍተኛ ሽፋን ሠርቷል፡፡
4. ስለ አክራሪ እስልምና እና ስለ ትንኮሳው እጅግ አነሥተኛ እና ክስተት ተኰር የሆኑ መረጃዎችን በመስጠት ችግሩ ሲያጋጥም ለመንግሥት ማመልከት እንደሚገባ አቅጣጫ ለማሳየት ሞክሯል፡፡
የፕሮቴስታንትና የተሐድሶ መናፍቃንን ሴራ በማጋለጥ ረገድ
ከላይ ለመግለጽ እንደሞርነው ማኅበረ ቅዱሳን የፕሮቴስታንትና የተሐድሶ መናፍቃንን ሴራ በማጋለጥ ረገድ ቤተክርስቲያንንና ምእመናን እንዲጠነቀቁ እንዲሁም የመናፍቃኑን ማንነት እንዲያውቁ በማድረጉ ረገድ በጣም ብዙ ሥራዎች ሠርቷል፤ እየሠራም ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ «የዘመቻ ፊሊጶስን» የመናፍቃን ባለብዙ በጀት ሰፊ እንቅስቃሴ ቀድሞ መረጃ ለቤተክርስቲያንና ለምእመናን በመስጠት ሴራው እንዲከሽፍ ምእመናንም እንዲጠበቁ አድርጓል፡፡ በዚህም የመናፍቃኑ ሴራ በታሰበበት ሁኔታ ሳይሔድ ተኮላሽቷል፡፡
ሌላው እግራቸውን በቤተክርስቲያን ታዛ ልባቸውን በመናፍቃኑ አዳራሽ አድርገው በቤተክርስቲያን ውስጥ በመሽሎክሎክ የሚሠሩ ተሐድሶ መናፍቃንን ማንነት መረጃ በማቅረብና በማጋለጥ ከድብቅ ዓላማቸው እንዲገቱና እንዲወገዙ አድርጓል፡፡ በዚህ መረጃም ምእመናን ማንነታቸውን እንዲለዩና እንዲጠነቀቁም ተደርጓል፡፡ /በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የነዚህ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ በገሃድ በቤተክርስቲያኒቱ ሰርገው በመግባትና ለተልዕኮ ባስቀመጧቸው የውስጥ ሰዎች አማካኝነት ተጠናክረው እየሠሩ ነው፡፡ የነዚህንም ማንነት መረጃዎቻችንን አጠናክረን ስንጨርስ ለቅዱስ ሲኖዶስና ለምእመናን የምናሳውቅ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እንገልጻለን፡፡/
በተጨማሪም ላይችሉት የተቀበሉትን የምንኩስና ሕይወት ትተው በመናፍቃኑ አዳራሽ በድብቅ ጉባኤ ያደረጉትን ግለሰቦች ማንነት በማጋለጥ ለምእመናንና ለቤተክርስቲያን አባቶች ለማቅረብ የተደረገውና መናፍቃኑ የቤተክርስቲያንን የዋሀንን ለማሳሳት አስመስለው ከሚያሳትሟቸው የሕትመት ውጤቶችና የድምፅ መልእክቶች ምንነትና ማንነት በማጋለጥ ማኅበረ ቅዱሳን መረጃ ሲሰጥ ቆይቷል፤ አሁንም ወደፊትም ይሰጣል፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ በዐለት ላይ የተመሠረተ ማኅበር ነውና ቤተክርስቲያን የሰጠችውን ሓላፊነት በብቃት ይወጣል፡፡
በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ አጽድቆ በሰጠው መመሪያና ደንብ መሠረት ማኅበሩ በዓይን የሚታይ፣ በእጅ የሚዳሰስ ለውጥ ያመጣ ሥራ ሠርቶ አሳይቷል፡፡ በማሳየት ላይም ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ወደፊትም ያሳያል፡፡ ነገር ግን በውስጥ ያሉ ሥራቸው ያልታወቀባቸው የመሰላቸው የመናፍቃኑ ዐርበኞች ማኅበሩን ሳያውቁት አልያም ለማወቅ ባለመፈለግ ጥቅመኛ አድረገው የሚያስወሩት አሉባልታ ከእውነት የራቀ መሆኑን ማንም የሚገነዘበው ሐቅ መሆኑን ሊረዱት ያስፈልጋል፡፡
እነዚህ እኩያን የቤተክርስቲያን ጠላቶች ማኅበረ ቅዱሳን ባሉት አባላትና በበጎ አድራጊ ምእመናን ድጋፍ በጉልበት በዕውቀትና በገንዘብ ቤተ ክርስቲያን ያለባትን ክፍተት እያጠና ይሞላል እንጂ ከቤተክርስቲያን ዜሮ አምስት ሣንቲም በጀት እንደ ማይመደብለት እያወቁ አለማወቃቸው ነው፡፡ በጀት ከመምሪያቸው በመመደብ ማኅበሩን ያንቀሳቀሱት ይመስል ቤተክርስቲያን ይሠሩልኛል ብላ ያስቀመጠቻቸው አንዳንድ በሓላፊነት ቦታ ላይ ያሉ የመናፍቃኑ ተላላኪዎች ግን ማኅበሩ ሒሳቡን ኦዲት እንደማያደርግና እንደማያስደርግ ጊዜያዊ ትርፍ የሚያገኙ መስሏቸው አሉባልታ በመንዛት ማኅበሩን ያልሆነ ስም ለማሰጠት ሲጣጣሩ እየተሰማና እየታየን ነው፡፡ እውነቱ ግን ይኼ አይደለም፡፡ ማኅበሩ ሲኖዶሱ ባጸደቀለት ግልጽ መመሪያን መሠረት በሚያገለግሉ ባለሙያ አባላቶቹ በየጊዜው ሒሳቡን እያሰላና እያስመረመረ ነው ሥራውን በጥራት እየሠራ የሚገኘው፡፡ ይኼንን አሠራር ለማወቅ ለሚፈልግ ማንኛውም አካል ሁሉ ማኅበሩን ቀርቦ ማየት፤ በማኅበሩም በተለያዩ አህጉረ ስብከት የተሠሩትን ሥራዎች መመርመር ይችላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን አሠራሩ ግልጽ አገልግሎቱም የሚታይ ነው፡፡ እነዚህ የማኅበሩን አገልግሎት ለማሳጣት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚለፍፉት አንዳንድ የመምሪያ ሓላፊዎች ባልሆነ ነገር ላይ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ከሚያባክኑ ይልቅ ቤተክርስቲያኒቱ የመደበችላቸውን በጀት በአግባቡ ባለመጠቀማቸው ምክንያት በየጊዜው በየጠቅላላ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ ላይ በሪፖርት ላይ ከመወቀስ ቢድኑ መልካም ይሆን ነበር፡፡
ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ለማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ ስለ ማኅበሩ አሠራር ብዙ ማለት ይቻል ነበር፤ ነገር ግን ምእመናን ከአሳሳቾች ትጠበቁ ዘንድ ስለማኅበሩ አገልግሎት ከብዙ በጥቂቱ ይኽን እውነታ እንድታውቁ እንወዳለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር